በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ክልሉ ፈጥኖ ማቋቋም አለበት – አቶ ተመስገን ጥሩነህ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ክልሉ ፈጥኖ ማቋቋም አለበት – አቶ ተመስገን ጥሩነህ

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከሰሞኑ በተቀሰቀሰው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በአፋጣኝ መልሶ እንዲያቋቁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ጠየቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የጸጥታ ኃይል ባለበትና በፖለቲካ ልዩነት ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሚወገዝ ነው ብለዋል።

አቶ ተመስገን በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት የአማራ ህዝብ ከክልሉ ውጭ በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች ከሁሉም ጋር በጋራ መኖር የሚችልና የዜጎችን በነጻነት ተንቀሳቅሶ መስራት የሚደግፍ ሕዝብ ነው ብለዋል።

ያም ሆኖ በተለያዩ ጊዜያትና አካባቢዎች የብሄርና የሃይማኖት መልክ የሚይዙ ግጭቶች እየተቀሰቀሱ ንጹሃን ዜጎች ሰለባ እየሆኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭትም ተዋልዶና ተሳስሮ የሚኖር ህዝብ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በመጻረር በንጹሃን ላይ የደረሰውን ጥቃት የክልሉ መንግስት ያወግዘዋል ብለዋል።

ወደ አገር ልማት የሚገባው ቅድሚያ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ሲቻል መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት ህግ የማስከበር አቅሙን መወጣት ይገባዋል ነው ያሉት።

በግጭቱ ሁሉም ህዝብ ተጎጂ መሆኑን ገልጸው፤ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት መድረስ የለበትም ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ከሰሞኑ በደረሰው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በአፋጣኝ ማቋቋም እንዳለበትም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መንግስት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለማቋቋም ለሚደረገው ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

(ምንጭ ኢዜአ)