በስራ አስፈፃሚው ቁርጠኝነት ማጣትና አድሎ ሀገር አደጋ ላይ ወድቃለች – የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በስራ አስፈፃሚው ቁርጠኝነት ማጣትና አድሎ ሀገር አደጋ ላይ ወድቃለች ሲል የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ገለፀ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ጥቅምት 21/2012 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ በስራ አስፈፃሚው አካል ቁርጠኝነት ማጣት፣ በአድሎና ራስ ወዳድነት ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ መፍረስ እየተንደረደረች ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ አንድነታችንን የሚፈታተኑና የዜጎችን ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ የሚቀጥፉ ክስተቶች ማየትና መስማት የተለመደ ሆኗል ያለው መግለጫው”እንዲህ ያሉ ዘግናኝ ድርጊቶች መልካቸውን እየቀያየሩ የድርጊቶቹ አፈፃፀም ስፋትና ጥልቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ ቀጥሏል ብሏል። “ሰሞኑን በኦሮሚያ በሀረርና በድሬደዋ ለማየትም ሆነ ለመስማት በሚዘገንን ሁኔታ ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ መንግስት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት 78 ንፁኃን ዜጎች ህይወታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተቀጥፏል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከባድ የአካልና የመንፈስ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በሽዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፣ ለጊዜው ግምቱ በውል ያልታወቀ ንብረት ወድሟል፣ የእምነትና የሃይማኖት ቦታዎች ተደፍረዋል፤ ተቃጥለዋል።” ሲል ኢሃን በመግለጫው አትቷል።

እንዲህ አይነቱ እሳፋሪና አሰቃቂ ተግባር በተደጋጋሚ ሲፈጠር የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ዋና ተግባሩ የሆነው መንግስት ድርጊቱን አስቀድሞ በመከላከል፣ ድርጊቱ በሚፈፀምበት ወቅትም በፍጥነት በማስቆምና በመከላከል እንዲሁም ድርጊቱን የፈፀሙ ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ በኩል የሚያሳየው ቸልተኝነትና ዳተኝነት በኢትዮጵያ መንግስት አለ ለማለት ፈፅሞ አያስችልም ብሏል። ጉዳዩ በቶሎ ካልቆመ ወደ ሀገር መፍረስና እርስ በእርስ ጦርነት እንደሚያመራ አስጠንቅቋል። “ወደ ሀገር መፍረስ እየተንደረደርን የምንገኘውና የዜጎች መጨፍጨፍ በተጠናከረ ሁኔታ የቀጠለው በአስፈፃሚ አካላት በኩል በተፈጠረ የቁርጠኝነት ማጣት፣ አድሎና ራስ ወዳድነት ምክንያት ነው።” ሲል ተችቷል።

መንግስት ተቀዳሚ ተግባሩ የሆነውን የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ አቅቶት የእርስ በእርስ ሽኩቻና የብሔር አድልዎ እየታመሰ ሐገር አደጋ ላይ መውደቋን በግላጭ እያየን ይህንኑ አካል ህግ እንዲያስከር በተደጋጋሚ መጠየቅ ሐገራችን የምትገኝበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በቅጡ አለመገንዘብ ወይም ራስን ማታለል ነው ያለው ፓርቲው፣ “የችግሮችን መፈጠር ማቆም እንደማይችል ከተፈጠሩም በፍጥነት እንደማያስቆምና አጥፊዎችንም ከአድልዎና ከወገንተኝነት ርቆ ለህግ ሊያቀርብ እንደማይችል በተደጋጋሚ ተፈትኖ ወድቋል።” ብሏል። ከምኞትና ራስን ከማታለል አስተሳሰብ ወጥቶ ችግሩን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ለእውነተኛ መፍትሔ አስተዋፅዖ ያደርጋል ሲልም ዘላቂ መፍትሔ ነው ያለውን ጠቁሟል።