" /> እስካሁን ባለው መረጃ አምስት ሰዎች ሲሞቱ ስምንት ሰዎች ደግሞ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ቆስለዋል | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

እስካሁን ባለው መረጃ አምስት ሰዎች ሲሞቱ ስምንት ሰዎች ደግሞ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ቆስለዋል

BBC Amharic : ከቅዳሜ ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬና አካባቢው ግጭት ተቀስቅሶ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል።

የሰሜን ሸዋ ዞን የሕዝብ ደህንነትና የሰላም ግንባታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ካሳሁን እምቢአለ ለቢቢሲ እንደገለፁት “አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከባለፉት ቀናት አንጻር መሻሻሎች አሉ፤ አሁንም ግን በተወሰኑ አካባቢዎች አለመረጋጋት ይታይባቸዋል” ብለዋል።

አራት ቀናትን ባስቆጠረው ግጭት ከአጣዬ ከተማ በተጨማሪ በዙሪያው በሚገኙ ሌሎች ቀበሌዎችም የተኩስ ልውውጡ ተዛምቶ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ካሳሁን “በአጠቃላይ በከተማውም ሆነ በዙሪያው አካባቢ ውጥረት አለ።

“እስካሁን ባለው መረጃ አምስት ሰዎች ሲሞቱ ስምንት ሰዎች ደግሞ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ቆስለዋል” ብለዋል።

የተገደሉትና የቆሰሉት ሰዎች በአጣዬ ከተማ ብቻ የሚኖሩ ሳይሆኑ በአጠቃላይ በኤፍራታና ግድም ወረዳ በሚገኙና ግጭቱ በተቀሰቀሰባቸው ቀበሌዎች የሚኖሩ “በተኩሱ ተሳትፎ ያልነበራቸው ንጹሓን ዜጎች” መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለመሆኑ በማንና በማን ነው ተኩስ የሚካሄደው? ተብለው የተጠየቁት አቶ ካሳሁን “ክልሉን ሰላም ለመንሳት በሚደረገው እንቅስቃሴ በየአካባቢው አጀንዳ ተሰጥቶት የሚንቀሳቀስ ኃይል አለ። ሸዋ ላይም በነዚህ ኃይሎች ነው ችግሩ እየተፈጠረ ያለው” ብለዋል።

የግጭቱን መነሻ በተመለከተ “ጉዳዩ የሚጣራ ሆኖ አጣዬ ላይ የሥራ ስምሪት በተሰጣቸው ልዩ ኃይሎች ላይ በተቃጣ ተኩስ ነው አሁን ወዳለንበት ቀውስ የገባነው” ብለዋል መምሪያ ሃላፊው።

ከወራት በፊት በአካባቢው ተመሳሳይ ግጭት ተፈጥሮ በስፍራው የመከላከያ ሰራዊትና የልዩ ሃይል አባላት እንዲሰፍሩ መደረጋቸው ይታወሳል።

በመሆኑም ግጭቱ ለሁለተኛ ጊዜ ሲከሰት በአጭሩ መቆጣጠር ባለመቻሉ ለአራት ቀናት ዘልቋል።

ለምን መቆጣጠር ተሳናችሁ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ካሳሁን “ችግር ፈጣሪዎቹ በሁለቱም ወገን (በኦሮሞና አማራ) ሽፋን እያደረጉ ያሉት ህዝቡን ነው። በመሆኑም ህዝቡ ላይ ከባድ ነገር እንዳይፈጠር ሲባል ችግርን በቀነሰ መልኩ ነው የመከላከያ ሰራዊት እየተቆጣጠረና እያረጋጋ ያለው” የሚሉት መምሪያ ሃላፊው በሌላ በኩል ደግሞ ችግሩ የተፈጠረው በተለያዩ አካባቢዎች በመሆኑ በወቅቱ የነበረው የመከላከያ ሰራዊት ቁጥር አነስተኛ ስለነበር በአጭር ጊዜ መቆጣጠር ሳይቻል ቀርቷል ብለዋል።

እስካሁን ችግር ፈጣሪ ከሚባሉትም ሆነ ተኩስ ከከፈቱት ቡድኖች በቁጥጥር ሥር የዋለ አለመኖሩን የሚናገሩት ኃላፊው “በሚመለከተው አካል ምርመራ ተጀምሯል፤ ችግሩን ለማወቅ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

በአካባቢው በተደጋጋሚ ችግር በመፈጠሩ “ህብረተሰቡ ስጋት ላይ ነው። መፍትሔ የምንላቸውን ሁሉ እናስቀምጣለን” ብለዋል የመምሪያ ኃላፊው አቶ ካሳሁን እምቢአለ።

ዛሬ ጠዋት ለአጣዬ ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ኃላፊ ስልክ ብንደውልም አሁን ያሉበት ሁኔታ መረጃ ለመስጠት የሚያስቸግራቸው መሆኑን ገልጸው “አሁን የተኩስ ልውውጡ የቆመ ቢሆንም ከተለያየ አካባቢ የሚሰባሰብ ኃይል ግን አሁንም ተኩሱ ወደ ሚካሄድባቸው አካባቢዎች አሁንም እየመጣ ነው” የሚል መረጃ ሰጥተውናል።

በተያያዘ ዜናም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን፣ ጂሌ ዱሙጋ ወረዳ በተቀሰቀሰ ግጭት የሶስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አሕመድ ሐሰን ለቢቢሲ እንዳስረዱት ግጭቱ የተቀሰቀሰው እግዝየ በተባለች ቀበሌ ነው።

የግጭቱ መነሻም አንድ ሠው በፀጥታ ኃይሎች ተገድሏል የሚል ወሬ ከተሰራጨ በኋላ ነው ብለዋል።

በአካባቢው የታጠቁ ግለሰቦች ከፀጥታ አካላት ጋር ተኩስ መግጠማቸውን የሚናገሩት አስተዳዳሪው በተኩስ ልውውጡ ሶስት ሰዎች ሲሞቱ የቆሰሉ እንዳሉም ተናግረዋል።


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV