በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ልብ መንቀሳቀስ አለመቻል የምርጫውን ስራ ከባድ እንደሚያደርገው ተጠቆመ

DW : የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ ትክክለኛነት፣በሃገር በቀል ሲቪል ማህበራት ሊዳኝ ይገባል ሲል አሳሰበ።ሀገራዊ ምርጫና የምርጫ ባለድርሻ አካላት ሚና ላይ አትኩሮ ዛሬ በአፍሪቃ ህብረት በተካሄደው ውይይት ላይ የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በቀድሞዎቹ ምርጫዎች እንደነበረው የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ግምገማ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው መጪው ምርጫ ግን በራሳችን ሲቪል ማህበራት ሊገመገም ይገባል ብለዋል።ለዚሁ ተግባርም የሲቪል ማህበራት ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።ይሁን እና የምርጫ ጉዳይ ተንታኝ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ምርጫውን እንዲታዘቡ የሚፈለጉ የሲቪል ማህበራት አቅም አናሳነት እና በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ልብ መንቀሳቀስ አለመቻል የምርጫውን ስራ ከባድ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል። በዚሁ ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።