ኢሕአዴግ አገር አቀፍ የፓርቲ ውህደት›› ለመተግበር መፍጨርጨር መጀመሩ ከንድፈ ሐሳቡ፣ ከመርሆቹና ከመስመሩ ጨርሶ መውጣቱን ያመለክታል

ኢሕአዴግ አሁን ባለበት የመካነ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አገር አቀፍ የፓርቲ ውህደት›› ለመተግበር መፍጨርጨር መጀመሩ ከንድፈ ሐሳቡ፣ ከመርሆቹና ከመስመሩ ጨርሶ መውጣቱን ያመለክታል

ሕወሓት የሌለበትን የኢሕአዴግ ውህደት እየመጣ ይሆን?

በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ የተካሄደው የኢሕአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ከፊል ገጽታ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መሪነት ደርግን ለመጣል ለ17 ዓመታት ከተደረገው ጦርነት ዘመን አንስቶ እስከዛሬ ድረስ በፖለቲካ አተያዩ እያተቀያየረ የመጣ ሲሆን፣ በርካታ አጥኚዎች በትግል ዘመን በሌኒናዊ ትንታኔ የሚመራ ማርክሳዊ ድርጅት፣ ሥልጣን በያዘበት ዘመን ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ድጋፎችን በመሻት የሊብራል አመለካከትን ቀጥሎ ደግሞ የሊብራሊዝምና ኒዮ ሊብራሊዝም አመለካከቶችን በጽኑ የሚተቸውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሲያራምድ እንደቆየ በተለያዩ ጽሑፎቻቸው ያመለክታሉ፡፡ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕይ እየተመራ የኢትዮጵያ ብልጽግና ለማረጋገጥ አርሶ አደሩን የትግል ስትራቴጂያዊ አጋር አድርጌ እታገላለሁ በማለት አራት ብሔራዊ ፓርቲዎችን በማቀፍ ግንባር ፈጥሮ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ አገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘው ኢሕአዴግ፣ በተደጋጋሚ በሕወሓት የበላይነት የሚመራና ለሌሎቹ ብሔራዊ ድርጅቶች እምብዛም ቦታ የሌለው ግንባር ነበር እየተባለ ይተቻል፡፡ በዚህ ሒደት በሁሉም የኢኮኖሚና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ላቅ ያለ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ በፖለቲካ ረገድ ፈቅ ማለት ያልቻለና ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓትና ለዴሞክራሲ ቦታ የሌለው ሥርዓት ተፈጥሯል በሚል ግንባሩ ክፉኛ ይተቻል፡፡

ይሁንና በፈተናዎች መካከል በሚፈጠሩ ድሎች ነው መለካት ያለብኝ የሚለው ኢሕአዴግ፣ እነዚህን ስኬቶችን ሲያጎላ ቢቆይም ከቆይታ በኋላ የፖለቲካ ጽንፈኞች በፈጠሩት ተቃውሞ አመራሮቹን ለመቀየር ተገዷል፡፡ በዚህም መሠረት በፓርቲው ሊቀመንበርና በአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው አዲሱ የፓርቲና የመንግሥት አስተዳደር በግንባሩ ሊያመጣው ከሚሠራባቸው ሥራዎች አንዱ፣ ለረዥም ጊዜ ሲንከባለል የመጣውና የግንባሩ ፓርቲዎች ውህደትና የአንድ አገራዊ ፓርቲ ምሥረታ ነው፡፡

ይኼ የፓርቲው ውህደት አስፈላጊነት ከሟቹ የቀድሞ የግንባሩ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአመራር ዘመን አንስቶ ሲታሰብበት የቆየ ነበር፡፡ ውህደቱ መቼ፣ እንዴትና በማን ይከወን የሚለው ግን ቁርጥ ሆኖ አልተነገረም ነበር፡፡ ሆኖም ኢሕአዴግ ወደ አንድ ፓርቲ ቢያድግ ሊያስገኛቸው የሚችላቸውን ድርጅታዊና አገራዊ ጥቅሞችን በመተንተን ውህደቱ የሚከወንበትን ሒደት በሚመለከት ጥናት እየተደረገ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይኼ ጥናት በተለይ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ በተደረገው የፓርቲው 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ ተነስቶ ጥናቱን የግንባሩ ምክር ቤት እንዲመራውና በቀጣዩ የግንባሩ ጉባዔ ላይ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት እንዲወሰን ከስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡

በግንባሩ አባል ፓርቲዎች መካከል የውህደቱ አስፈላጊነት ላይ ልዩነት ባይኖርም፣ ከውህደት አስቀድሞ መደረግ ስላለባቸው ጉዳዮችና ቅድመ ሁኔታዎች ላይ በተመሳሳይ ገጽ ላይ መገኘት ባለመቻላቸው ረዥም ጊዜ የወሰዱ ክርክሮች በአባል ፓርቲዎች መካከል ሲደረጉ እንደቆዩ በተደጋጋሚ ሲሰማ ቆይቷል፡፡

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ግንባሩን ወደ አንድ ውህድ አገራዊ ፓርቲ ማሸጋገር ምክንያታዊ ነው ብለው ያምኑ እንደነበር ከእርሳቸው ጋር ቆይታ ማድረጉን በመጥቀስ በቅርቡ ያስነበበው ዕውቁ ምሁርና የዓለም የሰላም ፋውንዴሽን ዳይሬክተሩ አሌክስ ዱዋል፣ ውህደቱ ግን አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶች ሁሉ ተደርገው በትክክለኛው ጊዜ መደረግ አለበት የሚል አቋም ነበራቸው ብሏል፡፡ ይኼ ትክክለኛ ጊዜ ደግሞ አገሪቱ በ2025 አሳካዋለሁ ብላ የምታቅደው የመካከለኛ ገቢ አገር መሆን ነው፡፡

ይሁንና በብሔር ማንነት ላይ በማተኮርና አገራዊ ማንነትን በመዘንጋት ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲደበዝዝ አድርጌያለሁ በማለት ራሱን የገመገመው ኢሕአዴግ፣ ግንባሩን ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ ማምጣት ላይ ትኩረት በማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡

ነገር ግን ይኼ አገር አቀፍ ፓርቲ ምን መልክና ርዕዮተ ዓለማዊ ወገንተኝነት እንደሚኖረው ያልተነገረ ሲሆን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ግን ሊከተል እንደማይቻል በግንባሩ አባል ድርጅቶች እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች ማሳያ ናቸው፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ መሆን የሚቻለው የቀድሞው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ወደ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የቀድሞው የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ወደ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ስማቸውን መቀየራቸው የሚጠቀስ ሲሆን፣ ግፋ ሲልም አዴፓ አዲስ ርዕዮተ ዓለም ለማልማት እንደሚሠራ ከአሁን ቀደም መጥቀሱ ሌላ ማሳያ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በግንባሩ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ የቀረበው የመወያያ ሰነድ አዲስ ርዕዮተ ዓለም ማልማትን ግብ አድርጎ ማስቀመጡ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚዋሃደው ኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለም እንደማይሆን ይጠቁማል፡፡

የግንባሩን ውህደት በተመለከተ ግን በግንባሩ ሊቀመንበር ከሚሰጡ አስተያየቶች በዘለለ አባል ፓርቲዎችም ሆነ አጋር ፓርቲዎች በተናጠል ሐሳባቸውን ይፋ ሲያደርጉ ባይደመጥም፣ የግንባሩ ቀደምት ፓርቲና የ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግል መሪ የነበረው ሕወሓት ግንባሩን በፍጥነት ወደ ውህደት መምራት ኢሕአዴግን ወደ ሞት የሚሸኘው እንደሆነ በማስጠንቀቅ፣ ይኼ የሚሆን ከሆነ ግን ከሌሎች ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ግንባር እንደሚፈጥር በመግለጽ የውህድ ፓርቲው አካል እንደማይሆን በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም. በታተመው የፓርቲው ልሳን ወይን መጽሔት ሐተታ አቅርቧል፡፡

የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በመገምገም ‹‹ታሪክ ራሱን ይደግማል›› እንደሚለው ‹‹የህዳሴ መዋዕል ተገትቶ፣ ደግሞ ወደ ተሻገርነው አሳፋሪ የአዙሪት መንገድ እየተመለስን እንገኛለን›› በማለት የሚተነትነውና ‹‹በኢትዮጵያ አገር አቀፍ የተዋሃደ ፓርቲ ጥያቄ ለምን›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ሰነድ፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በኢሕአዴግ ድርጅት ውስጥ ባቆጠቆጡ ጥገኞች ማን አልበኝነት መፈራረስ መጀመሩ የሚታይና ተጨባጭ ሐቅ ነው፡፡ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር የሚመነጩ የድርጅቱ ጽኑ እምነቶችና መመርያዎች በጠራራ ፀሐይ ተቀምተው በጥገኛው የመበስበስ ኃይል አስተሳሰብና ፕሮግራም እየተተኩ ይገኛሉ፡፡ በአጭሩ ኢሕአዴግ ቀብር ብቻ ይቀረዋል ካልተባለ በስተቀር የሞተ ድርጅት ሆኗል ቢባል ነባራዊ ሁኔታው ይገልጸዋል፤›› ሲል ይደመድማል፡፡

ስለዚህም፣ ‹‹ኢሕአዴግ አሁን ባለበት የመካነ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አገር አቀፍ የፓርቲ ውህደት›› ለመተግበር መፍጨርጨር መጀመሩ ከንድፈ ሐሳቡ፣  ከመርሆቹና ከመስመሩ ጨርሶ መውጣቱን ያመለክታል፡፡ ኢሕአዴግን በአቋራጭ አንድ ፓርቲ ለማድረግ የሚፈልገው ኃይል ዓላማውና ህልሙ ኢሕአዴግን ማጠናከር ሳይሆን ጨርሶ በማፍረስ ግብዓተ መሬቱን በመፈጸም አብዮታዊ ዴሞክራሲና መሪ ድርጅቱን የማጥፋት ተልዕኮ ያነገበ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እየሰመረለት ይገኛል፤›› በማለትም የተዋሃደ ፓርቲ የመፍጠር ሒደቱን ልክ አለመሆኑን ይተቻል፡፡

ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥርዓትን በመፍጠር አገሪቱን ሲያስተዳድርበት የቆየው አደረጃጀት ‹‹በሁሉም ገጽታው ተገቢና ምክንያታዊ ነበር፤›› በማለት የሚከራከረው ይኸው ሰነድ፣ ‹‹በኢሕአዴግ ውስጥ እየተነሳ ያለው ከግንባር ወደ ውህድ ፓርቲ የመሸጋገር ጉዳይ በመርህ ደረጃ መጠናት ያለበትና የጥናቱ ውጤት ቀርቦ ውይይት ማድረግ ተገቢ ቢሆንም፣ በደምሳሳው አንድ ውህድ አገር አቀፍ ፓርቲ አያስፈልግም ባንልም ከተጨባጭና ወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ ውህደት ምን ማለት ነው? ከምን ይነሳል? በየትኛው እምነትና አመለካከት የሚመራ ውህደትና ለውህደት የሚያስፈልጉ እምነቶችና መለያዎች የትኞቹ ናቸው? በዚህ ረገድ ያሉ የአብዮቶች ተሞክሮ፣ የራሱ የኢሕአዴግ ተሞክሮ በብቃትና በንቃት መታየት አለባቸው፤›› ሲል ያሳስባል፡፡

ይኼ የሰነዱ አቋምና ገለጻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጋር የሚመሳሰል መልዕክት ያለው ሲሆን፣ ውህደቱን በተመለከተ የተደረገው ጥናት ውይይቶች እየተደረጉበት እንደሆነ በማስታወቅ፣ ‹‹የውህደቱ ጉዳይ እንዴት ይሁን? መቼ ይሁን? በምን አግባብ ይሁን? የሚሉ ጥያቄዎችን ከማንሳት ውጪ በሁሉም ፓርቲዎች ውህደት አያስፈልግም የሚል አቋም አልተንፀባረቀም፤›› በማለት አብራርተው ነበር፡፡  መቅደም ያለባቸው ሥራዎች ስላሉ እነርሱ ይቅደሙ የሚሉ አሉ እንጂ ውህደቱ አያስፈልግም የሚሉ እንደሌሉም ገልጸው ነበር፡፡ ሆኖም የፓርቲው ውህደት የጥቂት ግለሰቦች ወይም ፓርቲዎች ሐሳብና ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ፓርቲዎች ሐሳብና ፍላጎት መሆን ስላለበት ጥልቅ ውይይቶችን እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል፡፡

የውህደትን አስፈላጊነት በተመለከተ በአባል ፓርቲዎች መካከል የተለየ አቋም እንደሌለ የግንባሩ ሊቀመንበር ቢያስታውቁም፣ አካሄዱ ኢሕአዴግን የመግደል ነው በማለት ተንትኖ፣ ‹‹እየተቀበረ ያለውን ኢሕአዴግ አልቅሰን እንሸኘው ወይስ ሙሉና የተጨበጠ አማራጫችንን ይዘን ቀርበን ትግላችንን እናጋግል፤›› የሚሉ አማራጮች ከፊቱ እንደተደቀኑ በመግለጽ የሕወሓት ልሳን ወይን ያትታል፡፡

ሰነዱ ትግሉን በተመለከተ ሊኖረው ስለሚችል አማራጭ ሲያስቀምጥ፣ ‹‹ኢሕአዴግን ላዋህድ የሚለው ኃይል ባስቀመጥነው አቅጣጫ ብንዋጋው የተወሰነ ጊዜ ቢሰጠን እንጂ የያዘውን መደብ ይተገብራል፤›› በማለት፣ ‹‹ይኼ ከሆነ እኛ ወደ ውህዱ ፓርቲ ልንገባ አንችልም፤›› ሲል ይደመድማል፡፡ ምክንያቱም ድርጊቱ ‹‹ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ለሕዝቦች በተለይ ደግሞ ለትግራይ ሕዝብ ትግል ትልቅ ክህደት ስለሚሆን ነው፤›› ይላል፡፡

ስለዚህም እንደ ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥታዊ ግንባር›› አልያም ‹‹የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ግንባር›› ዓይነት አማራጭ ግንባሮችን ይዞ መቆም ይገባል በማለት ሰነዱ ያስቀምጣል፡፡ ለዚህም የተጀመረውን ሥራ በበለጠ የማፋጠን አስፈላጊነት ያሰምርበታል፡፡

የኢሕአዴግ ውህደት ይሠራ ዘንድ የሚያዋህድ ፕሮግራም፣ ሥልትና ስትራቴጂ፣ የተዋሃጆቹ ታሪካዊ አመጣጥና የሚያዋህዳቸውን ጉዳይ የሚያትት ሕገ ደንብና አሠራሮች እንዲሁም አደረጃጀቶች በግልጽ ማዘጋጀት፣ ለውህደቱ የሚያመች ሰፊ የፖለቲካና የሥነ ሐሳብ መደላድል መፍጠር እንዲሁም የውህደቱን ‹‹ኮር›› አመራር መፍጠር፣ መሰባሰብና መገንባት ያሻል ይላል ሰነዱ፡፡

ከዚህ ውጪም ኢሕአዴግን በፍጥነት ማዋሃድ የሚፈጥሯቸው ሥጋቶችን ይጠቁማል፡፡ ከእነዚህም አንዱ የብሔር ማንነታችን በመጨፍለቅ በአንድ ፓርቲ ስም ሁሉንም ዘርፎችና አካባቢዎች በበላይነት በመቆጣጠር ፀረ ዴሞክራሲያዊነትንና የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት ሊያስከትል ይችላል በማለትም ያስቀምጣል፡፡ ይኼ እንዳይሆን ግን የኢሕአዴግ ችግር የአደረጃጀት ሳይሆን የአስተሳሰብ ነውና ያመመው ቦታ ላይ ይታከም በማለት ይከራከራል ሰነዱ፡፡

ይኼንን ጉዳይ በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞችና ተመልካቾች፣ ሕወሓት ከአሁን ቀደም በግንባሩ ውስጥ የነበረውን የበላይነት በማጣቱና ፓርቲው የሚዋሃድ ከሆነም ይኼ የበላይነት ይበልጡኑ በመጥፋት በግንባሩ የነበረው የባለቤትነት አስተሳሰብ ይከስማል ይላሉ፡፡ ይኼ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በኋላ የታየ እውነት ነው የሚሉት አስታያየት ሰጪዎች፣ ውህደቱ ሕወሓት የነበረውን የበላይነት ጭምር የሚያሳጣ ነው በማለት ያስቀምጣሉ፡፡

ከአሁን ቀደም በ1985 ዓ.ም. በተፈጠረ ውህደት 16 ፓርቲዎች ተሰባስበው የፈጠሩት የቀድሞውም የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ደኢሕዴግ)፣ የአሁኑን ደኢሕዴን የፈጠሩት ውህደት በመፈጸም እንደሆነ በመጥቀስ የሚከራከሩ አስተያየት ሰጪዎች፣ ኢሕአዴግ ከዚህ ልምድ መውሰድ ይችላል ይላሉ፡፡ የሚታገሉበት አመለካከትና አስተሳሰብ ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ ለውህደት ርዕዩ ዓለምንና ሕገ ደንብን ምክንያት ማድረግ ሌሎቹን ፓርቲዎች አለማመን ነው እንጂ ሌላ ምክንያት አይታይም በማለት፣ ከ28 ዓመታት በኋላ መዋሃድ እንደውም ቀላል መሆን ነበረበት ይላሉ፡