" /> በሕገ ወጥ መንገድ ባሕር ተሻግረው ለመሄድ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል። | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

በሕገ ወጥ መንገድ ባሕር ተሻግረው ለመሄድ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል።

በአገር ውስጥ ያለው መፈናቀል ሕገ ወጥ ስደትን አባብሷል?

BBC Amharic : በሕገ ወጥ መንገድ ባሕር ተሻግረው ለመሄድ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል። በተለያየ ጊዜ ባህር ለመሻገር ሲሞክሩ ሕይወታቸው የሚያልፉ ዜጎችን ዜና መስማት የተለመደ ሆኗል።

ከሳምንታት በፊትም ከትግራይ ክልል ኢሮብ ወረዳ ከሊቢያ ተነስተው ሜዲትራንያንን ሲያቋርጡ የነበሩ 15 ወጣቶች ሕይወታቸው ማለፉንም ሰምተናል።

በአማራ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሰው ኃይል ጥናትና የሥራ ስምሪት አገልግሎት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ጌታሰው መንጌ፤ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጋላጭ ከሆኑ ክልሎች አንዱ የአማራ ክልል መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በየመን

የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር በድብቅ የሚፈፀም በመሆኑ ቁጥራቸው ይህን ያህል ነው ብሎ ማስቀመጥ ባይቻልም ሊሻገሩ ሲሉ በድንበር አካባቢ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ግን መጥቀስ እንደሚቻል ያስረዳሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ዓመት ብቻ በሰመራ በኩል ወደ ጂቡቲ ሲሄዱ 545 ሰዎች ተይዘው ወደ አካባቢያቸው ተመልሰዋል።

በመተማ መስመርም የስደተኛ ማቆያ ማዕከል ስላለ በየጊዜው በርካቶች ተይዘው ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱ ይናገራሉ።

“በአብዛኛው ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበትን የመተማን መንገድ ለመሸሽ የአብርሃጂራን መንገድ ይመርጡታል” የሚሉት ኃላፊው በዚህ ዓመትም 290 የሚሆኑ ሕገ ወጥ ስደተኞች ድንበር አካባቢ ተይዘው ወደ አካባቢያቸው መመለሳቸውን ያስታውሳሉ።

እነዚህ ስደተኞች ከአማራ ክልል ብቻ ሳይሆኑ ከደቡብ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአዲስ አበባ እና ሶማሌ ክልል የመጡ መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ አክለዋል።

ስደተኞቹ በአብዛኛው ሴቶች ሲሆኑ 40 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ህፃናት ናቸው።

እንደ ዳይሬክተሩ ከሆነ በክልሉ ካሉ አካባቢዎች በአብዛኛው የሚሰደዱት ከምሥራቁ የአማራ ክፍል [ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ የኦሮሚያ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ] ነው። ይሁን እንጂ “ከሌሎች አካባቢዎች የሉም ማለት አይደለም” ብለዋል።

የፓስፖርት ክልከላን ጨምሮ ሕገ ወጥ ስደትን ለመቀነስ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም አሁንም በሥራ አጥነት እና በአገር ውስጥ ባለው መፈናቀል ምክንያት ቁጥሩ እየጨመረ እንደመጣ ዳይሬክተሩ ያብራራሉ።

“በሕጋዊ መንገድ የሥራ ስምሪት ለማድረግ፤ ያውም በቂ ቅስቀሳ ሳይደረግ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ተመዝግበዋል። ይህም ዜጎች ሕጋዊ በሆነ መንገድ የመሄድ ፍላጎት እንዳላቸው ያየንበት ነው” ሲሉ፤ ይህ ባይሆን ኖር ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሰው በሕገ ወጥ መንገድ ሊሄድ ይችል እንደነበር ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

እስካሁን ከአማራ ክልል በሕገወጥ መንገድ ሄደው ሕይወታቸው ያለፉ ስደተኞች ምን ያህል እንደሆኑ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸውም አክለዋል።

በትግራይ የደቡብ [ራያ] እና ምሥራቅ ዞኖች [አዲግራት፣ ውቅሮ፣ ኢሮብ… ] በሕገ ወጥ ስደት በስፋት የተጠቁ ዞኖች መሆናቸው ከክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊና ጉዳይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የትግራይ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ክትትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ገ/ሕይወት እንዳሉት አብዛኞቹ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ስደት የሚያቀኑት ወጣቶች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከልም የሴቶቹ ቁጥር ከፍ ያለ ነው።

እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ በኦሮሚያ ክልልም አብዛኛው ለዚህ ሕገ ወጥ ጉዞ ተጋላጭ የሆኑት ታዳጊዎችና ወጣቶች ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ጠይቡ፤ ከክልሉ ለሕገ ወጥ ስደት የሚዳረጉት እድሜያቸው ከ12 ዓመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎች መሆናቸውን ይናገራሉ – በቅርቡ ወደ አረብ አገራት ሲሰደዱ ተይዘው ከተመለሱት መካከልም ስልሳዎቹ ህፃናት መሆናቸውን በመጥቀስ።

አቶ መሐመድ እንደሚሉት በክልሉ በአብዛኛው የሚሰደዱት ከስድስት ዋና ዋና ዞኖች ሲሆን እነሱም ጅማ፣ ባሌ፣ አርሲ እና የምዕራብ አርሲ ዞኖችን በዋነኛነት ይጠቅሳሉ።

“በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሌሎች አገራት የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ይሄ ነው ተብሎ ባይታወቅም ቁጥሩ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው” ብለዋል- አቶ መሐመድ።

መውጫ በሮች…

ከትግራይ ክልል በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ባህር ማዶ ለመሻገር የሚሞክሩት የሚጠቀሙበት የአፋር-ጅቡቲ መስመር አንዱ ሲሆን፤ ወደ አውሮፓ ለመሄድ ያሰቡ ደግሞ በሁመራ-ሊቢያ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋን እንደ አማራጭ በመጠቀም ወደ ሳዑዲ አረቢያና የመን እንደሚያቀኑ አቶ ሰለሞን ይናገራሉ።

አቶ ጌታሰውም ከአማራ ክልል በሕገ ወጥ መልኩ ሰዎች ከሚሰደዱባቸው መስመሮች መካከል ሦስት መውጫ በሮችን በዋናነት ይጠቀሳሉ።

አንደኛው በጅቡቲ አድርጎ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚያደርስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመተማ በኩል ሱዳን – ሊቢያ ከዚያም ወደ አውሮጳና ሳዑዲ አረቢያ ጉዞ የሚደረግበት ነው፤ በዚህ ድንበር ከፍተኛ ቁጥጥር ስለሚደረግ ሕገ ወጥ ስደተኞች እምብዛም አይደፍሩትም።

ሌላኛው አዲስ የተከፈተው የአብርሃጂራ መንገድ ነው።

አቶ መሐመድ በበኩላቸው ከኦሮሚያ ክልል የሚሰደዱትም ሁለት ዋና ዋና መንገዶችን እንደሚጠቀሙ ያስረዳሉ።

አንደኛው በአማራ ክልል በኩል በማቋረጥ በመተማ አድርገው ወደ ሱዳን እስከ ሊቢያ የሚደረግ ጉዞ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በጅቡቲ በኩል ወደ የመንና ሌሎች የአረብ አገራት ለመጓዝ ጥቅም ላይ የሚውለው መንገድ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በሕገ ወጥ መንገድ ኬንያንና ታንዛኒያን አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረግ የስደት ጉዞ እንዳለም አቶ መሐመድ ገልፀዋል።

የአፍሪካ የስደተኞች መውጫ መንገዶች
የአፍሪካ የስደተኞች መውጫ መንገዶች

ለምን ይሰደዳሉ?

ዜጎች በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱባቸው ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው የሚሉት አቶ ጌታሰው በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገር ውስጥ ያለው መፈናቀል ቁጥሩን እንዳባባሰው ይናገራሉ። ሥራ አጥነትም ሌላው ዐብይ ምክንያት ነው።

ዜጎች ተምረው፤ ተመርቀው ሥራ የሚያጡበት ሁኔታ በመኖሩና በሥራ ፈጠራ ዘርፍ ላይ አመርቂ ሥራ ባለመሰራቱ ዜጎች ስደትን እንደ አማራጭ ይወስዱታል ብለዋል።

ትምህርታቸውን በተለያየ ምክንያት ያቋረጡና አማራጭ የለንም ብሎ የሚያስቡ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን የሚሸሹ፣ የሕገ ወጥ ደላሎች አቅጣጫና ስልቱን የለወጠ ቅስቀሳም ሰበብ ናቸው።

“ችግሩን ለመፍታት የውጭ አገር ሕጋዊ የሥራ ስምሪትን ጨምሮ የተለያዩ መፍትሄዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ” የሚሉት ዳይሬክተሩ ሕብረተሰቡ ችግሩን እንዲገነዘብ እየሰሩ ቢሆንም ይህን ለማድረግ የሚመደበው በጀት አነስተኛ በመሆኑ በርካቶችን መድረስ አለመቻሉን ይናገራሉ።

አቶ ሰለሞን ገ/ሕይወት በበኩላቸው ‘የተሳሳተ’ ብለው በሚገልጹት ወጣቶቹ በሚሄዱባቸው የውጭ አገራት የተሻለ ነገር ይገኛል በሚል እምነት፣ በአቻና ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ግፊት ከአገር ለመውጣት የሚገደዱባቸው ምክንያቶች እንደሆኑ ያስቀምጣሉ።

“ሁሉም ትምህርት የጨረሰ፤ ተመርቆ ሥራ ይቀጠራል ማለት አይደለም። ሥራ አጥነት፣ ማጉላላትና አስፈላጊውን አገልግሎት አለመስጠት የለብም አንልም። በተቻለ መጠን ግን በአገራቸው ሰርተው የሚቀየሩበት እድል አለ” በማለት አብዛኛዎቹ በሕገ ወጥ መንገድ ለመሄድ ሲሉ የሚይዟቸው ሰዎች ማንነት በሚጣራበት ጊዜ መኪና እና ቤት ያላቸው መሆናቸውን ያስረዳሉ።

“የሚጠቀሙት መንገድ የተወሳሰበ ሲሆን ሰፊ ኔትዎርክ አላቸው። ይህ ትልቁ ችግራችን ነው። ሲያዙም የሚገጥማቸው ቅጣት አስተማሪ አይደለም፤ አንዳንዶቹ በዋስ ሁሉ ይፈታሉ። የፍትህ አካላት አስተማሪ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ግን ሥራው ራሱ ያሳየናል” ሲሉ ለሕገወጥ ስደት ትልቁ ችግር የሕገወጥ ደላሎች ጉዳይ እንደሆነ ያሰምሩበታል።

በዚህም ምክንያት በየጊዜው ከክልሉ የሚወጡ፣ አደጋ የሚደርስባቸውና የሚሞቱ ስደተኞች በውል ማወቅ እንደማይቻል በመግለጽ ቁጥሩ የማይናቅ ወጣት ግን ከአገር ለመውጣት ሕጋዊ ያልሆኑ መንገዶች እንደሚጠቀም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊም የተለየ ሃሳብ የላቸውም። ለሕገወጥ ስደቱ እንደ ምክንያት የሚያነሱት ሥራ አጥነትን ሲሆን ሌሎች ደግሞ የተሻለ ሕይወትንና ሐብትን ፍለጋ አልመው የሚሄዱ እንዳሉም ተናግረዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በሕገ ወጥ መንገድ የሚጓዙት ዜጎች በባህር ሰጥመው ሕይወታቸው ሲያልፍ በመንገድ ላይ የተለያየ ችግር ሲገጥማቸው ሪፖርት እንደሚደርሳቸውም ኃላፊው አክለዋል።

ለችግሩ እልባት ለመስጠት ምን እየተሰራ ነው?

በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ 50 ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞችን ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለመላክ እቅድ እንደተያዘ አስታውቀው ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን ወደ ኤዥያና አውሮፓ ሃገራትም የሠለጠነ የሰው ኃይል በሕጋዊ መንገድ ለመላክ እንደታሰበ መናገራቸው ይታወሳል።

ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሥራ ስምሪት መጀመሩንና ወደ እስያና አውሮፓም የሠለጠነ የሰው ኃይል ለመላክ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ዳይሬክተር ብርሃኑ አበራ ለቢቢሲ ገለፀዋል።

ይህንኑ አስመልክተን የጠየቅናቸው አቶ ጌታሰው ከአማራ ክልል ምን ያህል ሥራ ፈላጊዎች በዚህ ስምሪት ውስጥ እንደሚሳተፉ ለጊዜው ባያውቁም ለዚህ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በክልሉ ካሉ 125 የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ኤጀንሲዎችም ብዙዎቹ የሥራ ውል እያፀደቁ ነው።

እስካሁን በአንድ ኤጀንሲ አማካኝነት ከ16 በላይ ሴቶች ወደ ሳዑዲ በቤት ሠራተኝነት በሕጋዊ መልኩ መላካቸውን ያስታውሳሉ።

በክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ መዋቅር 20 ሺህ ሰዎች ተመዝግበው 10 ሺህ 434 ሰዎችን አሰልጥነው ማጠናቀቃቸውን ይናገራሉ።

20 ሺህ ሰዎችን ለማሰልጠን በመንግሥት የተመረጡ የሥልጠና ማዕከላት ከአንድና ሁለት በላይ የሙያ ዘርፍ ሥልጠና የመስጠት አቅም ስለሌላቸው የግል ማዕከላትን አካቶ በ48 የሥልጠና ማዕከላት ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

በመሥሪያ ቤቱ ባሉት መዋቅሮች ፍላጎት ያላቸውን ሥራ ፈላጊዎች አዋጁ በሚፈቅደው መሠረት ምዝገባ ማካሄዳቸውን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ዳይሬክተሩ እንደገለፁልን የሥራ ዘርፎቹ፤ የቤት ውስጥ ሠራተኝነት፣ የቤት ውስጥ ሥራና የቤት አያያዝ፣ ሹፌር፣ ነርስ ሲሆን ተፈላጊ ብቃቱ እንደ ሥራ ሁኔታው ቢለያይም ለቤት ውስጥ ሠራተኛነት ቢያንስ ስምንተኛ ክፍል ያጠናቀቁ፣ በሰለጠኑበት ዘርፍ የሙያ ብቃት ወስደው ያለፉ፣ የጤና ምርመራና አሻራ ጨርሰው እንዲሄዱ ይደረጋል ብለዋል።

በነርስነት ሙያ አሰሪዎችና በተቀባይ አገራት ያለው ፍላጎት በሚያቀርቡት መሠረት እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

ስደትን ጠቅልሎ ማስቆም እንደማይቻል የሚናገሩት አቶ ሰለሞንም ቢያንስ በሕጋዊ መንገድ ወደ ‘ሚፈልጉት አገር ሄደው በክህሎት እና በብቃት ሠርተው ተጠቃሚ የሚሆኑበት አማራጭ መኖሩን መገንዘብ አለባቸው ባይ ናቸው።

መንግሥት ስምምነት ከደረሰባቸው አገራት ጋር ሠራተኞችን በሕጋዊ መንገድ አሰልጥኖ መላክ የሚያስችለው አሰራር በመተግበሩ በአሁኑ ሰዓት በቤት አያያዝ፣ ህጻናት እንክብካቤ እና በሾፌርነት በመንግሥት እና በግል ተቋማት ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን አቶ ሰለሞን ይጠቅሳሉ።

አቶ መሐመድ እንደሚሉት ይህንን ሕገ ወጥ ስደትን ለመቀነስ እና ዜጎችም በሕጋዊ መንገድ ሰርተው ለራሳቸውና ለአገሪቱ እንዲተርፉ ለማድረግ መንግሥት አዲስ ሕግ በሥራ ላይ እያዋለ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን የሚያዘዋውሩ ደላሎች ላይ እርምጃ መውሰድን ለማጠናከርና ለማህበረሰቡ የግንዛቤ መስጫ ሥራዎችን በስፋት ለመስራት መታሰቡን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሚክስድ ማይግሬሽን ሴንተር የተባለ የመረጃና የጥናት ተቋም በድረ ገጹ ላይ በ2019 ሁለተኛው ሩብ ዓመት ባወጣው ሪፖርት ከሦስት ወራት በፊት ወደ ጎረቤት አገር ሶማሊያ የሚገቡና የሚወጡ ስደተኞች ቁጥር [የመን፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያና ጂቡቲ] በ41 በመቶ ጨምሯል።

ከአምስት ወራት በፊት ደግሞ ወደ 19 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያንና ሶማሊያዊያን የመን መግባታቸውን ሪፖርቱ ገልጿል። በግንቦት ወር መጨረሻ የመን የገቡ ስደተኞች ቁጥርም 74 ሺህ በላይ እንደሆነ አመልክቷል።

በሪፖርቱ እንደተገለፀው በሚያዚያ ወር በትንሹ 40 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በየመን የባህር ዳርቻ ላይ ሕይወታቸው ሲያልፍ ይህ መንገድ በተለይ ከምሥራቅ አፍሪካ የሚመጡ ስደተኞች የመን ለመድረስ የሚጠቀሙበትና እጅግ አደገኛው ነው።

አብዛኞቹ ስደተኞች በሊቢያ ተይዘው እስር ቤቶች ስለሚገቡ የሜደትራኒያንን ባህር አቋርጠው የአውሮፓን ምድር የሚረግጡት ስደተኞች ቁጥር ቀንሷል። በዘንድሮው ዓመት ከምሥራቅ አፍሪካ ወደ አውሮፓ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ከ50 የሚያንስ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

ከተጠቀሱት ክልሎች ውጪ ባሉ የሃገሪቱ አካባቢዎችና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ስላለው በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረገውን ስደት በተመለከተ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።


የመረጃ ቲቪ አባል ይሁኑ - JOIN US