ግልጽ መልእክት ለጠ/ሚ አብይ አህመድ – ከኦሮሞ ጽንፈኞች ተፋተው ከሕዝብ ጋር ይወግኑ #ግርማካሳ

መረጃ ቲቪን ሰብስክራይብ በማድረግ ወቅታዊ ዜናዎችን፣ ትንተናዎችን፣ የኪነጥበብ ፕሮግራሞችን እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ማግኘት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

ጠ/ሚ አብይ አህመድ፣ «መደመር ውጤት እንደሚያመጣ ያየንበት ተጨባጭ ማስረጃ ነው። ተደምረን ይሄን አሳክተናል። ተደምረን ብዙ ጉዳይ እናሳካለን። በተደጋጋሚ እንዳልነው የሚጮሁ ድምጾች አሉ። እነሱ አቧራዎች ናቸው። እኛ አሻራ ለማሳረፍ ፣ ታሪክ ለመስራት በጋራ ከቆመን ኢትዮጵያ ለሁላችን የምትበቃ ፣ ሁላችን የምታኮራ ሃገር ስለሆነች ይህንን በማድረግ ኢትዮጵያውያን ዳግም አዳዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ይችላሉ ፤ ያደርጋሉም የሚል እምነት አለኝ» ሲሉ የችግኝ ተከላዉን ዘመቻ መሳካቱን ገልጸዋል።

Deforestation በአገራችን ሳይሆን በአለም ደረጃ ትልቅ ችግር እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ቀደም ሲል የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ችግሩን ተረድተው የችግኝ ተከላ ዘመቻ ያደረጉበት ጊዜም ነበር። ጠ/ሚኒትር አብይ አህመድም በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያዉያንን በዚህ አንገብጋቢ አጀንዳ ዙሪያ ማንቀሳቀሳቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባል።

ሆኖም ግን የችግኝ ተከላ ካለው አገራዊ ፋይዳ ባሻገር፣ ችግኝን ለፖለቲካ ፍጆታና ለፕሮፖጋንዳ መጠቀሙ፣ ችግኝን ፖለቲሳይዝ ማድረጉ ግን አሳዛኝ ነው። በአገሪቷ ዜጎች በጅምላ ሲታሰሩ፣ የሰብአዊ መብቶች ሲረገጡ፣ ዜጎች በግፍና በጭካኔ ሲፈናቀሉ፣ በሕወሃት ጊዜ ወደ ነበረበው ስንመለስ … ዝምታን የመረጡና ለስብእና ደንታ የሌላቸው፣ አሁን የአገር ችግር ችግኝ ብቻ የሆነ ይመስል፣ ከሰው ልጅ ችግኝ በልጦባቸው፣ ችግኝ ሲተክሉ የሚያሳይ ፎቶ ለመለጠፍ ሲሽቀዳደሙ ማየታችን፣ ምን ያህል መርህ የመከተል ችግር እንዳለብን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

ይሄን ብዬ ጠ/ሚአብይ በተናገሩት ላይ ፣ የሚከተለውን ምላሽ እንድሰጥ ይፈቀድልኝ

———-
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር ሆይ፣

– የርስዎ አገዛዝ ዜጎችን በጅምላ እያሰረ ፣
– የርስዎ ድርጅት ዘረኛና አፓርታይዳዊ የኬኛ ፖለቲካን እያራመደ፣
– የርስዎ ድርጅት አባላትና መሪዎች በየቦታው ዜጎችን መጤ እያሉ እያፈናቀሉና ከቅያቸው እየነቀሉ፣
– የርስዎ ጓደኞችና እርስዎ እራስዎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በአደባባይ እየዛቱ፣
– በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ድጋፍ ሰጥትዎት የነበረ ቢሆንም፣ እርስዎና ድርጅትዎ ኢትዮጵያዊነትን በአፍ ብቻ በመስበክ፣ በተግባር ግን ጽንፈኞች ህዝብንና አገርን እንዲያሸበሩ እየፈቀዱ፣
– ሜጫና ገጀራ ይዘው የሚያስፈራሩትን ፣ በአደባባይ በይፋ አመጽና ረብሻ የሚቀስቅሱትን፣ ባንክ የሚዘርፉትን እየታገሱና እንክባካቤ እያደረጉ፣ ብእር አንሰተው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለፍትህና ለእኩልነት የሚታገሉትን፣ እንደ ባላደራው አመራሮችን መታገስ ተስንዎት፣
– ባላደራው ስብሰባዎች እንዳያደርግና ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ እያደረጉ፣
– እርስዎን ከሚያመሰግኑ ቡድኖችና ድርጅቶች በቀር ሌሎች በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ እያከላከሉ፣

በአጭሩ በአገሪቷ ከሕወሃት ያልተሻለ እንደውም በአንዳንድ መስፈርቶች የባሰ ድባብ ፈጥረው፣ እንዴት ነው አሁንም ስለ መደመር የሚያወሩት ????????? እረ ትንሽ እንኳን ይፈሩ …

ከአንድ አመት በፊት በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የርስዎን የመደመር፣ የፍቅር የአንድነት መልእክቶች ተቀብለው ተደምረው ነበር። ያልተደመሩ የነበሩት የርስዎ ድርጅት ጽንፈኛ አባላቶች፣ እንደ ኦነግ፣ ጃዋራዊያን ያሉ ቡድኖችና ህወሃቶች ነበሩ። እነርሱ ከጅምሩ እርስዎ እንዳይሳካልዎት ሲሰሩ ነበር። በሰኔ 16 ሊገድልዎትም አስበው የነበሩ እነዚህ ቡድኖች ነበሩ። ያኔ በርስዎ ቦታ ደረቱን ሰጥቶ የሞተልዎትን አዲስ አበቤዎች ነበሩ። እርስዎ ግን በአስር ሚሊዮን የደገፍዎትን ህዝብ ወደ ጎን ገፍተው ፣ አገራችን የጽንፈኞች መፈንጫ እንድትሆን አደርጓት። እርስዎ ግን የአዲስ አበባን ወጣት በጅምላ ከወር በላይ በግፍና በጭካኔ እንዲታሰር አደረጉ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር፣

ይሄን ስጽፍ ከጥላቻ የተነሳ አይደለም። ከትልቅ ሃዘን የተነሳ ነው። ከአንድ አመት በፊት የነበረውንና አሁን ያለውን ሁኔታ ሳስበው ውስጤ በጣም ያዝናል። አንዳንዴ “እኝህ ሰው የለየላቸው ከሃዲ ናቸው” እላለሁ። ደግሞ መለስ እልና፣ “ያሉበት ሁኔታ ከባድ ስለሆነ ነው፣ አብረዋቸው ያሉ አላሰራ ብለዋቸው ነው እላለሁ”። በነዚህ በሁለት ሐሳቦች መካከል ይኸው እየዋዠኩ አለሁ።

አሁንም ክብር ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ ወጥተው በአደባባይ የሚናገሩትን፣ ምን አልባት ከጭፍን ደጋፊዎችዎትና አገር ቤት ካሉ የመንግስት ሰራተኞችና የድርጅትዎ አባላት ውጭ የሚሰማዎት እንደማይኖር ምን ያህል እንደሚገነዘቡ አላውቅም። የችግኝ ፖለቲካ የቀናት ፖለቲካ ነው። የሕዝብን መሰረታዉ የመብት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት ጥያቄ መመለስ ካልቻሉ፣ ከሕዝብ ጋር መልሰው ካልተስማሙ፣ በሕዝብ አሁን ካለው ደረጃ በባሰ እየተተፉ ነው የሚመጡት። ያ ደግሞ የርስዎና የድርጅትዎን አወዳደቅ በጣም የከፋ ነው የሚያደረገው።

ምን አልባት የኔን የአንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ምክር የሚሰሙ ከሆነ ፣ ጥቂት ሐሳቦች እንዳካፍልዎት ይፍቀዱልኝ።

ይሄ ሕዝብ ጠልቶኛል ብለው ተስፋ መቁረጥ የለብዎትም። በተወሰነ መልኩ በርስዎ አመራር ያዘኑና የተበሳጩ ብዙ ቢሆኑም በችግኝ ተከላው ዘመቻ፣ የርስዎን ጥሪ ሰምቶ የወጣውን ሕዝብ በማየት ህዝቡ ዘንድ ትንሽም ቢሆን በርስዎ ላይ የተስፋ እንጥብጣቢ እንዳለው አመላካች ነው። ህዝቡ አሁንም ወደ ቀናው መንገድ ከመጡ፣ ቀና አመራር ከሰጡ፣ ያኔ ሲሰጥዎት የነበረውን ድጋፍ መልሶ ሊቸርዎት ይችላል። ህዝብ ቂመኛ አይደለም።

ሆኖም ግን በእጅጉ ላሰምረበት የሚገባው ነገር አለ። የኢትዮጵያ ሕዝብ አጭበርባሪ፣ አፈ ጮማ የሆነ ሰው አይፈልግም። አንዴ በንግግር ተማርኮ ድጋፍ ሰጥቷል። ከዚህ በኋላ በንግግር አይማረክም።

እባክዎትን

– ከኦሮሞ ጽንፈኞች ይፋቱና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ይቁሙ !!!!!
– ከአንድ አመት በፊት ቃል የገቡትን፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ ተግባራዊ እርምጃ ይወሰዱ፣
– ተሸክመው ይዘው የሚዞሩትን፣ ኦህዴድ/ኦዴፓ የተባለ የበሰበሰ ዘረኛ ድርጅት ወይም አሮጌዎን አቁማዳ ያራግፉና ወደዚያ ይጣሉ። አዲስ አቁማዳ ይያዙ፣
– ዜጎች በሁሉም የአገሪቷ ግዛቶች የዘር ልዩነት ሳይደረግባቸው መኖር የሚችሉበትን ዘመናዊ የሆነ ስርዓት ለመዘርጋት ቁርጠኝነት ያሳዩ፣
– ይሄ የኋላ ቀር የጎሳ ፌዴራሊዝም ፈርሶ ለአስተዳደር አመች የሆነ፣ ሁሉንም ዜጎች እኩል የሚያይ፣ ከዘርና ከጎሳ የጸዳ ፊዴራል ሲስተም እንዲዘረጋ ተግባራዊ የሆነ እንቅስቃሴ ይጀመሩ። አሃዳዊ ስርዓት ይመለስ አላልኩም። አሁን ካለው የተሻለ ወደፊት ሊያሻግር የሚችል ዘመናዊ የፌዴራል ስርዓት ነው ይዘርጋ የምለው፣

ያኔ ክብር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከአንድ አመት በፊት ደግፈዎት የነበረውን፣ አሁን ግን ” ኤይ ፣ ኤዲያ” ብሎ ከርስዎ እየሸሸ የመጣውን ህዝብ መልሶ ወደርስዎ ሊስቡት ይችላሉ። ችግኝ መትከል ሸጋ ቢሆንም፣ ከችግኝ በላይ የሰው ልጅ ክብር እንዳለው ሲያወቁ፣ ያኔ ሁላችንም ከጎንዎት እንሰለፋለን።

መድሃኔ አለም ኢየሱስ ክርስቶስ ልቦና ይስጥዎት !

ከዚህ በታች የሚታየው ፎቶ በጂንካ ነው። “አግላይ የዘር ፖለቲካ በምን መልኩ ውጤቱ ዜሮ ነው” በሚል የዶ/ር አብይ ፎቶ ያለበት ፎቶ ነው። ያኔ ፣ ከአንድ አመት በፊት።