‎ዶ/ር አቢይ የአክራሪ ኦነጋዊያን አይዲኦሎጂ የትሮዣን ፈረስ ወይስ ኢትዮጵያዊነት የዶ/ር አቢይ የትሮዣን ፈረስ??-ወንድወሰን ተክሉ

መረጃ ቲቪን ሰብስክራይብ በማድረግ ወቅታዊ ዜናዎችን፣ ትንተናዎችን፣ የኪነጥበብ ፕሮግራሞችን እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ማግኘት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

**አንድ -መነሻየዶ/ር አቢይ መራሹ የኦዴፓ መንግስት በትረስልጣኑን የጨበጠው በሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግልና ብሎም መጨረሻ ላይ የማሸነፊያዋን ጎል (Penalty )ባስቆጠረው በአዴፓ ቢሆንም ይህ የአዴፓና ብሎም መላው የአማራ ህዝብ ለለውጥ ያደረገው ታላቅ ተጋድሎ፣መስዋእትነትና ወዳጃዊ ወገንተኝነት በዶ/ር አቢይ የሚመራውን ኦዴፓ መሰሪ የሆነ የክህደት እርምጃ እንዲወስድበት የልብ ልብ ከመስጠትና አማራ ተኮር ሴራ እንዲያራምድ ከማድረግ ውጭ ለነገደ አማራ ህዝብም ሆነ ለአዴፓ የፈየደው ነገር እንደሌለ ዛሬ ላይ በእርግጠኝነት ለመናገር ያስገደዱን ተግባራት ሲፈጸሙ እያየን ነው፡፡እንደ ሀገር ኢትዮጵያ እንደማህበረሰብ ደግሞ የነገደ አማራ ህዝብ የኦዴፓ መራሹ ሴራ ገፈት ቀማሽ በመሆን በህልውናቸው ላይ ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦ ይገኛል የሚሉ ድምጾችን ተአማኒነትን የሚገልጹ በርካታ አመላካች እርምጃዎች ሲወሰዱ በአንክሮ ለማየት ተችሏል፡፡

ከሶስት ሳምንት በፊት በባህር ዳር የተከሰተው አደጋ እንደ አቢይ መራሹ የኦዴፓ መንግስት አገላለጽ «መፈንቅለ መንግስት» ሁኔታን ተከትሎ በነገደ አማራ ላይ የተከፈተው ሁሉን አቀፍ ዘመቻ፣የአዲስ አበባ ጉዳይ፣የአክራሪ ኦነጋዊያን አጀንዳ ያላቸው የኦሮሞ ፖለቲከኞች አይገፌ መሆን፣የጠምሩ ለዴሞክራሲና ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ላይ ያላቸው አቋም ከጠቋሚ ኦዴፓዊ ድርጊቶች ውስጥ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ይፋዊ ተግባራት ሲሆኑ ከእነዚህ ይፋዊ ተግባራቶች ሌላ ከመጋረጃው ጀርባ የተወጠኑትንና የታቀዱትን ዓላማዎች ማየቱ ደግሞ እንደ ሀገር አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብና ሉአላዊቷ ኢትዮጵያን ህልውናን እና እንደ ነገድ ደግሞ የነገደ አማራን ህልውናን ምን ያህል ለአደጋ የተጋለጡ ስለመሆናቸው እንድናይ ያስገድደናል፡፡

ነገሮች በፍጥነት እየተለዋወጡ በሚሄዱበት በአሁኑ ሰዓት በዶ/ር አቢይ የሚመራው የኦዴፓ መንግስት የዜግነት ፖለቲካን እናራምዳለን ከሚሉ የአንድነት ጎራው ዘንድ የሚደግፉት ወገኖች ዛሬም ድረስ በተመሳሳይ አቋማቸው እንደጸኑ ማየት ሌላው የሀገሪቱን ህልውና ከአደጋ ለመታደግ አዳጋች አድርጎ ያሳየን ሁኔታን የመፍጠሩን ሁኔታ በአስጊ ሂደቶች ላይ እንድንገኝ አስገድዶናል፡፡

የአቢይ መራሹ መንግስት በገንዘብ እማይገዙ የተባሉትን የተቃዋሚ ጎራ መሪዎችን በሙሉ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ ገዝቶዋቸው እኪሱ ማድረግ የመቻሉ ሀቅ መንግስት በአሁኑ ሰዓት አንድም የሆነ ይፋዊ ተቃዋሚ የሌለው እንዲሆን ያደረገ ሲሆን ትንሽ ይገዳደሩኛል የሚላቸውን ኃይሎች ደግሞ በ«መፈንቅለ መንግስት» ፖለቲካዊ ሴራ በጅምላ የማደንና የማሰር ዘመቻን ከፍቶባቸው አደረጃጀታቸውን ሳይጠነክር በፊት በማፈራረስ ተግባር ላይ የተጠመደ ሆኗል፡፡

***ሁለት -ነገደ አማራን ልክ እንደ ኩርድ፣ጅብሲና አርመን ሀገር አልባ የመሆን እጣፈንታ

ዛሬ በዶ/ር አቢይ የሚመራው የኦዴፓ መራሹ መንግስት እያራመደ ያለው አጀንዳ በአክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ከዘመናት በፊት ተቀምሮ ጊዜና ወቅት ሲጠባበቅ የነበረው ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርና ስምን አፍርሶ የአፍሪካ ቀንድ ኮንፌዴሬሽን የሚባልን ሀገር የመፍጠር ሁኔታን በሚመስል መልኩ ተግባራዊ ድርጊቶቻቸው እያሳበቁ ነው፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ኮንፌዴሬሽንን የሚፈጥሩ ክልላዊና አከባቢያዊ መንግስታትም
1ኛ-የትግራይ ክልላዊ መንግስት
2ኛ-የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት
3ኛ-የሲዳማ ክልላዊ መንግስት
4ኛ-የሱማሌ ክልላዊ መንግስት ከኢትዮጵያ በኩል ሲሆን ከሰሜን የኤርትራ መንግስት ከምስራቅ የሶማሌላንድ መንግስት እንዲካተቱበት የታቀደ ሲሆን ለዚህ ዓላማ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚነት የኤርትራው መንግስትና ብሎም የትግራዩ ነጻ አውጪ ነኝ ባይ ህወሃት ሙሉ በሙሉ ተስማምተው ሚናቸውን ለመወጣት በተጠንቀቅ ላይ እንዳሉ ይታያል፡፡

በዚህ የአፍሪካ ቀንድ ኮንፌዴሬሽንን የመመስረት አጀንዳ ላይ እንደ ነገድ የራሳቸውን ክልላዊ መንግስት ሳይመሰርቱ ወደ ትግራይ፣ኦሮሚያ፣ሶማሌና ሲዳማ ክልሎች ስር በውዴታም ይሁን በግዴታ እንዲጠቃለሉ ከተበየነባቸው ህዝቦች ውስጥ የነገደ አማራ ህዝብ አንዱና ዋነኛው ሲሆን የእቅዱም ተፈጻሚነት የነገደ አማራን ግለርስት መሬት በመቀራመት ዛሬ በኢራን፣ኢራቅ፣ሶሪያና ቱርክ ተከፋፍለው እንዳሉት የኩርድ ህዝብ ሀገርና ግዛት አልባ የማድረግ ታላቅ የሆነ ሴራ እንዳለው ነው መረዳት የሚቻለው፡፡

የአማራን ከትግራይ ጋር እሚያዋስነውን ሴማናዊ ግዛቶቹን ማለትም ሰሜን ጎንደርንና ሰሜን ወሎን በትግራይ ስር እንዲወድቅና ደቡባዊውን ወሎን፣ሸዋን እና ከፊል ጎጃምን ደግሞ በኦሮሚያ ስር በማዋል የተቀሩትን ውስን የጎንደርና ጎጃም አውራጃዎችን በአማራ፣ቅማንት፣አገው አውራጃዎች ከፋፍሎ በተጽእኖ ስር ማዋል የሚል ሲሆን ይህንን ኦነጋዊ አጀንዳን እውን ለማድረግ ከሁሉ በፊት ለዚህ ዓላማ/አጀንዳ እንቅፋት ይሆናሉ ተብለው Identified የተደረጉ ሁለት ክልሎችን ማለትም የአማራን ክልላዊ መንግስትና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልላዊ መንግስትን ማዳከምና ማፈራረስ በመሆኑ በመጀመሪያውኑ በእነዚህ ሁለት ክልሎች ላይ የኦነጋዊያኑ የጥቃት ሰይፍ ሊመዘዝ የቻለ ሲሆን የዶ/ር አቢይ መራሹ መንግስትም ይህንን በቅንባር ቀደምትነት የማስፈጸሙን ተግባር በብቃት ሲፈጽምና ሲያስፈጽም እየታየ ነው፡፡

የነገደ አማራና ብሎም የዶ/ር አቢይ መራሹን ኦዴፓን ወደ ስልጣን በማምጣት ደረጃ ቁልፉን ሚና የተጫወተው አዴፓ ታማኝነቱን ለዶ/ሩ አመራርና ለመንግስታቸው ቅንጣት ታህል ሳይቀንስ በጀርባ የተወጋ ይመስል በ«መፈንቅለ መንግስት» ተብዬው ሴራዊ አደጋ ማግስት አጠቃላይ የነገደ አማራ ፖለቲካዊ ተቋማትና እንዲናዱ ከፍተኛ የሆነ ዘመቻ ሊከፈትባቸው በቅቷል፡፡

ዛሬ በመላው ዓለም ሀገር አልባ ሆነው የተበተኑት አውሮፓዊያኑ የጅብሲና የአርመን ነገዶች ልክ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት ልክ ዛሬ በአራት የባህረ ሰላጤ ሀገራት ተከፋፍለው እንዳሉትና የራሳቸውን ሀገርና ንጉስ እንደነበራቸው የኩርድ ህዝብ ሁሉ ከዘመናት በፊት የራሳቸው የሆነ ሀገርና መንግስት ያላቸው ሲሆኑ ዛሬ ግን ሀገርና መንግስት አልባ ሆነው በመላው ዓለም ተበትነው እንዳሉት ሁሉ የአማራም ነገድ ዛሬ ፈጣን የሆነ እርምጃ ካልወሰደና ነገዳዊ ማንነቱን በሚያረጋግጥለት መልኩ ተዳራጅቶ ባላንጣዎቹን ካልመከተ ተመሳሳይ እጣፈንታ አይገጥመውም ለማለት የቀን ህልመኛ ፈሪና ሰነፍ መሆንን ይጠይቃል፡፡

የሁኔታው አስከፊነት ማለትም የነገደ አማራ ተዳክሞ ለተቀራማቾች ሰለባ መሆን የሚጎዳው በመጀመሪያ ደረጃ እራሱኑ ነገደ አማራን ቢመስልም At long hand ውስጥ ትልቁ ሰለባ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ የምንላት የሺህ ዘመናት ባለእድሜ ሀገራችን እንደምትሆን እሙን ነው፡፡

**ሶስት-ግንዛቤ ሊሰጣቸው እሚገቡ ክስተታዊ ምልክቶች

ለመሆኑ የዶ/ር አቢይ መራሹ የኦዴፓ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ ሲያስተጋባ የነበረውን የአንዲት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መንፈስን በሚጻረር መልኩ በሚከተሉት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ዳተኛ ሆኖ ቃሉን በማጠፍ ሊቆም ቻለ ብላችሁ እራሳችሁን ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ??

እነሱም-
1ኛ- የአዲስ አበባ ጉዳይ-ለምንድነው የዶ/ር አቢይ መራሹ ኦዴፓ መንግስት በአዲስ አበባ ላይ ከመላ ኢትዮጵያዊያን ፍላጎትና አላማ ውጪ በተቃረነ መልኩ የግል ንብረት ለማድረግ ቁርጥ አቋም ወስዶ ለተግባራዊነቱ እየሰራ ያለው ?? ዛሬ በአዋሳና በይርጋለም አከባቢ ህዝብ በሚበጠበጥበት ወቅት ዝምታን መርጦ ወደ አስመራ ያቀናውና ብሎም የኦነግ ኃይሎች ወደ ሃያ የሚጠጉ ባንኮችን ሲዘርፉ በዝምታ በማለፍ ግን በአዲስ አበባ ጉዳይ ያገባናል ብሎ መንቀሳቀስ በጀመረው እስክንድር ነጋ ላይ ዘመቻ ለመክፈት የተጣደፈው?

2ኛ- ከ150ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ሲከበር የነበረውንና እንዲቋረጥ የተደረገውን የኢሬቻ መንፈሳዊ ክብረ በዓልን ከመጪው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እናከብራለን ማለቱ በእርግጥም መንፈሳዊውን በዓል በሞቀና በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ብቻ ነው ወይንስ ምን ዓላማ ኖሮት ነው?’

3ኛ-አዲስ አበባን የኦሮሚያ ብቻ ለማድረግ የተወሰነበትስ ሁኔታ ለምን ይመስላችኋል?

4ኛ-ከሁለት ቀን በፊት በኦዴፓ የተገለጸው በኦሮሚያ የዜግነት ትምህርት ይዘትና ዓላማውስ ምን ይመስላችኋል??

5ኛ-ዶ/ር አቢይ ወደ ትግራይ አክሱም ተጉዞ ከክልሉ መሪ ዶ/ር ደብረጺዮን ጋር መክሮ በተመለሰ ማግስት ብዙም ሳይቆይ የባህርዳሩ አደጋ መከስትና አደጋውንም ወዲያውኑ የ«መፈንቅለ መንግስት » ሙከራ በማለት ክልሉን በፌዴራል ኃይል ስር እንዲውል አድርጎ አጠቃላይ የነገደ አማራን ፖለቲካዊ፣ደህንነታዊና ክልላዊ መዋቅርን Dismantle ለማድረግ ለምን ይመስላችኋል እዚያ ከትሞ ጸረ አማራ ዘመቻን እያጧጧፈ ያለው?

6ኛ-የነገድ ተኮር ብሄርተኝነት ለሀገራዊ ህልውና አደጋ ነው ሲል መንግስት እራሱ ሲያስተጋባ ይደመጣል ግን የዚህ ጎሳ ተኮር አደረጃጀት ዋና ምንጭ ስለሆነው ህገመንግስት መለውጥም ሆነ መሻሻል ጉዳይ አትምጡብኝ በማለት ድርቅ ብሎ ስለሀገር አፍራሹ ህገመንግስት ጥብቅና እየቆመ ያለው??

7ኛ-በአሜሪካ የኦሮሚያ ቆንስላ መክፈትንስ ለምን ይሆን ብላችኋል??

8ኛ-የዓባይን ግድብ ቸል ብሎ ማስቆምና ብሎም የሀገሪቱ ዓይን የሆኑትን እንደነ የኢትዮጵያን አየር መንገድ፣ቴልኮም፣መብራት ኃይልንና የባቡርና የንግድ መርከብ ድርጅቶችን በፕራይቭታይዜሽን ስም ለመሸጥ የታሰበው በእርግጥ ለሀገር ታስቦ ነውን ወይንስ ከላይ ላሰፈርኩት ድብቅ አጀንዳ አንጻር መሸጥ ስላለባቸው ነው??

9ኛ-የዶ/ር አቢይ መራሹ መንግስት በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ህዝባዊ ድጋፍ ያገኘ መንግስት ሆኖ ሳለ ጠምሩ ግን የሚተማመኑት በኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ ላይ ሳይሆን በራሳቸው በኦሮሞ ህዝብና ብሎም በውጪ ኃይሎች ብቻ ለምን ሆነ?

10ኛ-ጠምሩ በፓርላማ ቀርበው የሲዳማ የክልል ልሁን ጥያቄ በህገመንግስቱ መሰረት በህጋዊ መንገድ ብቻ የሚመለስ ይሆናል እያሉ ከጎን የጃዋር፣ኦነግና የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሲዳማ ጥያቄ በውድም በግድም ይፈጸማል እያሉ ሲያስተጋቡና ብሎም ትርምስ ሲፈጠር ለምንድነው ጠምሩ ሁኔታውን በዝምታ እያዩ ያሉት??

ሁሉም ምክንያትና ዓላማ አለው፡፡ያለምክንያትና ያለ አላማ የተፈጸመና እሚፈጸም አንዳች ተግባር የለችም፤ አትኖርምም፡፡ ይህን ሂደት በቅርበት የሚከታተሉ እጅግ ጥቂት ሰዎች ዶ/ር አቢይ የኦነግ አይዲኦሎጂ ትሮዣን ፈረስ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ የለም ኢትዮጵያዊነትና ዴሞክራሲ የዶ/ር አቢይ የትሮዣን ፈረስ ናቸው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

ከእነዚህ ለየት የሚሉትና ዛሬም በዶ/ር አቢይ አቋም ላይ ሙሉ በሙሉ ተስፋ ያልቆረጡ የለም ዶ/ር አቢይ በኦዴፓ ውስጥ በተሰገሰጉ አፍቃሬ ኦነጎች ክፉኛ ተወጥረዋል እንጂ ሰውዬው ይህንን አይነት ተግባራትን የመፈጸም ፍላጎትና አላማ የላቸውም ሲሉ ይከራከሩላቸዋል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሰዎች እንደሚሉት ዶ/ር አቢይ በእርግጥም በአክራሪ የኦነግ ኃይሎች ያለፍላጎታቸው የፊጢኝ ተደፍቀዋል ብለው ቢናገሩም እንዴት አድርገው ከዚህ ደፈቃ እንደሚገላገሉና በአሸናፊነት ነጥረው ወጥተው ሀገሪቱን እንዳስተጋቡት መፈክር መምራት እንደሚችሉ የሚያሳዩት አቅጣጫና መፍትሄ የላቸውም፡፡

የዛሬ ጽሁፍ አቀናባሪ ከዓመት በፊት ዶ/ር አቢይ በኦህዴድ ውስጥ ባሉ አክራሪና አፍቃሪ ኦነጎች በኃይል ተደፍቀዋል ብሎ የሚያምነውን እምነት ዛሬ ላይ ማስተጋባት አይችልም፡፡

እንደዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ መረጃ ላይ የተንተራሰ እምነት መሰረት ዛሬ በዶ/ር አቢይ እየተፈጸሙ ያሉት ተግባራቶች በአፍቃሪ ኦነጎች አስገዳጅነት ሳይሆን በራሳቸው በዶ/ር አቢይ በጎፈቃድና ፈላጊነት ሆን ብለው የሚፈጽሟቸው አላማዎቻቸው ናቸው ብሎ ነው እሚያምነው፡፡

ዶ/ር አቢይ በአፍቃሬ ኦነግ ካድሬዎች ተጽእኖ ስር ወድቀዋል ብለን ብናምን እንኳን እሳቸው በተጽእኖው ስር የመሆን ፍላጎት ከሌላቸው የሚድንበት ብቸኛ መንገድ «እኛ እንሞትልዎታለን» ያሏቸውን የአዲስ አበባ፣የአማራን እና ሌሎች ህዝቦችን ድጋፍ በማስተባበር በኦህዴድና ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን የአክራሪ ኦነጋዊያንን ተጽእኖን መክቶ ማሸነፍ ይቻላል እንጂ በአንጻሩም ለኦነጋዊ አመለካከትና አላማ ሲሉ ነፍሳቸውን እስከመስጠት በደረሱት የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና በአማራው ህዝብ ላይ የክህደት ተግባር ፈጽመው ባልዘመቱባቸው ነበር ብሎ ይህ ጸሃፊ ያምናል፡፡

እናም ዶ/ር አቢይ የኦነጋዊ አይዲኦሎጂ የትሮዣን ፈረስ በመሆን ለሀገራዊ ህልውናችን ብርቱ የሆነ አደገኛ ስጋት የደቀኑብን መሪ ሲሆኑ ይህንን እይታዊ እምነት አልጋራም የሚሉ ከሆነ እጅግ አሳማኝ የሆኑ እርምጃዎችና ተግባሮችን በመፈጸም ሊያሳምኑን ይገደዳሉ ብዬ ነው እምረዳውና ይህንን አይነቱን ተግባር ማለትም የእኛን የኢትዮጵያዊያንን ልብና ቀልብ ከስጋት የሚመልሱ እርምጃዎችን መውሰድ የመቻልና ያለመቻላቸውንም በቀጣዩቹ ሳምንታትና ወራት ውስጥ ማየት የምችለው ጉዳይ ይሆናል እያልኩ ጽሁፌን እደመድማለሁ፡፡

************
አስተያየትዎንና ጥያቄዎን በ [email protected] ጻፉልኝ እመልሳለሁ!