ኢህአዴግ ከአባል ፓርቲዎቹ መግለጫ በኋላ ወዴት ያመራል?


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ በበርካቶች ዘንድ የተለያዩ አነጋጋሪ ጉዳዮችን በማስነሳት እያነጋገረ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ዶ/ር አደም ካሴ አበበ፣ ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ገቢሳ፣ እንዲሁም አቶ ልደቱ አያሌው በመግለጫውና በገዢው ፓርቲ ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ገቢሳ እንደ ጥምረት ፓርቲዎቹ አንድ ሃሳብ እንዲኖራቸው የሚጠበቅ አይደለም ይላሉ። ጥምር ፓርቲ ውስጥ ያሉ ቡድኖች ካልተግባቡ የመፍረስ እድል ይኖራል፤ ይህም አዲስ ነገር አይደለም።

ዋናው ነገር የኢህአዴግ ፓርቲዎች ጥምረት ከሌለ ሃገሪቱ እንዴት እንደምትተዳደር ጥያቄን ሊፈጥር ይችላል። ነገር ግን ገዢው ፓርቲ ችግር ውስጥ ከገባ ሰንብቷል።

ኢህአዴግን በአንድነት አዋህዶ ይዞት የነበረው ህወሓት እንደነበር የሚናገሩት ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ገቢሳ አሁን ህወሓት ያንን ለማድረግ በሚችልበት ደረጃ ላይ ስላልሆነ እያንዳንዱ የጥምረቱ አባል የሆነ ፓርቲ በተለያየ አቅጣጫ መሄድ ከጀመሩ ቆይተዋል። ወደፊት ልዩነቶቻቸውን አቻችለው አብረው ሊቀጥሉ ይችላሉ ወይም ደግሞ ሊታረቅ ወደማይችል ቅራኔ ውስጥ ገብተው ፓርቲው ሊፈረካከስ ይችላል፤ ነገር ግን አሁን ካለው ሁኔታ ተነስተን ይሄ ሌሆን ይችላል ለማለት አስቸጋሪ ቢሆንም ከሁለቱ ግን አንዱ ይሆናል።

ነገር ግን የኢህአዴግ ጥምር ፓርቲዎች ውስጥ እየታዩ ካሉት ነገሮች በመነሳት በጥምረቱ ውስጥ በአንድነት የመቆየት እድላቸው የመነመነ ይመስላል፤ ቢሆንም ግን ሃገሪቱ ወደ ምርጫ እየሄደች በመሆኗ ያሉባቸውን ችግሮች አቻችለው ለዚያ ሲሉ አብረው ሊቆዩ ይችላሉ።

ከሁሉ ግን ግልጽ እየሆነ የመጣው በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች በግንባሩ ዉስጥ የፈጠሩትን ጥምረት በማስቀረት ወደ አንድ ወጥ ውሁድ ፓርቲነት እንሸጋገራለን ያሉት ዕቅድ ፈጽሞ ሞቶ የተቀበረ ጉዳይ ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ህዝቄል የግንባሩ ውህደት የማይሆን እንደሆነ ይናገራሉ።

ኢህአዴግ እንደ ድርጅት አለ፤ በድሮው በጥንካሬው በድሮው አስተሳሰብና ሞገስ ግን የለም። ተወደደም ተጠላም ግን ኢህአዴግ አለ አሁን ሀገሪቱን እየመራት ያለው እርሱ ነው ይላሉ አቶ ልደቱ። አሁን ለውጡን እየመሩት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትርም የተመረጡትም በኢህአዴግ ነው።

ኢህአዴግ እርሳቸውን ሲመርጣቸው ህወሓት አባላትም እዚያው ቁጭ ብለው እጃቸውን አውጥተው ነው የመረጧቸው። ይህንን ሀገርና ህዝብ ወደዚህ አይነት ከፍተኛ ችግር የከተተው እንደ ድርጅት ራሱ ኢህአዴግ የሚባልው ድርጅት ስለሆነ ከዚህ ችግር ለማውጣትም መስራት ከፍተኛ ሚና መጫወት ያለበት ራሱ ኢህአዴግ ነው ብለው ያምናሉ አቶ ልደቱ።

“ኢህአዴግ ስንል ደግሞ ህወሓትንም ይጨምራል። ስለዚህ ከመነጣጠል ይልቅ በአብሮነት በመስራት ለለውጡ መትጋት አለበት።”

ግጭት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ?

እንደዚያ የሚያስቡ ወይንም ሙከራ የሚያደርጉ ኃይሎች ሊኖሩ ይችላሉ። በእኔ እምነት ግን የትግራይም ሆነ የአማራም ህዝብ በአሁኑ ወቅት አሁን ከገባበት ችግር መውጣት ነው እንጂ ወደሌላ አሳሳቢ ውጥረትና ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት አለው ብዬ አላምንም። ህዝቡ የዚያ አይነት እምነት እስካለው ድረስ እንደዚያ አይነት የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች የሚፈልጉትን ነገር ያደርጋሉ ብለው አያምኑም አቶ ልደቱ።

ኢህአዴግ ምን ያድርግ?

ይህ ገዢ ፓርቲ፤ ኢህአዴግ የሀገሪቱን ዕታ ፈንታ በብቸንነት ተቆጣጥሮ እያለ በሀላፊነት ስሜት መስራት አቅቶት ሚበታተን ከሆነ እርሱ ውስጥ የሚፈጠረው መበታተን ለሀገርም ሊተርፍ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው ልደቱ።

ይህ ትልቅ ሀገርና የሕዝብ ሀላፊነት ያለባቸው መሆናቸውን አውቀው ከመቼውም በላይ ከግል እንዲሁም ከቡድን ስሜትና ፍላጎት በፀዳ መልኩ ከፖለቲካ ሽኩቻ በፀዳ መልኩ አብረው መስራት አለባቸው። አዴፓም አሁን ባለበት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ሊረዳ የሚገባው ነው። ከፍተኛ አመራሮቹ ተገድለውበት ተዳክሟል። ይህንን ድርጅት በዚህ ወቅት ለማጥቃት መሞከርም ተገቢ አይደለም ይላሉ አቶ ልደቱ።

አቶ ልደቱ አያሌው የህወሓት መግለጫ በአንድ በኩል ሀገሪቱ ውስጥ አሳሳቢ ችግሮች መኖራቸው መጠቀሱና እነዚህን ነገሮች መንግሥት ይፍታቸው መባሉ ችግር የለውም ባይ ናቸው። በዚያ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ አሳሳቢ ነገር መኖሩ አጠያያቂ አይደለም።

ነገር ግን ደግሞ አንዳንድ ነጥቦች አሁን ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን በሰከነ መልኩ በብቃት ለመፍታት የሚያስችሉ ሳይሆኑ የበለጠ ችግሩን የሚያወሳስቡና ከባድ የሚያደርጉ ሆነው ነው ያገኘኋቸው ይላሉ።

እንደ አቶ ልደቱ አባባል አሁንም ከሕዝብ ጋር ተያይዞ ህወሓት የሚነሳበትን ቅሬታ ቦታ ሰጥቶ ለመተው ፍላጎት ያለው አይመስላቸውም።

ትምክህተኛ የሚለው አባባል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብዙ ችግር ፈጥሯል የሚሉት አቶ ልደቱ “እነርሱ ሲናገሩ ለጥቂቶች ነው ሕዝቡን አይደለም ቢሉም ህዝብ አባባሉን እንደ ስድብ ወስዶ ጠልቶታል። ህዝብ የጠላውን አነጋገር አሁን ለውጥ በሚፈለግበት ወቅት እየደጋገሙ ማንሳት የሚጠቅም አይመስለኝም፤ ችግርን ያባብሳል እንጂ።”

ሁለተኛ ጉዳይ ብለው አቶ ልደቱ እንደስህተት የሚያነሱት ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ችግር የመነጨው አሁንም ከአማራ አካባቢና ከአዴፓ እንደሆነ ብቻ ተደርጎ የተገለፀ መንገድን ነው። “በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ለተፈጠረው ችግር የተጠያቂነት ደረጃ እናውጣ ከተባለ ቀዳሚው ህወሃት ነው የሚሆነው። አለበለዚያ ደግሞ በጥቅል የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ናቸው የሚሆኑት” ይላሉ።

አንድን ክልል እየመራ ያለ ድርጅት ለይቶ በዚህ ደረጃ ተተያቂ ለማድረግ መሞከር፤ በዚህ ደረጃም ማስፈራራት ስም ማጥፋት (ብላክ ሜል) ማድረግ አሁን ከሚፈለገው አንፃር ሁኔታዎችን የሚያባብስ እንጂ መፍትሄ የሚሆን እንዳልሆነ አቶ ልደቱ ይናገራሉ።

የተነሱ ሃሳቦች

ዶ/ር አደም ካሴ አበበ ሆላንድ ዘ ሄግ ውስጥ የሚገኙት የፖለቲካ ተንታኙ እንደሚሉት በመግለጫው ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሳበው ከመንግሥት ባለስልጣናትና ከጄነራሎቹ ግድያ ጋር የተያያዘው ክፍልና በአዴፓና ህወሓት መካከል ያለው አለመግባባት የተገለፀበት ክፍል ነው። ይህም ለአርሳቸው ኢህአዴግ እንደ ግንባር ወደፊት ወዴት ነው የሚሄደው? ፣ የታቀደው ምርጫ ምን መሆን አለበት እና ሲዳማን ጉዳይ ያነሳባቸው መግለጫ ክፍሎች ወደፊት የሚያዩ ሆነው ነው ያገኟቸው።

አቶ ልደቱ በመግለጫው ውስጥ እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ ነገሮች እንዳሉ በማንሳት፤ በአንድ በኩል የባህርዳሩና የአዲስ አበባው ግድያ የተያያዘ መሆኑን እንደሚገልጽ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ ተጣርቶ እውነቱ ታውቆ ለህዝብ መገለፅ አለበት ተብሎ መባሉን ያነሳሉ።

“በመግለጫው ላይ በጣም በተቀነባበረ ሁኔታእና ረዥም ጊዜን በፈጀ ዝግጅት አዲስ አበባ ያሉት ሰዎች እንደተገደሉ ተደርጎ ሰፍሯል፤ይህ ትክክል አይደለም” ይላሉ።

ይህም የሚያሳየው ህወሓት በቂ መረጃ አለኝ እያለ ነው ማለት ነው። ይህ መረጃ ካለ ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማቅረብ አለበት ማለት እርስበእርሱ ይጣረሳል ብለው ይጠቅሳሉ።

ሌላው አቶ ልደቱ ያነሱት አዲስ አበባ ውስጥ ከተፈጸመው የጄነራሎች ግድያ ጀርባ የውጪ ኃይሎች እጅ እንዳለበት መግለጫው በግልፅ ማስቀመጡ ነው። “ይህንን ብሎ ደግሞ ወረድ ይልና በአማራ ክልል የተከሰተውን ነገር የውጪ እጅ እንዳለበት አድርጎ መግለፅ ትክክል አይደለም” ይላሉ።

ህወሓት አሁን ሀገሪቱ የገባችበት ችግር እውነት ያሳስበው ከሆነ በመውቀስ በመክሰስ ሳይሆን ፓርቲው ውስጥ ተገቢ የሆነ ትግል በማድረግ በትዕግስትና በሆደ ሰፊነት አብሮ ለመስራት በመዘጋጀት ለዚህ ችግር አገሪቷንና ሕዝቡን የዳረጉት መሰረታዊ ነገሮች ምንድን ናቸው በሚለው ግምገማሞ የእሱ ተጠያቂነት ከፍተኛ እንደነበር አምኖ በመቀበል ነው መፍትሄ ማግኘት የሚቻለው ይላሉ አቶ ልደቱ።

ዕህ ባለፉት 27 ዓመታት የተሰራው ሁሉ መልካም እንደሆነና ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ችግር እርሱ ከስልጣን ከተነሳ ለኋላ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ የተፈጠረ አድርጎ የማቅረብ ሙከራው ካለፈው ጥፋቱ ካለፈው ውድቀቱ አለመማሩን ነው የሚያሳውም ይላሉ።

አቶ ልደቱ አክለውም “ህወሓት የችግሩ አካል ነው የመፍትሄውም አካል መሆን አለበት መፍትሄው አካል ሲሆን ደግሞ በሙሉ የሀላፊነት ስሜት መሆን አለበት” ሲሉ ይመክራሉ።

አብሮ ስለመስራት

ስለ ሀገር ከሆነ የምናወራው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከእራስ ቡድን ፍላጎትና ጥቅም በላይ የሀገር ጥቅም የሚያሳስባቸው ከሆነ አማራጩ እርስ በእርስ መካሰስ፣ የፖለቲካ ሽኩቻው ወስጥ መግባት ሳይሆን አንድ ላይ መቆም ነው።

27 ዓመት ሙሉ የበደሉትን ህዝብ ለመካስ የሚፈልጉ ከሆነ መፍትሔው ጥሎ መውጣት አይደለም አይደለም የሚሉት አቶ ልደቱ ፤ መድረኩ ውስጥ ሀቀኛ የሆነ ትግል አድርጎ ችግሩን በጋራ እንዲፈታ ማድረግ ነው። ኢህአዴግ እንደ አንድ ድርጅት መቆም የሚጠበቅበት ጊዜ ዛሬ ነው።

በዚህ ሰዓት አኩርፎ መውጣት የኢትዮጵያን ችግር የበለጠ ያወሳስበዋል እንጂ መፍትሄ የሚሰጥ አይመስለኝም ይላሉ።

ከሌላ ድርጅት ጋር በጋራ ስለመስራት

ይህ ሀሳብ ከፋፋይ ነው፤ አሁን ኢትዮጵያዊያኖች በአጀንዳ በተለያየ መልኩ ተከፋፍለን እርስ በእርስ የምንታገልበት ወቅት መሆን የለበትም። አንድ ላይ ሆነን ይህንን ችግር ተወጥተን ህዝቡ ወደ ሚፈልገው አቅታጫ ይህችን ሀገር ለማሻገር ነው መጣር ያለብን።

ስለዚህ ይሄ ከልጅነት ጀምሮ የተጠናወተው የመከፋፈል ባህሪ ህወሕት አሁንም እንዳልለቀቀው ይህ መግለጫ አሁንም በደንብ ያሳያል ይላሉ አቶ ልደቱ። ስለዚህ ከዚህም አንፃር የያዘው መንገድ ትክክል አይደለም። አሁን የሚጠበቀው አንድ ላይ ቁጭ ብሎ መስራት ነው አንእጂ መነጠል እንዳልሆነ ይመክራሉ።

ከእነማን ጋር ይሰራል?

ድርጅቱ በግልፅ ከእነዚህ ከእነዚህ ጋር እሰራለሁ ባላለበት በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት ይቸግረናል። ነገር ግን ፖለቲከኛ ስለሆንኩ በተዘዋዋሪ ምን ለማለት እንደፈለገ ይገባኛል የሚሉት አቶ ልደቱ፤ “ይህ አካሄድ አፍራሽ ነው አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኃይል አሰላለፍ በከፍተኛ ደረጃ የሚያናውጥ ሀገሪቱን ወደበለጠ ውስብስብ ችግር የሚከት ነው።”

በዚህ መግለጫ ትኩረት የተደረገው አዴፓ ላይ ነው። እርሱን እንደጠላት በመፈረጅ ከእርሱ አመለካከት ጋር የሚሄዱ ሌሎች ድርጅቶችን ምናልባትም ከኢህአዴግ ውጪ ካሉ ድርጅቶች መካከል ከህወሓት አመለካከትና አደረጃጀትጋር አብረው ከሚሄዱ ኃይሎች ጋር ለመስራት የመፈለግ ነገር እንደሚያዩ ይናገራሉ አቶ ልደቱ።

ሲያክሉም “ይህ በጣም ከፍተኛ ችግር ነው። ትግራይ ሕዝብንም የሚገልፅ ነው ብዬ አላስብም። የትግራይ ሕዝብንም ከኢትዮጵያ ህዝብ የሚነጥል አስተሳሰብ ነው። ህወሓት እራሱ ባጠፋው ጥፋት የትግራይ ሕዝብን ችግር ውስጥ እንዲገባ ነው ያደረገው። ለዚህ ተጠያቂ ነው።”

“በዚህ መልኩ የሚቀትል ከሆነ አሁንም እሰራ ያለው የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል እየሰራ ነው ያለው ማለት ነው፤ ይሄ ደግሞ አያዋጣም። የትግራይ ሕዝብም የዚህ መግለጫ መንፈስ ትክክል አለመሆኑን በማወቅ ድርጅቱን መገሰፅ ያለበት እመስለኛል።”

“ሕዝቡም ህወሓትን ትክክል አይደለህም፣ አብረንህ እንሰራለን መብታችን እንዲከበር እንፈልጋለን ነገር ግን በኢትዮጵያ አንድነት ላይ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በገጠመው ችግር ላይ ተነጥለን ወጥተን የችግሩ አካል መሆን የለብንም የመፍትሄው አካል መሆን አለብን የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ያለበት” ይላሉ አቶ ልደቱ።