(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ ለመሠረት ሚድያ ከሚደርሱ ተከታታይ ጥቆማዎች መሀል በጎንደር ከተማ እና ዙርያው እየተፈፀሙ ስላሉ የእገታ ድርጊቶች በብዛት ይገኙበታል።
ጥቆማዎቹን ተቀብሎ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ማጣራት ሲያደርግ የነበረው የመሠረት ሚድያ ባልደረባ ይህን መረጃ አጠናቅሯል።
“ከተማዬን መልሱልኝ”
“ስለ ጎንደር ዝም አልልም” እና “ከተማዬን መልሱልኝ” የተሰኘ ንቅናቄ በጎንደር ከተማ ከሰሞኑ ተደርጎ ነበር፣ አላማው ደግሞ በከተማው ውስጥ እና በአካባቢው እጅግ እየተለመደ የመጣውን የእገታ ወንጀል ‘በቃ!’ ለማለት።
ከተለያዩ ምንጮች ማረጋገጥ እንደቻልነው አሁን ላይ ጎንደር ከተማ ውስጥ በየቀኑ ንፁሃን ይገደላሉ፣ ይታገታሉ።
ወላጅ የታገተ ልጁን እስከ 2 ሚሊዮን ብር መልሶ እየገዛ እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪዎች “ልመና እንኳን ስትወጣ የመንግስት አካል ነኝ ብሎ ይከለክላል። ቤተክርስቲያን በር ላይ ቆመህ ገንዘቡ አይሞላም። ያለህ አማራጭ የልጅህን ሞት መቀበል ይሆናል” ብለው በምሬት ይናገራሉ።
ጎንደር ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ “ህዝቡ ተማረረ፣ ከተማዋን ማን እንደሚያስተዳድራት አይታወቅም። በየቀኑ ቀብር እና ለቅሶ ነው። አባት የቤት እመቤት ሆነ፣ ወጣት በሙሉ ተሰደደ፣ ልጆች በስጋት ጭንቀት ዉስጥ ወደቁ” ብለው የሁኔታውን አስከፊነት አስረድተዋል።
“ግድያውም የከፋ ነው”
ከአራት ቀን በፊት ስሙ እንዲጠቀስ ያልተፈለገ አንድ ጎንደር ውስጥ ያለ የሰንበት ትምህርት ቤት የመዝሙር ክፍል ባልደረባ ከእናቷ እና ከቤት ሰራተኛቸው ጋር፣ በአጠቃላይ 3 ሴቶች ተገድለው እንዳደሩ የሰንበት ትምህርት ቤቱ ባልደረቦች ይናገራሉ።
“እባካችሁ፣ ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ልደታ ማርያም ብላችሁ ድምፃችንን ስሙን፣ መፍትሄ አሰጡን። ከእገታው በተጨማሪ ግድያውም የከፋ ነው” ብለው መላው ኢትዮጵያውያንን ተማፅነዋል።
“በጎንደር ከተማ ሰው በህይወት ወጥቶ እና ገብቶ መስራት አልቻለም። ሰው በየቀኑ ታፍኖ ይወስዳል፣ የተጠየቀውን ገንዘብ አልከፍል ያለ ይገደላል” ያሉን ሌላው የከተማው ነዋሪ ናቸው።
እንደ ምሳሌም ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንዲት እናትን ከነልጅዋ በለሊት ለማፈን ሲሞክሩ ፍቃደኛ ስላልሆኑ በግፍ በጎንደር ከተማ ቀበሌ 16 ላይ መገደላቸውን ያነሳሉ።
“ከተማዋን እያለሙ የነበሩ ብዙ ባለሀብቶች ወደ አዲስ አበባ ሄደዋል፣ ከጎንደር በአራቱም አቅጣጫ ተንቀሳቅሶ መስራት አልተቻለም። በአጠቃላይ ሰዉ የኑሮ ውድነት ከሚያሰቃየው በላይ በሰላም ወጥቶ መግባት አልቻለም” ብለዋል።
“እገታው ቤት ለቤት ሆኗል”
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ደጋግመው እንደሚሉት በፊት በፊት መንገድ ላይ ይታገት የነበረው አሁን ከፍ ብሎ ቤት ለቤት በጨለማ የሚደረግ ድርጊት ሆኗል።
“ትናንት እንኳን አንዲት የ4 ወይም የ5 አመት ልጅ ከቤቷ ግቢ ጨዋታ ላይ እያለች ጠፍታለች፣ የት እንደገባች እስካሁን ድረስ አይታወቅም” ያሉን ደግሞ ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።
መሠረት ሚድያ የጎንደር ከተማ አስተዳደርን በዚህ ዙርያ ያነጋገረ ሲሆን ለግዜው ስሜ እና የስራ ድርሻዬ አይጠቀስ ያሉ አንድ አመራር ለድርጊቱ የፋኖ ታጣቂዎች እና የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ በመጠቀም ላይ ያሉ ህገወጥ ግለሰቦች እና ቡድኖች ድርጊቱን እየፈፀሙ ናቸው ብለዋል።
“ከአንድም ሁለት ሶስት ግዜ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ድርጊቱን ፈፅመው ሲያዙ እና ምርመራ ስናደርግ ያገኘነው ውጤት የሚያሳየው ይህንን ነው” የሚሉት ሀላፊው ችግሩ ከባለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ከአካባቢው የፀጥታ አካላት አቅም በላይ እየሆነ እንደመጣ ይናገራሉ።
የፋኖ አመራሮች በበኩላቸው ድርጊቱን በእነርሱ ላይ በመለጠፍ እንቅስቃሴያቸውን ለማጠልሸት መንግስት የሚያደርገው ሙከራ ነው ብለው ይሞግታሉ።
“ይህን ድርጊት እኛም የምናወግዘው ነው፣ መንግስት በርካታ ሰዎችን እያገተ ይገኛል። ይህን በማስረጃ ማሳየት የምንችለው ጉዳይ ነው” ያሉት የፋኖ አመራሮች ችግሩን ለመፍታት እነርሱም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
በዚህ ሁሉ እሰጥ አገባ መሀል ግን የጎንደር ህዝብ “ከተማዬን መልሱልኝ” እና “አትግደሉን” እያለ ይገኛል።