የአቶ ንጉሱ የተለሳለሰ አስተያየት ግፈኞችና ዘረኞችን የሚያበረታታ ነው #ግርማካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

የቀድሞ የአማራ ክልል መንግስት ቃል አቀባይ፣ አሁን በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክረተሪ የሆኑት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ፣ “በለገጣፎ ከተማ የተወሰደውን የህገ ወጥ ቤቶች ማፍረስ እርምጃ ተክትሎ በቦታው ተገኝተን ከአመራሩ እና ከነዋሪዎች ጋር ተወያይተን ነበር። በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጉዳዩን የሚያጣራ አንድ ግብረ ሀይል ተደራጅቶ ወደ አካባቢዉ እንዲሰማራ አድርጏል። የዜጎችን ቅሬታ የማዳመጥ እና ህግን የማስከበር ተግባራት ሳይነጣጠሉ ይፈፀማሉ” ሲሉ በፌስ ቡክ ድህረ ገጻቸው ጽፈዋል።

በለገጣፎ በከተማዋ ባለስልጣናት የተፈጸመው ሰቆቃና ግፍ የተለያዩ ሜዲያዎች በስፋት የዘገቡት ሲሆን ከተለያዩ ማእዘናት ኢትዮጵያዊያን ድርጊቱን እያወገዙ ይገኛሉ። ሆኖም አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣  በሕዝብ ላይ የደረሰውን ግፍና በደል በአይናቸው አይተውም፣  ድርጊቱን የማዉገዝ ድፍረት አለማግኘታቸው ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። በከተማዋ አስተዳደሮች  የተፈጸመው ሕግ ወጥ ብቻ ሳይሆን አረመኔያዊ ድርጊትን ወደ ጎን በማድረግ፣  አቶ ንጉሱ ህገ ወጥ አድርገው ያቃረቡት ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎችን ብቻ መሆኑ ብዙዎችን አስከፍቷል።አሳዝኗልም።

በለገጣፎ የፈረሱ ቤቶችን ተከትሎ፣ እኩይ ተግባራቶቻቸውን ለመሸፋፈን ፣  የኦህዴድ አመራሮች የፈረሱ ቤቶች “ሕገ ወጥ” እንደሆኑና ቤቶቹን ሲያፈርሱ ሕግን የማስከበር ስራ እንደሆነ በስፋት ለመናገር ሞክረዋል። አቶ ንጉሱም የኦህዴድ ሃላፊዎችን ንግግሮች እንደ ወረደ በመቀበል ሳይሆን አይቀርም፣ ነዋሪዎቹን ሕግ ወጥ ቤት የሰሩ አድርገው ያቀረቡት።

የአቶ ንጉሱ የቀዘቀዘና ደካማ አስተያየት ብዙዎችን ያስቆጣ ሲሆን፣ አቶ ንጉሱ ሕወሃት የበላይ የነበረ ጊዜ፣ “ አንዱ ልጅ፣ ሌላው የእንጀራ ልጅ የሚሆንበት አሰራር መኖር የለበትም” በሚል እኩልነት እንዲሰፍን ያሳዩትን ድፍረት ፣ አሁን እርሳቸው በአራት ኪሎ ሲቀመጡ፣ እኩልነትን የሚረግጡት ኦዴፓዎች ሲሆኑ፣ የኦዴፓ ሃላፊዎች በኦሮሞ ክልል ኦሮሞዉ እንደ ልጅ ሌላውን ግን እንደ እንጀራን ልጅና ሁለተኛ ዜጋ ሲያዩ፣ አቶ ንጉሱ  ያንን የመቃወም ድፍረት በማጣት መለሳለስን መርጠዋል።

ወንጀልን የሚሰሩና ዜጎች ላይ ግፍ የሚፈጸሙ የመንግስት ባለስልጣናት፣ እነ አቶ ንጉሱ እንዳደረጉት፣ ምንም የማይባሉ ከሆነ፣ ወንጀልን ወንጀል፣ ግፍን ግፍ የማለት ድፍረት ከሌለ፣ ወንጀለንና ግፍን ማበረታታ ነው።አቶ ንጉሱ ያደረጉት ይሄንኑ ነው።

በአቶ ንጉሱ ደካማ አስተያየት ዙሪያ ፣ ጋዜጠኛ አያሌው መንበር፣ “ለሚመራው ህዝብ ቤት ሰርቶ መስጠት ያልቻለ ወይም ህብረተሰቡ ህግን ተከትሎ ቤት እንዲሰራ አሰራር ያልዘረጋ መንግስት፣መንግስት ሀላፊነቱን ስላልተወጣ ዜጎች አማራጭ ሲያጡ ገንብተው ግብር የሚከፍሉበትን ቤት “ህገ ወጥ ነው” ማለት ራስን አለመመልከት እና ህገወጥነት ነው” የአቶ ንጉሱ ንግግር የነቀፈ ሲሆን፣ “ በቤት ጉዳይ ህገወጡ መንግስት ነው!! ለዜጎች ቤት ገንብቶ ማቅረብ አልያም አማራጭ አሰራር ማቅረብ የመንግስት ግዴታ ነው።የመንግስት አፈቀላጤዎች ስራቸውን እንኳን ዘንግተው “ህገወጥ ቤት” ሲሉ ይውላሉ።ህገወጦቹ ግን እነርሱ ናቸው።” ሲል ሕግ ወጡ በስልጣን ላይ ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት እንደሆኑ ይገልጻል።

የአቶ ንግሱ ንግግር አሉታዊነቱ እንዳለ፣ በአንጻሩ ከሁለት ቀናት በፊት፣  የአዴፓ አመራርና የአማራ ክልላዊ መንግስት ምክትል ቃል አቀባይ የሆኑት ፣ አቶ መላኩ አላምረው፣ አቶ ንጉሱ ከሰጡት አስተያየት በጣም የተለየ ይዘት ያለው፣ ለሚሰማ ትምህርት ሰጪ መልእክት አስተላልፈዋል።

“ ሕግ ይከበር፤ ነገር ግን ሕግ የሚከበረው ሰዎችን በተለይም አቅመ ደካሞችን በማዋረድ አይደለም፡፡የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ፤ ነገር ግን የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው የሰውን ልጅ ተፈጥሯዊ መብት በመረጋገጥ አይደለም፡፡ከተሞች ተውበው ይገንቡ፤ ነገር ግን ከተማ የሚገነባው የግድ ሰፈርን በማፍረስና ሕዝብን ለጎዳና በመዳረግ አይደለም” ያሉ አቶ መላኩ “በሕግ የበላይነት ስም” በዜጎች ላይ ግፍና ሰቆቃ መፈጸም ሕግን ማስከበር ሳይሆን ሕግን መጣስ እንደሆነ ነው የገለጹት።