የለገጣፎ – ለገዳዲ ሕገወጥ ቤቶች መፍረስ የሚታወቁ ሐቆች – መንግስቱ አሰፋ

የለገጣፎ – ለገዳዲ ሕገወጥ ቤቶች መፍረስ ብዙ እያነጋገር ይገኛል። ጉዳዩን በሕግ እና ፍትሕ ዓይን ከማይታችን በፊት ስለቤቶች እስኪ የሚታወቁ ሐቆችን እናስቀምጥ።

~ቤቶቹ ገበሬዎች ተታለው በካድሬ በትንሽ ብር ከተገዙ በኋላ በደላሎች እና ኦሕዴድ (ኦዲፒ) ካድሬዎች ለነዚህ ቤት የሚፈስርባቸው ባላቤቶች በተቸበቸቡ መሬት ላይ የተገነቡ ናቸው። ከ1990ዎቹ ጀምሮ ማለት ነው። አንዳንዶቹ ከተማ አስተዳድሩ ከመቋቋሙ (1998ዓ.ም.) በፊት ነበሩ። ሕጋዊ የመሬት ባለቤትነት ካርታ ባይኖራቸውም የመብራት እና የዉሃ ውጪ አንዳንዶቹም ግብር ሁላ እየከፈሉ ነበር። መንግሥትም ለነዚህ ቦታዎች ካሳ መክፈሉን ይናገራል።

~ከጥቂት ወራት በፊት የኦሮሚያ ክልል መሬት አስተዳደር ቢሮ በፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ባደረገው ጥናት ከ 12000 በላይ ሕገ ወጥ ቤቶች መኖራቸውን እና ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቆ ነበር። የዚያ አካል የሆነው ነገር ነው እንግዲህ አሁን ቤቶቹን እንዲፈርሱ የማድረግ ሥራ እየሠራ ያለው።

~ቤቶቹን ማፍረስ ምናልባት ሕጋዊ መሠረት ሊኖረው ይችላል። ሕገወጥ ከሆነ ሕገወጥ ነው። ግን ፍትሓዊ ነው ወይ? ከጥቅሙ ጉዳቱ አያመዝንም ወይ? ሕግ በማስከበር የሚከሰተው ማኅበራዊ ቀውስ ከ collateral damage ገዝፎ የችግር መንስዔ አይሆንም ወይ? ፖለቲካውን አያጦዘውም ወይ? ሕፃናት እና ሴቶች፣ አቅመደካሞች፣ እርጉዝ እና አራስ እናቶች ፣ አዛውንት ውና መበላቶች ጎዳና ተዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ አይሆንም ወይ ብለን ስንጠይቅ የሕግ የበላይነት ማስከበር ሳይሆን በራሱ ዞሮ ትልቅ ችግር ይሆናል። ይህንን ችግር የፈጸሙ ካድሬዎች ዛሬ ወይ የትም አይገኙም ወይ እቅፋችሁ ውስጥ “የለውጥ አመራር” ሆኖ ሸገር ከትመዋል። እነሱ ላይ የኽ የሕግ ዱላ እንደማያርፍ እናውቃለን። ምስኪኑን ግን ሰላባ እያረጋችሁት ነው። ጩኸታቸው ውስጥ ሕመም አለ። እርምጃው ምንም ያህል ሕጋዊ ቢሆን ግን ፍትሐዊ ይሆናል ብሎ ማሰብ ይከብዳል።

በሌላ በኩል፥

~አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ፊጥ የሚልባችሁ፣ ከወከላችሁትን ሕዝብ አናት አልወርድ ያለ ፖለቲካ ቁማርተኛ እንዳለ ባትረሱ ጥሩ ነው። ይህ ዓይነት ሰው በሰው ሞት እና መከራ ተረማምዶ ቁማር የሚጫወት መሠሪ ሰው ነው። ትላንት ገበሬ ሲፈናቀል “የአክራሪ” ፖለቲካ ነው ብሎ ዝም ያለ አንኮላ ዛሬ ተነስቶ “ለጽድቄ ብዛት ቆዳዬ ጠበበኝ” የሚል ግብዝ ነው። “እነሱ” ብሎ የወል ማንነት የሚሰጥ እንከፍ “ብሔርን መሠረት ያረገ ጥቃት” ፣ “ሌላውን የማፅዳት ዘመቻ” እያለ “doomsday prophecy”ውን ያዥጎደጉዳል። ዋልታ ቴሌቪዥን ላይ ካወሩ
ሰዎች ግማሽ ያህሉ አማርኛ እንኳን መናገር ስለማይችሉ በትርጉም ነው ዋይታቸውን ያሰሙት። እና “የናት ሌባ ልጇን አታምንም” ይላል አገራዊ ብሂሉ። እንዴት ብላ ትመን? ሰው ሁሉ ልክ እንደሷ ስለሚመስላት የልጇን innocence እንኳን አትቀበልም። በሌላ በኩል ደግሞ “በኔ ወጥታ” ብላም ትፈራለች እና ነጋ ጠባ “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” እያለች ታዜማለች። የሕይወት ዜማዋ መታመን ሳይሆን “ቅጥፈት” ነው፤ ልክ እንደዚህ ግብዝ የፖለቲካ ነጋዴ።

አለልህ ደግሞ “እሰይ” እያለ የደስታ ከበሮ የሚደልቅ ዥልጥ የቂም ፖለቲካ አራማጅ። ከወለደች 3 ቀኗ የሆነች አራስ እናት ቤቷ ፈርሶ ጎዳና ላይ ሸራ ተወጥሮላት ስትታረስ ምንም የማይሰማው።

በመጨረሻም ለODP

ግትርነታችሁ እንዳይሰብራችሁ ተጠንቀቁ። ሕግን የማስከብር ሥራችሁ ሌላ የማይሽር ቁስል ባይፈጥር ጥሩ ነው። ነገርየው ከcollateral damage በእጅጉ ይበልጣል። አዲስ ማኅበራዊ ቀውስ እየፈጠራችሁ መሆኑን አትርሱ። እኛ እንድሆንን በተፈናቃይ ብዛት ከዓለም አንደኛ ስለሆንን እና ውድድር ስለሌለብን ሌላ አንጨምር። እኛ እንደሆንን እናንተን አንቅሮ ለመትፋት የዓይን ሽፋሽፍት ቦታ አይቀይሩም። ትላንት “ጀንሆይ” “ሥዩመ እግዚአብሔር” ብለን ያመለክናቸውን ሲነጋ “ሌባ” ‘ምንል ሰዎች ነን።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሪ ያልታደለ ሕዝብ ነው። በራሱ ፖለቲከኞች ቁማር የተበላ፣ ልጅ አስተምሮ በመኃይም የተመራ፣ ልጅ ለዳር ድንበር ሰጥቶ ተመልሶ በነሱ የተወጋ ምስኪን ሕዝብ ነው። ችጋሩ አያድርስ ነው። በመንግሥታት የተገፋ፣ በኢትዮጵያዊያን ቅዥቢ ፖለቲከኞች አንድ ትውልድ ካጣ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያልሞላው፣ ሁሌ ያልተጠበቀ መንግሥታዊ መቅሰፍት የሚያስተነግድ ሕዝብ ነው። ነገር ግን የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ እናንተ ይህንን ቀፋፊ ታሪክ ምዕራፍ ዘግታችሁ አዲስ ምዕራፍ ልትከፍቱ ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባችሁ ሰዎች ናችሁ። For some reason እናነትን ግን አምኗችኋል። ያሻግረኛል ብሎ ሥማችሁን እስከመነቀስ ደርሷል። ተልዕኮ መስጠቱ ነው እንግዲህ። ስለዚህ ይህንን ተልዕኮ የሚመጥን ዕቅድ አውጥታችሁ ሥሩበት እንጂ በእልህ ተነሳስታችሁ ቤት አታፍርሱ። የሕግ የበላይነት በሚል ሌላ ቀውስ አትፍጠሩ። ይኸንን ለማስተከከል የተሻለ መንግድ እና አመቺ ጊዜ ይኖራል በርግጠኝነት። ግትርነት አይሠራም። ከሰማይ በታች የማንደራደረው ነገር ሊኖር አይገባም። የማንወያይበት እና በውይይት የማይፈታ ነገር የለም። ፖለቲካ የማመቻመች (art of compromise) ብልኃት ነው እና የምትሥሩት ነገር ሕጋዊነት ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊነት እና ሰብዓዊነት ስሜት (humane + sensibility)ም ያለው ይሁን። ለድኃ ቤት የሠራ ቡድን ሌላ ቤት አልባ መፍጠር፣ ጎዳና ተዳዳሪን ከመንገድ ዳር አስነስቶ የሕይወት ተስፋቸውን ያደሰ መሪ ሌላ የ3,4,5,6,7, ዓመት እንቦቅቅላ ከሞቀ ቤት እና ከትምሕርት ቤት እያስወጣ ጎዳና ላይ ሊያሰጣቸው አይገባም። ይኸ ተቀባይነት የለውም። ከብዙ አቅጣጫ የሙጃ ፖለቲከኞች (aspirant power hungry, cult leaders, አክራሪ ፖለቲከኛ፣ sufferers of the bygone delusional nostalgia) ግፊት እንዳለባችሁ ይገባኛል። ግን እነሱን ሳይሆን አብዛኛው silent majority እናንተን ተስፋ ያረጋል። ምስኪኑ ገበሬ እናነትን ይጠብቃል፣ ተስፋ ያረጋል። ይህንን ተሥፋ ውኃ አትቸልሱበት።