የዳያስፖራ አባላት የገንዘብ፣ ጉዞ እና መዋእለ ንዋይ እቀባ ዘመቻ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጀምረዋል!

የዳያስፖራ አባላት የገንዘብ፣ ጉዞ እና መዋእለ ንዋይ እቀባ ዘመቻ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጀምረዋል!

ውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሲቪል ማኅበራት «ግፈኛ አገዛዝ» ያሉት መንግሥት ላይ የገንዘብ ተጽእኖ ለማሳደር ዘመቻ ጀምረዋል። ማኅበራቱ ዘመቻቸው፦ ኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው ብልጽግና መንግሥት ይፈጸማል ያሉትን ኢ-ፍትኃዊነትና ዘረኝነት በመቃወም፤ ትኩረቱ ፍትሕ ላይ ያተኮረ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራው ማኅበረሰብም ወደ ሀገር ቤት የሚልከውን ገንዘብ በባንኮች እንዳይጠቀም ጥሪ አስተላልፈዋል። ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚያደረጓቸውን ጎዞዎች እንዲያቋርጡ እና መዋእለ ንዋይ ፍሰት (ኢንቨስትመንት) ለማደርግ የሚደረጉ ሂደቶች በአጠቃላይም መቋረጥ አለበት ብለዋል።

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚንሥትር አህመድ ሽዴ ባቀረቡት ዘገባ፦ የፌድራል መንግሥት የበጀት ጉድለት እንደገጠመው ይፋ አድርገዋል።የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሀገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ 28 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ ማድረሱን ዐሳውቀዋል ።

ሚንስትሩ ጉድለት ያሉትን ለመሸፈንም ከአገር ውስጥ 194.6 ቢሊዮን ብር በብድር መንግስት መውሰዱን ገልጸዋል። «ብድሩም የተገኘው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር፣ ከትሬዠሪ ቦንድ እንዲሁም ከትሬዠሪ ቢል ነው።ካሉት የፋይናንስ ተቋማት 194.6 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ሬይዝ ተደርጓል»ም ብለዋል ። መንግስት ከፍተኛ የገንዘብ ችግር እንደገጠመው፤ የኑሮ ውድነቱም በከፍተኛ ደረጃ ማኅበረሰቡን እንዳማረረው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።