የኑሮ ውድነቱ እየባሰ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም

በኢትዮጵያ ከቀን ቀን እየተባባሰ የሄደው የኑሮ ውድነት የምግብ፣የፍጆታ፣የቁሳቁሶች፣የትራንስፖርትና የአገልግሎት ዋጋ ግሽበት አብዛኛውን ዜጋ አቅም አሳጥቷል።በተለይ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የኑሮ ውድነትን መቋቋም የማይችሉበት ደረጃ ላይ ከደረሱ ሰንብቷል።  የቤት ኪራይ ዋጋ እና የተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያ በየጊዜው መናር ኑሮን እጅግ አክብዶታል። መንግሥት  ለዓመታት የዘለቀውን የዋጋ ንረት ለማቃለል ይረዳሉ ያላቸውን የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰዱን ቢያሳውቅም የኑሮ ውድነቱ እየባሰ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም ።

ችግሩ የከፋ ደረጃ ላይ በደረሰበት በአሁኑ ወቅትም መንግሥት ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥያቄ እየቀረበለት ነው። የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫና ማድረጉን የሚገልጸው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፈደሬሽን በምህጻሩ (ኢሰማኮ) በቅርቡ መንግስት ችግሩን መቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስድ አሳስቧል። የሠራተኛው ደሞዝ የአሁኑን የገበያ ዋጋ ሊቋቋም በማይችልበት ደረጃ ላይ ነው የሚለው አንድ ሚሊዮን አባላት ያሉት ኢሰማኮ አስቸኳይ ያላቸውን የበኩሉን መፍትሄዎችም ከሦስት ሳምንት በፊት በተከበረው በዓለም የሠራተኞች ቀን

በአደባባይ ሰልፍ ለማቅረብ ቢያቅድም ሰልፉ ባለመፈቀዱ ሳይሳካላት ቀርቷል። ሆኖም ኮንፈደሬሽኑ ጥረቱን በመቀጠል ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የገንዘብ ሚኒስትርን ጨምሮ ለሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከታቸዋል ላላቸው ባለስልጣናት የችግሩን አሳሳቢነት በመግለጽ በአስቸኳይ ሊተገበሩ ይገባቸዋል ያላቸውን መፍትሄዎች ያካተተ ደብዳቤ መላኩን አስታውቋል።