ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ሽብር አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ሽብር አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ሰሜን አሜሪካ
ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ. ም
የቁርጥ ቀን አርበኞችን በማዋከብ እና ”ሰላም ይፅና” በሚል መፈክር ዘላቂ ሰላም አይገኝም

ትርጉም አልባ በሆነ ጦርነት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን በጦርነት ማግደው፤ ከአራት ሚሊዮን ያለነሱ የአማራ፣ የትግራይና፣ የአፋር ንጹሃን ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅለው፤ ወደ ትሪሊዬን የሚጠጋ ገንዘብ አፍስሰው፤ በእብሪትና በማን አለብኝነት ጦርነት ሲመሩ የነበሩ መሪዎች፣ በአደባባይ መልካም ስራ እንደ ሰሩ ዜጎች ሲሸላለሙና የስልጣን መንበራቸውን በሰላም ስም በህዝብ ልጆች ደም ላይ ሲያደላድሉ ከማየት በላይ የሚያንገፈግፍ ነገር ሊገኝ አይችልም፡፡ የነገድ ፖለቲካ የሚያራግበው መዋቅራዊ ስርዓት ሳይቀየር፣ ህገ መንግሥቱ ሳይከለስ፣ ወንጀለኞች ለፍርድ ሳይቀርቡ፣ ተጠያቂነት ሳይሰፍን፣ ገብሱ ከእንክርዳዱ ሳይለይ፣ የጥላቻና የበቀልን መርዝ የሚተፉ የኦህዴድ/ብልጽግና አመራሮች ምላስ ሳይገራ ”ጦርነት ይብቃ ሰላም ይፅና” በሚል መሪ ቃል የሽልማት ፕሮግራም አዘጋጅቶ ከነአጨብጫቢዎቻቸውና ተለጣፊ አጋፋሪ ባለሟሎቻቸው ጋር ሲሸላለሙ ማየትን የመሰለ የኢትዮጵያውያን ልብ የሚያደማ ትእይንት ሊኖር አይችልም።

የኦህዴድ/ብልጽግና ስርዓት የስግብግብነቱ ጥግ ወሰን ስለሌለው አማራን አዳክሞ ሌሎች ክልሎችን በመሰልቀጥ ሀገሪቱን ማፍረስ ወይም በራሱ አምሳል መቅረፅ ተቀዳሚ ዓላማው ነው፡፡ ይህን ዓላማውን ሊያደናቅፈው የሚችል ማንኛውንም ኃይል ለማጥፋት ቀን ከሌት እየባዘነ ይገኛል፡፡ በቅርቡ የአቶ ግርማ የሺጥላን ሞት ተከትሎ በፋኖዎችና በልዩ ኃይሎች ላይ ትጥቅ ለማስፈታት የሚደረገው ዘመቻ አማራውን ለማዳከም ከተያዘው እቅድ አንዱ አካል ነው፡፡ አማራን ከትጥቁ ከመለየት የሚጠባ ህፃንን ከእናቱ መለየት ይቀላል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የፋኖና የአማራ ልዩ ኃይል ከአፋር ልዩ ኃይል ጋር በመሆን የሀገር መከላከያ ሰራዊት አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ጊዜ የኦህዴድ/ብልጽግና ነፍሱንና ወንበሩን ያተረፉለት እነዚህ ባለውለታዎች ነበሩ፡፡ ዳሩ ግን ውለታ-ቢሱ የኦህዴድ/ብልጽግና ስርዓት ወንበሩን ካደላደለ በኃላ እነዚህን ኃይሎች ማጥፋት ስለፈለገ ዘመቻ አውጆባቸዋል፡፡

ይህንንም በመከላከያ ኢታማጆር ሹም ብርሃኑ ጁላ የሚመራ አማራውን ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ በኃይል ለማስፈፀም መከላካያው ኦፕሬሽን እንደመጀመር አውጇል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በበኩሉ ማንኛውም መስዋእትነት ተከፍሎም ቢሆን አማራው ትጥቅ ይፈታል ሲልም ተደምጧል። በአማራ ህዝብ ላይ ጦርነት አውጆ፤ ጋዜጠኞችን፣የማህበረሰብ አንቂዎችንና ሰላማዊ የፖለቲካ መሪዎችን እስር ቤት አጉሮ፣ ”ጦርነት ይብቃ፣ ሰላም ይፅና” እያሉ መደስኮር፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ማላገጥ ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ትርጉም ሊሰጠው ይችላም። እንዲህ አይነት ተውኔትና ሴራ እውነተኛና ዘላቂ ሰላምን በኢትዮጵያ የሚያመጣ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያ በታሪኳ በዚህ ደረጃ አይናቸውን በጨው ያጠቡ በሞራል የዘቀጡ የፖለቲካ መሪዎችን አስተናግዳ አታውቅም።
ስለዚህ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ሥሙን እንጂ ምግባሩን ሳይቀይር የጥፋት ፖለቲካ የሆነውን የነገድ ፅንፈኝነት መርዙን እየተፋ ላለፉት 32 ዓመታት፤ ለሚሊዮኖች የሰቆቃ፣ የግፍ ኑሮና፣ መገፋት፣ ምክንያት የሆነውና አሁን ለደረስንበት ሀገራዊ ውድቀት ተጠያቂ የሆነውን፤ በሙስናና፣ በደም፣ የተጨማለቀ ታሪክ ያለውን የኢህአዴግ/ብልፅግና ፖለቲካ ስርዓት፤ በቃኝ ብሎና አምርሮ በመታገል፣ ከራሱ ጫንቃ ላይ የማስወገጃው ጊዜ አሁን እንደሆነ ያምናል። በመሆኑም ባልደራስ የሚከተሉትን የትግል ጥሪዎች ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ያቀርባል።

1ኛ. የአማራው ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በመሆን የጀመረውን ሁለገብ ትግሉን አጠናክሮ በመቀጠል የእራሱንና የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር የታሪክ አጋጣሚ የጣለበትን ኃላፊነት ዳር ለማድረስ ትግሉን ማፋፋም ይጠበቅበታል፤
2ኛ. የኦህዴድ/ብልጽግና እንዲሁም የህውሃት ኃይሎች በጋራ በአማራ ህዝብ ላይ ሊዘምቱበት እየተዘጋጁ ይገኛሉ። ስለሆነም የአማራው ህዝብ በየዘመኑ የሚከሰቱ ጀግኖችን እያስበላ እንዳይቀጥል፣ ይህንን ትግል ህዝባዊ በማድረግ ስርዓቱን በሰላማዊ መንገድ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ይኖርበታል፤
3ኛ. ነባር የሆኑትን ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ተቋማትንና እሴቶችን አፈራርሶ የኢትዮጵያን ህልውና የመሻር ህልሙን እውን ለማድረግ ሌት ተቀን እየሰራ ያለውን የኦሮሙማውን ኃይል ሁሉም ኢትዮጵያዊ አምርሮ መታገያው ጊዜ አሁን ነው፤

4ኛ.በኑሮ ውድነት እየተለበለበ ያለውና በዝምታ፣ በሀገሩ አስከፊ ነባራዊ ሁኔታ እየተብሰለሰለ ያለው የአዲስ አበባ ህዝብ፤ በኦህዴድ መራሹ መንግሥት ከፍተኛ ሁለ ገብ የመሰልቀጥ ስጋትና ጫና ውስጥ ያለ ቢሆንም፣ የተፈጠረበትን ጫና በመቋቋምና ከፍርሃት ቆፈን በመላቀቅ፤ ከምን ጊዜውም በላይ አስከፊ የሆነ ከፋፋይና ሀገር አፍራሽ የሆነን አላማን አንግቦ የሚንቀሳቀሰውን የኦህዴድ/ብልፅግና የህወሓትን ጥምረት፤ በሰላማዊ መንገድ ታግሎ የሚጥልበት ጊዜው አሁን መሆኑን አውቆ ተግባራዊ የሆነ፣ የተደራጀ ሰላማዊ ተቃውሞን ማሰማት መጀመር ይኖርበታል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
ሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ
ሚያዚያ 25/2015
አዲስ አበባ