“አዲስ አበባ መግባት አልቻልንም፣ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠርን ነው”- መንገደኞች

ከሰሞኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ በተለይ ከሰሜን እና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች የተነሱ መንገደኞች ሸኖ ከተማ ሲደርሱ እገዳ እንደተደረገባቸው እና ወደ አዲስ አበባ መግባት እንዳልቻሉ የሚደርሱኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ትናንት ይህ ችግር ያጋጠማቸውን አንዳንድ ሰዎች በስልክ አናግሬ ነበር። ያሉኝ እንዲህ ይቀርባል:

“ከደሴ ተነስተን ሸኖ ስንደርስ ከመኪና አስወርደው አሰለፉን። ከዛም የአዲስ አበባ መኖርያ ፈቃድ ያላቸውን አሳለፉ፣ ሌሎቻችን ግን ከለከሉ። አሁን ተመልሰን ደብረ ብርሀን ከተማ እንገኛለን። ለምን እንደሆነ እንኳን በቅጡ አልነገሩንም፣ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠርን ነው።”

“ትናንት ከሰዐት 10:45 ላይ መሳርያ የያዙ የፀጥታ አካላት ከሸኖ መልሰውናል። እናቶች፣ ህፃናት እንዲሁም ምንም ብር የሌላቸው ጭምር ነበሩ። ደብረ ብርሀን ብር አዋጥተን እንዲያድሩ አርገናል፣ ከዚህ በሗላ ግን ምን እንደሚሆን አናውቅም።”

“መሳርያ የያዙት ፈታሾች እኔ የነበርኩበት ዶልፊን መኪና ውስጥ የነበረች አንዲት ዘውዲቱ ሆስፒታል ለህክምና የምትሄድን እናትን ጭምር መልሰዋል፣ የቀጠሮ ወረቀት ስታሳያቸው መሳርያ አውጥተው ነው የሚያስፈራሩት። በዚህ ምክንያት ደብረ ብርሀን እና ደብረ ሲና ብዙ ህዝብ ተጉላልቶ ይገኛል።”

ምንጭ – ኤሊያስ መሰረት