በአዲስ አበባ የነዋሪዎች ዲጅታል መታወቂያ ሳይታገድ በፊት በወሳኝ ኩነት ሰራተኞች እስከ ሰባት ሺህ ብር ይሸጥ ነበር

በአዲስ አበባ ከወራት በፊት የተጀመረውን ዲጅታል መታወቂያ በተለይ በወረዳ ደረጃ ባሉ አዲስ አበባ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ሠራተኞች እስከ ሰባት ሺሕ ብር ሲሸጥ እንደነበር አዲስ ማለዳ ከአንድ ወር በላይ ባደረገችው ማጣራት አረጋግጣለች።

አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ አስተዳደር ስር በተለያዩ ወረዳዎች ከአንድ ወር በላይ በፈጀ ጊዜ ባደረገችው የማጣራት ሥራ፣ አዲስ የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት ከተቋረጠበት ሚያዝያ 21/2014 በፊት በአምስት ክፍለ ከተሞች ተጀምሮ የነበረው ዲጂታል መታወቂያ በወሳኝ ኩነት ሠራተኞችና በአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል በሚፈጸም የቤተሰብ አካቶ ስምምነት ሲሰጥ እንደነበር አረጋግጣለች።

የዲጂታል መታወቂያ ሕጋዊ መስመር ተከትለው ማውጣት ለማይችሉ ሰዎች ሲሠራ የነበረው የአንድ አዲስ አበባ ነዋሪ በሆነ አባወራ እና በወሳኝ ኩነት ሠራተኞች ስምምነት ሲሆን፣ ስምምነቱ የሚፈጸመው በሕገ ወጥ መንገድ መታወቂያ የሚሠራለት ሰው አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው አባወራ የቤተሰብ አካል አድርጎ በመመዝገብ መሆኑን ለመመልከት ተችሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነ አንድ አባወራ ወይም እማወራ ከወሳኝ ኩነት ሠራተኞች ጋር በሚፈጥሩት ስምምነት እነሱ እንደሚሉት ‹በሕጋዊ መንገድ፣ ሕጋዊ መታወቂያ› የማውጣት ሥራውን ሕጋዊ ለማስመሰል መታወቂያ የሚወጣለት ሰው የዚህ አባወራ ወይም እማወራ የቤተሰብ አካል ሆኖ በወሳኝ ኩነት መዝገብ ላይ እንደሰፈረ ይቀጥላል። ይህ ዓይነቱ ሥራ የሚፈጸመው የወሳኝ ኩነት ሠራተኞች አስቀድመው ለዚሁ ተግባር ተስማምተው ባስቀመጧቸው ነዋሪዎች ሲሆን፣ በቤተሰብ መረጃ ምዝገባ ላይ የሌላቸውን የቤተሰብ ቁጥር ቀድመው የሚያስመዘግቡ ነዋሪዎች አሉ።

በወሳኝ ኩነት ሠራተኞችና በአዲስ አበባ ነዋሪ ስምምነት መሠረት የሚወጣው መታወቂያ ከቅርብ ወራት በፊት የተጀመረው ዲጂታል መታወቂያ ብቻ ሳይሆን፣ ወረቀት መታወቂያም በዚሁ መንገድ እንደሚሠራ አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። በተመሳሳይ ሁኔታ ‹በሕገ ወጥ በመንገድ ሕጋዊ መታወቂያ› የሚሉትን የወረቀት መታወቂያ ለማውጣት፣ መታወቂያ የሚሠራለት ሰው በትንሹ ሦስት ሺሕ ብር ጉዳዩን ለሚያስፈጽሙት ወሳኝ ኩነት ሠራተኞች መክፈል ይጠበቅበታል።

አዲስ ማለዳ አዲስ የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት ከመቆሙ በፊት የጀመረችው የማጣራት ሥራ ላይ የታዘበችው ሌላው ጉዳይ፣ ከውጭ ሆነው መታወቂያ ፈላጊዎችንና የወሳኝ ኩነት ሠራተኞችን የሚያገናኙ ደላሎች የቤተሰባቸው አባል አድረገው ሰዎች መታወቂያ እንዳገኙ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችንም ያፈላልጋሉ። ይሁን እንጂ የወሳኝ ኩነት ሠራተኞች በየሚሠሩበት ወረዳ ለዚህ ተግባር የሚተባበሯቸውን ሰዎች አንዳንዶቹን በክፍያ አንዳንዶቹን ደግሞ ያለ ክፍያ መታወቂያ የሚሠራለትን ሰው የቤተሰብ አባል የማድረግ ፈቃደኝነታቸውን ይጠየቃሉ።

በአዲስ አባባ ሕገ ወጥ የመታወቂያ ሥርጭትን ይከላከላል ተብሎ የታመነበት የዲጂታል መታወቂያ፣ በአምስት ክፍለ ከተሞች መሰጠት መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ማሳወቁን አዲስ ማለዳ ከኹለት ወር በፊት መዘገቧ አይዘነጋም።

አገልግሎቱ የተጀመረው በአራዳ፣ በቦሌ፣ በየካ፣ በጉለሌ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሕገ ወጥ የመታወቂያ ሥርጭትን እና አሠራርን ይቀርፋል ተብሎ እምነት የተጣለበት የዲጂታል መታወቂያ ማተሚያ ማሽን እና መታወቂያ የመስጠት ሥራ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።
በመዲናዋ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች የራሱን ሠራተኞች ጨምሮ በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ 48 ሰዎች እጅ ከፍንጅ መያዙን የመረጃ ኤጀንሲ መግለጹ የሚታወስ ነው።