ኢትዮጵያ እና ቱርክ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት እና በወንጀል ጉዳዮች ላይ የጋራ የሕግ ትብብር ለማድረግ ተስማሙ

ኢትዮጵያ መንግስት እና በቱርክ ሪፐብሊክ መካከል በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት እና በወንጀል ጉዳዮች ላይ የጋራ የሕግ ትብብር ለማድረግ የሚያስችሉ ሥምምነቶች ተፈርመዋል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፍትህ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደዉ የተመራ የልዑካን ቡድን አንካራ ቱርክ የገባ ሲሆን፤ የልዑካን ቡድኑ በቱርክ የፍትህ ሚኒስቴር በመገኘት በኹለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡

በዉይይቱም የቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት የፍትህ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ያኩፕ ሞጉል በቱርክና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መሆኑ እና በፍትህ እና በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ትብብሮች አስፈላጊና ወንጀልን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸዉ መሆኑን ገልፀዋል።

አክለውም በኹለቱ አገራት መካከል የተለያዩ ትብብሮች ሲደረጉ የቆየ ቢሆንም፤ በዚህ ደረጃ የፍትህ ትብብሮች ሰነድ መፈረማቸዉ ግንኙነቱን የበለጠ ሕጋዊ መሰረት የሚሰጠዉ መሆኑን ጠቅሰዉ በኹለቱ አገራት የሚፈለጉ ወንጀለኞችም በማንኛዉም ጊዜ በፍጥነት ተላልፈው መሰጠት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

አለምአንተ አግደዉ በበኩላቸዉ፤ ኢትዮጵያ ከብዙ አገራት ጋር በወንጀል ጉዳዮች ላይ በትብብር እንደምትሰራ፣ ከቱርክ መንግስት ጋር በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚደረገው የጋራ ሥምምነትም በኹለቱ አገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግረዉ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቱርክ በተለያዩ መንገዶች የኢትዮጵያ አጋር መሆኗን ማሳየቷን ገልፀው፤ በአቅም ግንባታ ዙሪያ ከቱርክ መንግስት ጋር በትብብር ለመስራት ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን፤ ቱርክ በሽብርተኛ ቡድኖች የደረሰባትን አሳዛኝ ጉዳቶች ኢትዮጵያ እንደምትገነዘብና በዚህም ከቱርክ መንግስትና ህዝብ ጎን እንደምትቆም፣ አገራችን ሽብርተኞችን እንደምታወግዝና ሽብርተኝነት እንዳይስፋፋ ጠንክራ እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡

በኹለቱ ወገኖች መካከል ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በቀጣይ በጋራ በቅርበት በመስራት ትብብሩን በማጠናከር ረገድ ትኩረት እንደሚሰጥ የኹለቱም አገራት ተወካዮች መግለፃቸውን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በመቀጠልም በኹለቱ አገራት መካከል በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ለማድረግ የሚያስችሉ ኹለት ሥምምነቶች በፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደዉ እና በቱርክ ፍትህ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሚስተር ያኩፕ ሞጉል አማካኝነት ተፈርሟል።