የመንግስቱ ኃይለማርያም ምክትል የነበሩት ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ አረፉ

ከሰላሳ ዓመታት በፊት በነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ በ81 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

የቀድሞው መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማሪያም ምክትል በመሆን የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ፣ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ለ20 ዓመታት ያህል በእስር ቆይተዋል።

ቢቢሲ ከቤተሰባቸው ለመረዳት እንደቻለው ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐ የልብ ሕመም የነበረባቸው ሲሆን ለዚህም በአገር ውስጥና በውጪ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት የነበሩት ፍሰሐ ሕይወታቸው ያለፈው አርብ ሚያዚያ 28/2014 ዓ. ም. እኩለ ሌሊት አካባቢ ሲሆን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እሁድ ሚያዚያ 30/2014 ዓ. ም. በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ተገልጿል።

ከእስር ከወጡ በኋላ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ስላለፉባቸው ሁኔታዎች የሚተርክ “አብዮቱና ትዝታዬ” የሚል መጽሐፍ ያበረከቱ ሲሆን፣ በዚህም “ደርግ በወሰዳቸው በጎ ዕርምጃዎች እንደምደሰት ሁሉ በማወቅ፣ በድፍረት፣ ባለማወቅና በስህተት ለተፈጸሙት ደግሞ ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ በበኩሌ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለው ነበር።

ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐ ከመጀመሪያው መጽሐፋቸው በተጨማሪ ሁለተኛ መጽሐፍ በማዘጋጀት ላይ እንደነበሩ ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ትግራይ አድዋ ውስጥ የተወለዱት ሌፍተናንት ኮሎኔል ፍሰሐ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአደዋ ንግሥተ ሳባ እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃን አዲግራት ውስጥ በሚገኘው አግአዚ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

በተጨማሪም አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን፣ ከዚያም በኋላ ወደ ሐረር ጦር ትምህርት ቤት ገብተው ከሰለጠኑ በኋላ በክብር ዘበኛ ውስጥ ገብተው በንጉሡ ቤተ መንግሥት ውስጥ ተመድበው አገልግለዋል።

ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐ ወደ አሜሪካ በመሄድ ከፍተኛ ወታደራዊ ሥልጠና ወስደዋል። ከዚህ በሻገርም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ተከታትለዋል።

ንጉሡን ከሥልጣን ያስወገደው ሕዝባዊ አብዮት ሲፈነዳና በደርግ አማካይነት ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ሲመሠረት ከጦር ኃይሉ ተወጣጥተው የአመራርነት ቦታውን ከያዙት የወቅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ነበሩ።

ከዓመታት ቆይታ በኋላ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ሲመሠረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪም ምክትል በመሆን የአገሪቱ ሁለተኛ ሰው ለመሆን በቅተው ነበር።

ከአማጺያኑ ጋር ለ17 ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የቆየው አስተዳደራቸው እየተዳከመ መጥቶ ፕሬዝዳንቱ አገር ለቀው ከተሰደዱ በሳምንታት ውስጥ የአማጺያኑ ስብስብ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የኢሕዲሪ መንግሥት ፍጻሜ ሆነ።

ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐን ጨምሮ በአገር ውስጥ የተገኙት የቀድሞው መንግሥት ባለሥልጣናት በአገሪቱ ውስጥ በተፈጸሙ ጭፍጨፋዎችና በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ተከሰው ለዓመታት በተካሄደ የፍርድ ሂደት እስር ተፈርዶባቸዋል።

ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታም ለ20 ዓመታት በእስር ካሳለፉ በኋላ ከ10 ዓመት በፊት በይቅርታ መለቀቃቸው ይታወሳል።