የትግራይ ሕዝብን የመታደግ ግዴታ የፌዴራል መንግስቱ አለበት #ግርማ_ካሳ

የዶ/ር ደብረጽዮንን መግለጫ ተመልከቼ አዘንኩኝ። ሕወሃት የለዉጡ አካል መሆን እንደማይችል፣ በሕወሃት ውስጥ ያሉ ለውጥ ፈላጊ ሃይሎች በውስጠ ሕወሃት ትግል እንደተሸነፉ፣ ክልሉ በኢትዮጵያው ቢንላድን፣ ጌታቸው አሰፋ፣ በነ ስብሃት ነጋ ቁጥጥር ስር ሙሉ ለሙሉ መሆኑ ተሰማኝ። የትግራይ ህዝብ ሰቆቃና ችግር እንደሚራዘም ታየኝ። በዚህ ምክንያት የፌዴራል መንግስት የትግራይን ሕዝብ ከሕወሃት መታደግ አለበት ወደሚል አቋም እየድረስኩኝ ነው።

“እንዴት? ” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ከቀላል መንገዶች ተጀምሮ ከበድ ወዳሉ እርምጃዎች መሄድ ይቻላል።

– አንደኛ – ሕወሃትን ከኢሕአዴግ ማባረር ያስፈልጋል። ሕወሃት ለፌዴራል ሕግ የማትገዛ ከሆነ፣ የፌዴራል መንግስት ወይም የገዢው ፓርቲ አካል የምትሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ያንንም እርምጃ አዴፓ፣ ኦዴፓና ደሃዴን በምርጫ ቦርድ ሕግ መሰረት መውሰድ ይችላሉ።

– ሁለተኛ – የሕወሃት አመራሮችን የባንክ አካዉንትና ንብረት ማገድ ቀጣዩ እርምጃ ሊሆን ይችላል።

– ሶስተኛ – ሕወሃት አሁንም አልሰማም ብላ፣ በትግራይ ተወስና ሕዝቡን ማሸበሩን ከቀጠለች፣ ሕወሃትን ሕገ ወጥ እየሆነ እንደሆነ በግልጽ በማሳወቅ፣ ለመጨረሻ ጊዜ ማስጠንቀቂያ በመስጠትና ሽማግሌዎች ሄደው አመራሮቹን እንዲያግባቧቸው በመላክ የሰላም ጥረት ማድረጉ ፣ በቀጣይነት ሊከተል ያለው እንዳይከሰት ይረዳል።

– አራተኛ – ሕወሃት ሰላም፣ እርቅን፣ ንግግር ፣ የሽማግሌዎች ጥሪ እምቢ ብላ አልሰማም ካለች፤ ሕወሃትን ሕገወጥ ድርጅት እንደሆነ በመደንገግ፣ የፌዴራል ጦርን  ወደ ትግራይ በመላክና የክልሉ ሕዝብ የራሱን አመራር እስኪመርጥ ድረስ በፌዴራል ስር ማድረግ የመጨረሻው አማራጭ ይሆናል። (ልክ የሶማሌ ክልልን ሕዝብ ከአብዲ ኤሊ ነጻ እንደተደረገው)

በዚህ መልኩ የትግራይን ሕዝብ ነጻ ማውጣት ይቻላል።

አንድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉም መዘንጋት የሌለብን ነገር፣ የትግራይ ሕዝብ ከማንም በላይ የሕወሃት ግፍና መከራ የተቀበለ፣ በሕወሃት ምክንያትን እንዲጠላ የተደረገ ሕዝብ ነው። በመሆኑም ሕወሃትን ከሕዝቡ መለየት መቻል አለብን። በሕወሃት ምክንያት ትግሬዎችን ሁሉ መጥላት የሕወሃትን ስራ እንደመስራት ነው የሚቆጠረው። በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ትግሬዎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ በማንኛውም የአገሪቷ ክፍል በሰላም መኖር እንዲችሉ የማያደርጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች አለማድረግ ብቻ ሳይሆን፣  ሌሎች ሲያደረጉም በጭራሽ መታገስ የለብንም። በጅምላ መክሰሰና መጥላት ዘረኝነት ብቻ ሳይሆን በሽታም ነው።!!!!!!!!!

ያ ብቻ አይደለም ሕዝብን የሚጎዱ እንቅሳሴዎችን ከማድረግ መቆጠብ አለብን። ለምሳሌ ወደ ትግራይ የሚሄዱና የሚገቡ መኪናዎችን እንዳያልፉ መንገድ መዝጋት ሕወሃቶችን ሳይሆን ሕዝቡን ነው የሚጎዳው። ትልቅ ስህተት ነው። የሕወሃት ባለስልጣኖች የሚፈልጉትን በአይሮፕላን ያስመጣሉ፣ መንገድ ተዘጋ አልተዘጋ። ሕዝቡ ነው የሚጎዳው።ህዝብ ተጎዳ አልተጎዳ እነርሱ ግድ የላቸውም።