ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን የማይመጥነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር

ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ብድር መቀበያ፣ መደራደሪያ፣ ፕሮፖዛል ማቅረቢያም መሆን የለበትም።

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን የማይመጥን ምክንያት :- ጌታቸው ሽፈራው

የትናንቱ ፓርላማ ውሎ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ መልካም ጉዳይ ነግረውናል። የረመዳንን በዓል በደመቀ ሁኔታ ይከበራል ብለውኛል። በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እምነት ሳይለያቸው በዓሉን እንዲያከብሩ ይሰራል ብለውናል። ይህ አስደሳች ዜና ነው። አስደሳችነቱ ደግሞ ለረመዳን ብቻ አይደለም። ባለፈው ልደትና ጥምቀት ይሄ ተሞክሮ ውጤታማ ነበር። ኢትዮጵያውያን በረመዳንም፣ በኢሬቻም፣ በጨምበላላም፣ በጥምቀት፣ መስቀል፣ ሻደይና ሶለል፣ ልደትና እየደመቁ በመጡት የፈረስ ጉግስ በዓላት ላይ ከውጭ እየመጡ እንዲያከብሩ ማድረግ ብዙ ጥቅም አለው።

ትናንትና የተነገረን ችግሩ ምክንያቱ ነው። በዓሉ በድምቀት እንዲከበር መታሰቡን ደስ ብሎን ሳንጨርስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ በዓል ያነሳሳቸው የሚመስል አድርገው ያቀረቡት ምክንያትን ለሰማ ጆሮን የሚያጮልና ለታሪክ ጠገቦቹ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችም ክርስትያኖችም ክብረ ነክ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አረብ አገራት በቂ ሙስሊም ያለን አይመስላቸውም። የላችሁም ይሉናል” ብለዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገር “ለምሳሌ” ተብሎ አልተነገረም እንጅ ሚስጥር ነው። እነ አብይ አህመድ ወደ አረብ አገራት ተመላልሰዋል። ብድርም ሌላም ሲጠይቁ ታዲያ አገራት የራሳቸውን ፍላጎት ይጭናሉ። አንደኛው የእምነት ጉዳይ ነው።

ራሳቸውን ሚዛን አድርገው እስልምናን እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጡ አገራት እንዳሉ እናውቃለን። ታዲያ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር እንደተረዳነው “በቂ ሙስሊም የላችሁም” የሚለውን የአንዳንድ አገራት ጫና ለመቀነስ ረመዳንን ደመቅ አድርጎ አክብሮ ማሳየት እንደ እቅድ ተይዟል ማለት ነው። ይህ ጉዳይ ከብዙ መልኩ ክብረነክ ነው። ታሪክ ጠገቡን የኢትዮጵያ ሙስሊም ትናንት ነዳጅ ስላገኙ ጫና ማድረስ የቻሉ አገራት ደረጃ ሊያወጡለት ተገቢ አይደለም። የኢትዮጵያ ሙስሊም ብድር መቀበያ፣ መደራደሪያ፣ ፕሮፖዛል ማቅረቢያም መሆን የለበትም።

እውነቱን ለመናገር ይህን የመሰለ ምክንያትን መቃወም ያለበት ታሪክ ጠገቡ የኢትዮጵያ ሙስሊም ነው። በዓሉ በደንብ ይከበር። መሰል ለፖለቲካ ሲባል ግን ግዙፉን የኢትዮጵያ ሙስሊም ልጣፊ አድርጎ ማቅረቡ ከእምነት ባሻገር ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ሊያስቆጣ የሚገባ ጉዳይ ነው። የቢላል አገር ሙስሊሞች አስተዋፅኦ ትናንት ነዳጅ ባከበረው ሚጥጥዬ አገር አይን የሚንኳሰስ፣ ቁጥሩ የማይናቅ ቢሆንም ገንዘብ ባላቸው ቁጥራቸው ትንሽ ነው ተብሎ አስተዋፅኦ የሚናቅ አይደለም። ከዚህ ባሻገር የመስቀል አደባባይን ጉዳይ የበለጠ ለማጦዝ ይሆናል በሚል አንዳንድ ሙስሊም አክቲቪስቶችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር አውግዘውታል።