አሸባሪ ለመሸገባት ትግራይ መቶ ቢሊዮን፣ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ለቆመው ወልቃይት ጠገዴ ምንም!

አሸባሪ ለመሸገባት ትግራይ መቶ ቢሊዮን፣ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ለቆመው ወልቃይት ጠገዴ ምንም! – ጌታቸው ሽፈራው

ትህነግ ምርጫ አደርጋለሁ ካለ በኋላ የፌደራል መንግስቱ ለትግራይ በጀት መድቧል። “እንዴት ለፌደራል መንግስቱ እውቅና ለማይሰጥ ትህነግ በጀት ይላካል?” ሲባል ለወረዳና ዞኖች እልካለሁ ብሎ ነበር። የሆነ ሆኖ ትህነግ ጫካ ገብቶም ትግራይ በጀት ተልኮላታል። ከታቀደላት በጀት አስር እጥፍ ( መቶ ቢሊዮን ) ተሰጥቷት አብዛኛውን ትህነግ ተጠቅሞበታል። በአንፃሩ ለወልቃይትና ራያ የተደረገ ነገር የለም። የተወሰኑ ወጭዎቻቸውን የሸፈነው የአማራ ክልል መንግስት ነው። ያውም ተጨማሪ በጀት ሳያገኝ፣ እንዲያውም ከጥቅምት 24 በኋላ መከላከያ መኪናዎቹንና ነዳጁን ተነጥቆ ሲመለስ አብዛኛውን አማራ ክልል ችሎ።

ባለፉት ወራት ራያ በትህነግ ስር ስለሆነ እንጅ ወልቃይት ላይ እያየነው እንዳለው የፌደራል መንግስቱ ምንም እንደማያደርግለት ግልፅ ነው። ወልቃይት በአማራ መንግስት ስር ቢሆንም የፌደራል መንግስቱ የትግራይ አካል አስመስሎ ከመሳል ያለፈ አመለካከት የለውም። ይሁንና ስለ ትግራይ በጀት ሲጠየቅ “በዞንና በወረዳዎቹ በኩል አደርሳለሁ” ያለው መንግስት በትህነግ ስር ለሚገኙ ወረዳዎች አደርሳለሁ እንዳላለ ከመንግስት ጎን ሆኖ አሸባሪ ለሚታገለው ዞን ግን በጀት ለማድረስ አልፈለገም። ወልቃይትን በወታደራዊ አፈፃፀም ይሸልሙታል ለበጀት ሲሆን ይረሱታል። ለወልቃይት ጠገዴ በጀት ለመላክ የሚያስቸግር ጉዳይ አልነበረም። ለትግራይ ተልኳል። ያውም አስር እጥፍ። ቀጠናው እጅግ ጠቃሚ፣ ኢትዮጵያ በብዙ ጉዳይ እየተጠቀመችበት ያለ ቀጠና ነው። በተደጋጋሚ በተደረጉ ስብሰባዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመንግስት ባለስልጣናት “በጀት ይለቀቃል” እያሉ ሲሸነግሩ ከአመት በላይ ሆኗቸዋል። መጀመርያ አካባቢ የወልቃይት ጠገዴን ወጭ የቻለው አማራ ክልል ነው። በጀት በማድረስ ልምድ አለው። ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ ዞን በአማራ ክልል ስር ሲሆን ጥያቄ አልቀረበም። በሕጋዊ ደብዳቤ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ይላላካል። ፌደራል መንግስቱ ሲፈልገው የሚያውቀው በአማራ ክልል ስር ያለ ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ ዞን ብሎ ነው። በወልቃይት ጠገዴ መሬት እያረሱ፣ እየነገዱ ያሉ ባለሀብቶች ለፌደራል መንግስት ግብር እየከፈሉ ነው። በመንግስትም ሆነ በፓርቲ ጉዳይ ይጠሯቸዋል። በበጀትና በመልሶ ግንባታ ጉዳይ ይተውታል። መሬት ለመሸንሸንና ሰሊጥ ለመሸጥ ይቋምጣሉ። የበጀት ጊዜ ፊታቸውን ያዞራሉ።

የመከላከያ ሰራዊቱ በትህነግ ሲመታ ከአማራ ፀጥታ ኃይሎች ጋር ሆኖ መከላከያውን ያዳነው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጭምር ነው። በሰኔ ወር ትግራይን ለቅቆ ሲወጣም ቁስሉን እያከመ የተቀበለው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ነው። በቀጠናው ከትህነግ ጋር በሚደረገው ውጊያ አርሶ አደሩ እርሻውን ትቶ ምሽግ ውስጥ ከርሟል። ቀሪው ሕዝብ ስንቅ አቀባይ ነው። ያለ በጀት የከረመችው ወልቃይት አመራር ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ሆኖ ሲያስተባብር ነው የከረመው። በአንፃሩ የፌደራል መንግስቱ ከወልቃይት ይልቅ አሸባሪ የከተመባትን ትግራይ በጀትና ሰብአዊ እርዳታ ጉዳይ ከልክ በላይ ሲያሳስበው ይታያል። አንዴ በአውሮፕላን ሌላ ጊዜ በየብስ የሚሄድላቸው እርዳታና መድሃኒት ጉዳይ ላይ መግለጫ ሲሰጥ ነው የከረመው። ወልቃይት ጠገዴ ሆስፒታሎቹ ፈራርሰው፣ ሕዝብ ጎንደር እየመጣ ይታከማል። በፌደራል ደረጃ የሚሰጠው የህክምና ቁሳቁስ እገዛ ግን ለወልቃይት ጠገዴ አይላክም።

ደሞዝ በመቋረጡ ፍርድ ቤቶች ተዘግተዋል። ትምህርት ቤቶች ዝግ ናቸው። እናቶች ቤት እየወለዱ ነው። የግብርና ግብአት ከተቋረጠ ቆይቷል። አመራሩና አልፎ አልፎ ያሉት ሰራተኞች የሚሰሩት በነፃ ነው። ይህ የሚሆነው አስር ጊዜ ዶላር አጠረኝ የሚለው መንግስት የውጭ ምንዛሬ የሚያገኝበት ሰሊጥ፣ የቀንድ ከብት፣ ጥጥ ወዘተ በስፋት ወደውጭ የሚላክበት ወልቃይት ጠገዴ ላይ ነው። መሬት ሲሆን በካድሬና ወዘተ ደብዳቤ “ይሰጥ” እየተባለ ይከፋፈላል። የበጀት ክፍፍሉ ላይ ግን ወልቃይት ጠገዴን የሚያስበው የለም። ለውጭ ምንዛሬ ሲሆን “ሰሊጡ ደረሰ አልደረሰም” እያሉ ይጠይቃሉ። ለበጀት ሲሆን ግን አይታያቸውም። ይህ የሚሆነው ትህነግ ዋናው ግንባር ብሎ ሊያጠቃው ቀን ከሌት በሚሰራበትና ሕዝቡ ከመከላከያ ጎን ሆኖ ስራውን የፀጥታ ጉዳይ ባደረገበት ወልቃይት ጠገዴ ነው።

ለወልቃይት ጠገዴ ከበጀትም በላይ እገዛ ያስፈልገው ነበር። ላለፉት አስርት አመታት በአፓርታይድ አይነት ጭቆና የኖረ ሕዝብ ነው። ሲጨፈጨፍ የኖረው አልበቃ ብሎ ማይካድራና ሌሎች ቦታዎች ላይ የተደገመው ዘግናኝ የዘር ፍጅት ልዩ ጥበቃ የሚያስፈልገው መሆኑን የሚያሳይ ነበር። ለትግራይ አስር እጥፍ ሲላክ ለመሰረታዊ አገልግሎቶች በጀት አለመላክ የተለየ ደባ ስለመሆኑ ግልፅ ነው። እስካሁን ባለው አካሄድ ወልቃይት ጠገዴ በአማራ ክልል ስር መሆኑን ደስተኛ ያልሆኑ ሕዝቡም ተማርሮ በፌደራል ወይ በሌላ አደረጃጀት እንዲሆን ፍላጎት ያላቸው አካላት አሉ። የትህነግ የውጭ ደጋፊዎች “ምዕራብ ትግራይ” እያሉ ስለሚነዛነዙ ብቻ ለእነሱ ማስታገሻ ተብሎ ሕዝብ በችግር እንዲጠበስም ተፈርዶበታል። መሬትና ወደ ውጭ የሚላክ አዝዕርቱን እየፈለጉ በጀት ላይ አላውቅህም ማለት ከከፋ ደባ የመነጨ እንጅ እንዲሁ ተራ አስተዳደራዊ ስህተት አይደለም። አማራው በግፍ ተይዞ የነበረ ሕዝቡ ጋር መኖሩን የሞራል የበላይነትም አቅምም ይሰጠዋል ብለው የሚያስቡ ክፉዎች እጅም ያለበት ነው።