በአፋር ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሳምንታት ቢያስቆጥርም፣ በመንግሥት በኩል ተገቢ ምላሽ አለመሰጠቱ እየተገለጸ ነው።

የአፋር ዳግም መጠቃት ዛሬም እንደ ትላንት? – Addis Maleda

በመርሻ ጥሩነህ

ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ከገባች አንድ ዓመት ከሦስት ወራት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በተለያዩ ተለዋዋጭ ሁነቶች ታጅቦ አሁንም እንደቀጠለ ነው። በጦርነቱ ከታዩ ተለዋዋጭ ሁነቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ጦርነቱ አንድ ጊዜ እየቆመ ሌላ ጊዜ እያገረሸ መቀጠሉ ነው።
ሕወሓት በአፋር እና አማራ ክልሎች ከአምስት ወራት በላይ ከቆየ በኋላ ወደ ትግራይ መመለሱ የሚታወስ ነው። ሕወሓት ወደ ትግራይ ቢመለስም አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአፋር ክልል ዳግም ጦርነት ከፍቷል። በአፋር ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሳምንታት ቢያስቆጥርም፣ በመንግሥት በኩል ተገቢ ምላሽ አለመሰጠቱ እየተገለጸ ነው።

አፋር ዳግም በሕወሓት ወረራ እየተጠቃ በመንግሥትም ይሁን በሌሎች አካላት ምላሽ አለመሰጠቱ በኢትዮጵያዊነቱ ለማይደራደረው አፋር ሕዝብ አይገባውም የሚሉ ሀሳቦች እየተንጸባረቁ ነው፡፡ አፋር ዳግም በጦርነት መጠቃቱን እና ተገቢ ምላሽ አለመሰጠቱን በተመለከተ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ እና ጦርነቱን በቅርበት የሚከታተለውን የአፋር ሕዝብ ፓርቲ እና የፖለቲካ ባለሙያ አነጋግሮ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አደርጎታል፡፡

ኢትዮጵያ በገጠማት ጦርነት ቀጥተኛ ሠላባ የሆኑት ትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ከአንድ ዓመት በላይ ከሠብዓዊ እስከ ቁሳዊ ኪሳራ አስተናግደዋል። መነሻውን በትግራይ ክልል ያደረገው ጦርነት ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል ተገድቦ ቢቆይም፣ በ2013 ሐምሌ ወር ላይ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ተሸጋግሮ ከአምስት ወራት በላይ ጦርነቱ በኹለቱ ክልሎች ውስጥ ቆይቷል።

በነዚህ ወራት የጦርነቱ ሠላባ የሆኑ የክልሎቹ ነዋሪዎች በርካታ የሠብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ አስተናግደዋል። ሠብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ያስተናገዱት የኹለቱ ክልል ነዋሪዎች ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ ነበር ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት) ወረራ ነጻ ወጡ ብሎ መንግሥት ያበሠረው።
በወቅቱ አማራ እና አፋር ክልሎች ከሕወሓት ነጻ መውጣታቸው ቢገለጽም፣ በኹለቱም ክልሎች የትግራይ አዋሳኝ በሆኑ አከባቢዎች ላይ ውጊያ እንደነበር፣ እንዲሁም በርካታ አዋሳኝ አካባቢዎች ነጻ አለመውጣታቸው ሲገለጽ ነበር። በወቅቱ ሕወሓት ከኹለቱ ክልሎች ወጣ በመባሉ የጦርነቱ ቀጥተኛ ተጎጅ ከሆኑት ዜጎች በተጨማሪ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደስታውን የገለጸበት ጊዜ ነበር።

ይሁን እንጂ፣ ሕወሓት ከአማራ እና አፋር ክልሎች መውጣቱ ከተገለጸ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኹለቱም ክልሎች የትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች በሕወሓት ጥቃት በድጋሚ መፈናቀል መጀመራቸው የሚታወስ ነው። በአዋሳኝ አካባቢዎቹ በሚካሄዱ ውጊያዎች ከሚፈናቀሉ ዜጎች በተጨማሪ ሕወሓት በአፋር ክልል ላይ በግልጽ መጠነ ሠፊ ጥቃት መጀመሩን መግለጹ የሚታወስ ነው።

ሕወሓት በአፋር ክልል ላይ ደጋግሞ በከፈተው ጥቃት የአፋር ሕዝብ ዳግመኛ የጦርነቱ ተጠቂ ከሆነ ሳምንታት ተቆጥረዋል። በዚህም ሕወሓት እስካሁን ከሦስት ያላነሱ ወራዳዎችን መቆጣጠሩን የአፋር ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ዳግም በተጀመረው ጦርነት ሕወሓት በአፋር ሕዝብ ላይ “የዘር ማጥፋት” ጦርነት እያካሄደ ነው የሚለው ክልሉ፣ ዳግም በተጀመረው ጦርነት ከ300 ሺሕ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን አስታውቋል።

ሕወሓት በአፋር ላይ የከፈተው ጥቃት ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑን የክልሉ መንግሥት የገለጸ ሲሆን፣ ሕወሓት ከዚህ ቀደም በክልሉ በኹለት ዙር በፈጸመው ወረራ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችት ለሠብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መዳረጋቸውን አስታውሷል። ከዚህ ቀደም በነበሩት ጥቃቶች ክፉኛ የተጎዳው የአፋር ሕዝብ ከደረሰበት ጉዳት ሳያገግም ተመልሶ ለመፈናቀል እና ለረሃብ መጋለጡ አየተገለጸ ነው።

ሕወሓት የከፈተው ሦስተኛ ዙር ጥቃት የአፋር ጅቡቲ መንገድን ለመዝጋት በከባድ መሣሪያ በመታገዝ የተሠነዘረ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል። በዚህም በአፋር ክልል በዞን ኹለት በመጋሌ፣ አብዓላ፣ በርሃሌ፣ ኩናባር እና አረብቲ ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ ተነግሯል።
በፌዴራል መንግሥት “የመጀመሪያ ምዕራፍ” በተባለው ጦርነት የአፋር ሕዝብ ጦርነቱን ለመመከት ለአምስት ወራት ዋጋ መክፈሉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ጦርነቱን ለመመከት ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ ዋጋ የከፈለው የአፋር ሕዝብ ዛሬ ላይ ሕወሓት በከፈተበት ሦስተኛ ዙር ጥቃት ብቻውን የጦርነቱ ገፋት ቀማሽ መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአፋር ሕዝብ ፓርቲ(አሕፓ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ መሐመድ አወል ተናግረዋል። “አፋር ከራሱ አገሩን ያስቀድማል” የሚሉት መሐመድ፣ የአፋር ሕዝብ ከወራት በፊት ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ ዋጋ እንዳልከፈለ ዛሬ ሕወሓት የከፈተበትን ጦርነት ብቻውን እየተጋፈጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሕወሓት በአፋር ክልል ዞን ኹለት በከፈተው ጦርነት ከአምስት ያላነሱ ወረዳዎች የጦርነት ሠለባ መሆናቸውን የሚገልጹት መሐመድ፣ መሣሪያ ያልታጠቀ አርብቶ አደር ለከፋ ችግር መጋለጡን ጠቁመዋል። በጦርነቱ እየደረሰ ያለው የሠብዓዊ መብት ጥሰት አስቃቂ ነው የሚሉት መሐመድ፣ ሴቶችና ሕጻናት ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ጠቁመዋል። በበረሃ የሚኖረው አርብቶ አደሩ የአፋር ሕዝብ ትላንት ጦርነቱን ለመመከት ዋጋ እንዳልከፈለ ዳግም በተከፈተበት ጦርነት ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ ለረሃብ መጋለጡን መሐመድ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው የአፋር ሕዝብ፣ ሕወሓት በአፋር እና በአማራ ክልሎች ከአምስት ወራት በላይ ወረራ በፈጸመበት ጊዜ ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ ዋጋ እንዳልከፈለ፣ ዛሬ በሕወሓት ዳግም ወረራ ሲፈጸምበት ከጎኑ የቆመ አካል እንደሌለ መሐመድ ጠቁመዋል። የአፋር ሕዝብ በሕወሓት ዳግም መጠቃቱን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት ለጥቃቱ ምላሽ አለመስጠቱ የአፋርን ሕዝብ እያስቆጣ ይገኛል።

የክልሉ ሕዝብ ከዚህ በፊት ባስተናገደው ጦርነት ከደረሰበት ሠብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ በማገገሚያው ወቅት፣ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው ሳይመለሱ፣ መጠለያ ሳያገኙ፣ በቂ ሠብዓዊ ድጋፍ ሳያገኙ፣ ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ሥብራት ሳያገግሙ እና ከሀዘናቸው ሳይጽናኑ ለዳግም ጦርነት ተዳርገዋል። የአፋር ሕዝብ ለዳግም ጦርነት መዳረጉን ተከትሎ በመንግሥት በኩል በቂ ምላሽ አለመሠጠቱ ደግሞ ችግሩን እያባባሰው ነው ተብሏል።

ዛሬም እንደ ትላንት?
የፌዴራል መንግሥት ‹‹የሕግ ማስከበር›› በሚል መነሻ በትግራይ ክልል መከላከያ አሠማርቶ ለስምንት ወራት ከቆየ በኋላ፣ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ሕወሓት በ2013 ሐምሌ ወር ላይ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ላይ ጥቃት መሠንረዙ ይታወሳል። ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል ተገድቦ የነበረው ጦርነት ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ ከአምስት ወራት በላይ በኹለቱ ክልሎች ተካሂዷል።

ከትግራይ ክልል ወደ አማራ እና አፋር ክልሎት የተሸጋገረው ጦርነት፣ በኹለቱ ከልሎች በሺሕዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ዜጎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ፣ ሴቶች እንዲደፈሩ፣ እናቶችና ሕጻናት ለረሃብና ጥም እንዲጋለጡ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲፈናቀሉ እና በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር የመንግሥትና የግለሰብ ሀብት እንዲወድም ምክንያት ሆኗል። ኹለቱን ክልሎች ለዚህ ኹሉ ኪሰራ የዳረገው ጦርነት ለአምስት ወራት ይዞታውን እያስፋፋ ሲሔድ መንግሥት ምላሽ አለመስጠቱ ሚሊዮኖችን ዋጋ ያስከፈለ እንደሆነ የሚያነሱት ብዙዎች ናቸው።

በወቅቱ ሕወሓት በኹለቱም ክልሎች ለወራት በከባድ መሣሪያ ንጹኃን ዜጎችን ሲደበድብ እና ሲያፈናቅል መንግሥት ተመጣጣኝ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ኪሳራው የከፋ እንዲሆን ማድረጉን ምሁራንና የጦርነቱ ሠለባ የሆኑ ማኅበረሠብ አባላት ሲገልጹ ይሠማል። በአማራ ክልል ሕወሓት እነ ወልዲያን፣ ደሴን፣ ኮምቦልቻን፣ ኬሚሴን፣ ሽዋሮቢትን አልፎ፣ ለአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው( 200 ኪሎ ሜትር) ደብረሲና እስከሚደርስ ድረስ፣ እንዲሁም በአፋር ክልል በኩል በርካታ አካባቢዎችን ሲያጠቃና የተፈናቀሉ ዜጎችን በተጠለሉበት በከባድ መሣሪያ ሲጨፈጭፍ መንግሥት በበኩል የመልሶ ማጥቃት ዕርምጃ አለመወሰዱ በብዙዎች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮ ነበር።

ለአምስት ወራት በዘለቀ ጦርነት ሚሊዮኖች ከተፈናቀሉ እና ንብረታቸውን ካጡ በኋላ፣ መንግሥት በወሰደው የማጥቃት ዕርምጃ ሕወሓት ከአፋር አና አማራ ክልሎች መውጣቱ የቅርብ ትውስታ ነው። ሕወሓት ከኹለቱ ክልሎች ቢወጣም መከላከያ ወደ ትግራይ እንዳይገባ በመንግሥት ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ በአዋሳኝ አካባቢዎች ሕወሓት በሚያደርሳቸው ትንኮሳዎች የሚፈናቀሉ እና የሚጠቁ ዜጎች አሉ።

በአዋሳኝ አካባቢዎች ከሚከሠቱ ትንኮሳዎች በተጨማሪ፣ በአፋር ክልል ዳግም ጦርነት ከተጀመረ ሳምንታት አልፈዋል። አፋር ዳግም ሕወሓት በከፈተው ጦርነት እየተጠቃ ቢሆንም፣ በመንግሥት በኩል ተመጣጣኝ መልስ እየተሠጠ አለመሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት መሐመድ ጠቁመዋል። አፋር ለሦስተኛ ጊዜ በተጠቃበት ጦርነት ብቻውን እየተዋጋ የፌዴራል መንግሥትም ይሁን ሌሎች ክልሎች ዝም ማለታቸው በኢትዮጵያ የማይደራደረው የአፋር ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እያባባሰው መሆኑም ተመላክቷል።

ሕወሓት በአፋር ላይ ጦርነት መክፈቱን ተከትሎ “አፋር እየተጠቃ ነው” የሚሉ ድምጾች በተለያየ መንገድ መሠማት ከጀመሩ ሳምንታት አልፈዋል። ይሁን እንጅ በመንግሥት በኩል ምላሽ አለመሰጠቱ በአፋር ክልል ዳግም የተጀመረው ጦርነት ዛሬም እንደትላንቱ እየሆነ ነው ወይ የሚል ጥያቄ እያጫረ ነው።

“መንግሥት ጦርነት የለም እያለ ይሳለቅብናል” የሚሉት አፋር ሕዝብ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ አባሉ መሐመድ፣ ዳግም በተጀመረው ጦርነት የአፋር ሕዝብ እየደረሰበት ያለው ሰቆቃ አስከፊ ነው ብለዋል። አፋር በሕወሓት ዳግም በተከፈተበት ጦርነት እየተጠቃ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አግልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ለጀርመን ድምጽ በሠጡት መረጃ በአፋር ክልል ጦርነት የለም ማለታቸው መንግሥት በአፋር ሕዝብ ላይ እየተሳለቀበት መሆኑን መሐመድ እንደ ማሳያነት አንስተዋል።

አፋር ክልል ዳግም በሕወሓት የተከፈተበትን ጦርነት አየተጋፈጠ ባለበት ወቅት መንግሥት ጦርነት የለም ማለቱን እና ለሚጠቃው አፋር ሕዝብ ከለላ አለመስጠቱን የሚገልጹት መሐመድ፣ መንግሥት ስለ አፋር ዝምታን መርጧል ነው ያሉት። በአፋር ሕዝብ ላይ ግፎች ተደራርበዋል የሚሉት መሐመድ፣ የመንግሥት ኃይል ከአፋር ሕዝብ ጎን አልተሰለፈም ብለዋል። “የአፋር ሕዝብ ድምጽ የለውም፣ ሎጅስቲክስ የለውም” የሚሉት የአሕፓ ሥራ አስፈጻሚ አባል፣ የጦር መሣሪያ ባልታጠቀ አርብቶ አደር ሕዝብ ላይ የከባድ መሣሪያ ጦርነት ሲከፈትበት መመከት የሚያስችል ተመጣጣኝ አቅም እያገኘ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

መንግሥት የጦርነቱን “ምዕራፍ አንድ” አጠናቅቂያለሁ ካለ በኋላ፣ የአገር መከላከያ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደስ ለመንግሥት ሚዲያዎች በሠጡት ቃለ መጠይቅ፣ “ምዕራፍ ኹለት” እንዳለና መከላከያ እየተዘጋጀ መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ለ “ምዕራፍ ኹለት” ጦርነት እየተዘጋጀ ነው የተባለው መከላከያ በአፋር ክልል ለተከፈተው ጦርነት ምላሽ አለመስጠቱ ዛሬም እንደ ትላንት እንዳይሆን ብዙዎች ሥጋት አላቸው።

የሰሜኑ ጦርነት በየጊዜው የሚያሳያቸው ተለዋዋጭ ኹነቶች የጦርነቱን መቋጫ እና ወደፊት ዕጣ ፈንታ ተገማች እንዳይሆን አደርጎታል የሚሉት ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር፣ መንግሥት እንደሚለው ጦርነቱ በምዕራፍ እየተከፋፈለ የሚቀጥል ከሆነ በአገር ላይ ከሚያስከትለው የሰው ኃይል፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ኪሳራ እየሠፋ ይመጣል ብለዋል። መምህሩ እንደሚሉት፣ የጦርነቱ መራዘም እና በጦርነቱ የሚጎዳው ማኅበረሠብ ችግር እየተባባሰ መሔዱ መንግሥት በሕዝብ በኩል ያለው ድጋፍ እንዲመናመን ዕድል እንደሚከፍት ጠቁመዋል።
ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ያስከተለውን ኪሳራ እስካሁን በተለይ በቀጥታ የጦርነቱ ሠለባ የሆነው ሕዝብ ያውቀዋል የሚሉት መምህሩ፣ መንግሥት በተደጋጋሚ በጦርነት የሚሠቃየውን ሕዝብ ሰቆቃ ማስቀረት መቻል አለበት ብለዋል።

አፋር ምን ይሻል?
አፋር ክልል ዳግም በሕወሓት ጦርነት ተጠቂ መሆኑን ተከትሎ በኢትዮጵያ መንግሥትም ይሁን በዓለም አቀፍ ማኅበረሠብ ትኩረት አልተሰጠውም የሚሉት የአሕፓ ሥራ አስፈጻሚ አባል፣ መንግሥት በአፋር ክልል ዳግም ጦርነት መጀመሩን ግልጽ አድርጎ ለሕወሓት ተገቢ ምላሽ መሥጠት አለበት ብለዋል። አፋር የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው የሚሉት መሐመድ፣ በቂ ሎጅስቲክስ ሳይኖረው የሚታገለውን የአፋርን ሕዝብ ለተከፈተበት ጦርነት ምላሽ ለመስጠት መከላከያ መታዘዝ አለበት ብለዋል።

“መጀመሪያ መንግሥት ዝምታውን መስበር አለበት” የሚሉት መሐመድ፣ መንግሥት የት አለ ብሎ የአፋር ሕዝብ እየጠየቀ ነው፤ አለሁ ይበል ብለዋል። አፋር እየተዋጋ ያለው የኢትዮጵያን ጠላት በመሆኑ ኹሉም ኢትዮጵያዊ ለአፋር ድምጽ መሆን አለበት ተብሏል። የአፋር ሕዝብ እየተጠቃ “የመንግሥት ዝምታ ዋጋ ያስከፍለዋል” ያሉት መሐመድ፣ መንግሥት ሕወሓትን ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ካላስወጣ የአፋር ሕዝብ ማንኛውንም ሠላማዊ ኹኔታ እንደማይቀበልም ጠቁመዋል።

ዳግም በተከፈተው ጦርነት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀለው የክልሉ ሕዝብ ችግር ላይ መሆኑን በመገንዘብ፣ የተፈናቀለውን ሕዝብ መደገፍ እንደሚገባም ተመላክቷል። ተፈናቃዮች ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ በረሃም እየሞቱ ነው ያሉት መሐመድ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አፋርን መደገፍ አለበት ብልዋል።
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ጥር 20/2014 አፋር ዳግም በጦርነት መጠቃቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ የክልሉ መንግሥት፣ የክልሉ ሕገ-መንግሥት በሚደነግገው መሠረት በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንዲያውጅ እና ጠንከር ያለ ኮማንድ ፖስት እንዲያደራጅ መጠየቁ የሚታወስ ነው። ፓርቲው በመግለጫው ለሕወሓት ጥብቅና ለቆሙ አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሠጠው ማሳሰቢያ “የአፋር ሕዝብ እየታረደ፣ በከባድ መሣሪያ አየተደበደበ እና አየተራበ ባለበት ወቅት በአሸባሪው ክልል እየደረሰበት ያለውን ግፍ በመደገፍ ጭራሽ ለአሸባሪው ቡድን በምታደርጉት ደጋፍ እሰከ ቀጠላችሁ ድረስ የአፋር ሕዝብ ለዚህ እኩይ ተግባራችሁ ምንም አይነት ትብብር አንደማይሰጥ ከወዲሁ እናሳስባችኋለን” ብሏል።