በስልክ በትግረኛ ቋንቋ ማውራት ህገመንግስታዊ መብቴ ነው – ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም

በስልክ በትግረኛ ቋንቋ ለማውራት እና ማስታወሻ ደብተር እንድንይዝ ይፈቀድልን ሲሉ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ማረሚያ ቤቱ መልስ ሰጥቷል።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና የህገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ለዛሬ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በ6 ተከሳሾች በተነሱ አቤቱታዎች ላይ መልስ እንዲሰጥ በያዘው ቀጠሮ ችሎቱ የተሰየመ ሲሆን አቤቱታ አቅርበው ከነበሩ ስድስት ተከሳሾች ውስጥ 11 ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሙሉ ገ/እግዛብሔር ክሳቸው በመቋረጡ አቤቱታቸው ታልፏል።

በዛሬው ቀጠሮ 8ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም እና 19 ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ በህመም ምክንያት በችሎት ያልቀረቡ ሲሆን 20ኛ ተከሳሽ አሰፉ ሊላይ 43 ኛ ተከሳሽ ተክላይ አብርሐ እና 44 ኛ ተከሳሽ ዘሚካኤል አንባዬ ግን ቀርበዋል።

የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የቀድሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዬ የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በትግረኛ ቋንቋ ስልክ ለማውራት ስለተከለከልን እንዲፈቀድልት ይታዘዝልን ስትል ያቀረበችው አቤቱታን በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ በስልክ ማውራትም የተከለከለው ለሀገሪቷ ደህንነት ክትትል ስለሚደረግ መሆኑን በጽሁፍ ምላሽ ሰቷል።

በተጨማሪም በማስታወሻ ደብተር ተከልክለናል ሲሉ ባቀረቡት አቤቱታ ላይም ማረሚያ ቤቱ ከፍርድ ቤት ማህተም ካለበት ሰነድ ውጪ መያዝ የተከለከለው በደህንንነት መከታተያ ስርአት መሰረት መሆኑን ምላሽ ሰቷል።

መንጃ ፍቃዴንና ፖስፖርቴን አ/አ የሚኖር ለአንድ የዩንቨርስቲ ተማሪ ዘመዴ እንዲያሳድስልኝ በማረሚያ ቤት ስለተከለከልኩ እንዲፈቀድልኝ ሲል 43 ኛ ተከሳሽ ተክላይ አብርሐን ባቀረበው አቤቱታን በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ የሚፈቀደው በኗሪነት መታወቂያ ብቻ በመሆኑን በጽሁፍ ምላሽ ሰቷል።

20ኛ ተከሳሽ የቀድሞ የትግራይ ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ አሰፉ ሊላይ በባለፈው ቀጠሮ ለሶስት ወር በፖሊስ እጅ መቆየታቸውን ጠቅሰው ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር።

በዕለቱ በፍርድ ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥ የታዘዘው ዓቃቢህግ በበኩሉ ተከሳሿ በነሀሴ 11 ቀን 2013 ዓ/ም በህገወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሀገር ሊወጡ ሲሉ በፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሶ በነሀሴ 12 ቀን ደግሞ ጉዳያቸው ተሰብሮ በተከሰሱበት የክስ መዝገብ ወደ ክርክር እንዲገቡ ለፍርድ ቤቱ ማሳወቁን በማስረጃ አስደግፎ ምላሽ ሰቷል።

በሌላ በኩል ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ በዚሁ መዝገብ ከተከሰሱ ሌሎች ተከሳሾች ጋር በአንድ ማረሚያ ቤት ነገር ግን በተለያዩ ቦታዎች መታሰራቸውን ተከትሎ ተገናኝተው ለመወያየት አለመቻላቸውን ጠቅሰው ተገናኝተው ለመወያየት እንዲፈቀድላቸው ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ማረሚያ ቤቱ መልስ ሳይሰጥ ማለፉ ተገልጿል።

ይሁንና ማረሚያ ቤቱ በቀጣይ ከቀጠሮ ስስት ቀን በፊት በዶ/ር ሰለሞን የቀረበው ተከሳሾች ተገናኝተን ለመወያየት ይፈቀድልን የሚለው አቤቱታ ላይ ምላሹን አካቶ እንዲቀርብ ታዟል።

ዛሬ በችሎት የተገኘው የተከሳሾች ጠበቃ ወንደሰን በቀለ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በስልክ በትግረኛ ቋንቋ ማውራት ህገመንግስታዊ መብታቸው መሆኑን በማብራራት ክልከላው ሰባዊ መብታቸውን የሚጋፋ እና ህግን የተከተለ አደለም ሲል መቃወሚያ አሰምቷል።

ጠበቃ ወንደሰን የግል ማስታወሻ ደብተራቸው ላይ ጽፈው አዘጋጅተው ፍርድ ቤት ይዞ የመምጣት መብት እንዳላቸው በመግለጽ እየተፈተሽ መከልከሉ የግል ነጻነታቸውን የሚጋፋ ጫና የሚፈጥር አሰራር ነው ሲል ጠበቃቸው ለማረሚያ ቤቱ ጥብቅ ትዛዝ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም አቤቱታ በቀረበባቸው ጉዳዮች ብቻ መርምሮ ትዛዝ ለመስጠት ለጥር 17 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል።

ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ