የሲዳማ ክልል ከተባለ አዋሳስ የት ልትሄድ ነው ? #ግርማ_ካሳ

 

የጎሳ አወቃቀር ለጉዳት ለመከፋፈል ዳርጎናል እየተባለ ባለበት ወቅት በወ/ሮ ሙፈሪያት የሚመራው ደሃዴን/ኢሕአዴግ፣ የደቡብ ክልልን እንደገና በዘር ለመከፋፈል ሲጣደፍ እያየን ነው። በደሃዴን የሚመራው የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሲዳማዎች ብቻ የሆነን አዲስ አፓርታይዳዊ ክልል ለመሸንሸን ዉሳኔ አሳልፏል።

ይህ ዉሳኔ ምን አልባት ለጊዜው ኢጄቶ የተባሉ የሲዳማ አክራሪዎችንና ከነኦነግና ኦብነግ ጋር ለዘመናት ሲሰሩ የነበሩ ራስቸውን የሲዳማ ነጻ አውጭ ግንባር ብለው የሚጠሩትን ጠባብ ዘረኞች ሊያስደስት ይችል ይሆናል። ግን የሲዳማ ማህበረሰብን በእጅጉ የሚጎዳ ዉሳኔ ነው። የሲዳማ ማህበረሰብ የሚጊዳ ብቻ ሳይሆን በዚያ የሚኖሩ ሌሎች ማህበረሰባትንም  ለከፍተኛ አደጋ ማጋለጡ የማይቀር ነው። በቅርቡ አክራሪ የሲዳማ ቡድኖች በወላይታዎች ላይ ያደረሱት ሰቆቃና እልቂት ሁላችንም የምናስታወሰው ነው። አሁን ደግሞ ጭራሽ “ይሄ የናንተ ክልል ነው”  ብለን ከሰጠናቸው ፣ “ሌላውን መጤ እያላችሁ ማባረራችሁን ቀጥሉበት” እንደማለት ነው። 

የደቡብ ክልል አነስ ወዳሉ ሕብረብሄራዊ አስተዳደርኖች መቀየሩ ችግር የለውም። ለምሳሌ የሲዳማ፣ የጌዴዎ ዞኖች አንድ ላይ ሆነው ሲዳማዎች የበላይ የሆኑበት ክልል ሳይሆን በዚያ የሚኖሩ ሁሉም ዜጎች እኩል የሚታዩበት የዘር ልዩነት የማይደረገበት ሕብረ ብሄራዊ መስተዳደር ቢሆን የበለጠ ሊጠቅም ይችላል።  መስተዳደሩም እንደ ድሮ የሲዳማ መስተዳደር ቢባልም ችግር የለውም። ግን የሲዳማዎች ክልል ተብሎ ራሳቸው ሲዳማዎችን ነን ብለው የሚጠሩ የበላይ የሆኑበት ክልል መፍጠር ግን ከእሳት ወደ ረመጥ መሄድ ነው።

ይህ ዉሳኔ ከሕግና ከፍትሃዊነት አንጻር ሶስት መሰረታዊ ችግርቾ አሉት።

አንደኛ – የሲዳማ ክልል ሲመሰረት በስተሰሜን በኩል አዋሳ አለች። የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሆና በመላው የደቡብ ክልል ሕዝብ ያደገች ከተማ ናት። በክልሉ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በፌዴራል ደረጃ ብዙ ወጭ አዋሳ ላይ ፈሷል። ይችን ዉብ ሕብረ ብሄራዊ ከአዲስ አበባና ከባህር ዳር ቀጥሎ፣ ምን አልባት ከባህር ዳር በላይ፣ ትልቅና ዘመናዊ የሆነች ከተማን ለአንድ ጎሳ ብቻ መስጠት ኢፍትሃዊነት ነው። በመሆኑም ሲዳማዎች ክልል ካልተሰጠ ብለው ድርቅ ካሉ ያለ አዋሳ መሆኑን እንዲረዱ ማድረጉ አስፈላጊና ዉሳኒያቸውን መልሰው እንዲመረምሩ ሊረዳቸው ይችላል። የአዋሳ ከተማ ራሷን የቻለን ቻርተር ከተማ ሆና እንድትቀጥልም መደረግ ነው ያለበት። አዋሳ የነዋሪዊቿ እንጂ የሲዳማዎችን ብቻ አይደለችም።

ሁለተኛ – ከሲዳማ ክልል በስተደቡብ የሚገኝ ሌላ ትልቅ የደቡብ ክልል ዞን አለ። የጌዴዎ ዞን። የሲዳማ ዞን የሲዳማ ክልል ይሁን ከተባላ የጌዴዎ ዞን ከተቀረው የደቡብ ክልል ዞኖች ጋር ይለያል ማለት ነው። ኩታ ገጥምነቱ ስለሚቀር። የጌዴዎ ዞን ከደቡብ ክልል ተለይቶ የራሱ ክልል ሊሆን ነው ? ወይስ በሲዳማ ክልል ውስጥ ሊጠቃለል ነው ? ስለዚህ የሲዳማ ክልል የመሆን ጉዳይን በተመለከተ ሲዳማዎችን ብቻ ሳይሆን የጌዴዎ ዞን ነዋሪዎችን የሚመለከት ነው የሚሆነው።

ሶስተኛ – ይሄን ዉሳኔ ያሳለፉ የክልል ምክር ቤት አባላት በመቶ በሞቶ ምርጫ አሸነፊ የተባሉ አባላት ናቸው። እንዲህ አይነት ዉሳኔ የመወሰን  ሕጋዊ መሰረት የላቸውም። ስለዚህ በሕግ አንጻር ዉሳኔያቸው ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

በዚህ ጉዳይ ላይ የዶ/ር አብይ አስተዳደርም ያለውን አቋም ምን እንደሆነ ሕዝብ ቢያወቀው ጥሩ ነው። ይሄ ዉሳኔ የነ ዶር አብይን አዎንታ ሳያገኝ እነ ወ/ሮ ሙፈሪያትና የደቡብ ክልል ምክር ቤት በራሳቸው ያደረጉት ነው ብዬ አላስብም። የሲዳማ ተወካዮች እንኳ ሲዳማ ዞን ወደ ክልልነት ይዙር ቢሉ፣ የጉራጌ፣ የጋሞ፣ የወላይታ … የተቀረው የክልሉ ምክር ቤት አባላት ከአዲስ አበባ ውስጣዊ መመሪያ ካልተሰጣቸው በቀር እሺ ይላሉ ብዬ አላስብም። በዚህ ጉዳይ ላይ ጋዜጠኞች የዶር  አብይን አስተዳደር መጠየቅና እውነታዉን ለማጣራት መስራት ያለባቸው ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልጋት ልዩነት የሚያሰፋ ሳይሆን የሚያጠብ ነው። አሁን ያሉት የዘር ክልልች ፈርሰው አዲስ ዘመናዊ ፣ በዘር ላይ ያልተመሰረተ፣ በአስተዳደር አመችነት ፣ በሕዝብ ፍላጎት፣ በኢኮኖሚና በታሪክ ላይ ያማከለ፣ ሁሉም ዜጎች በሁሉ የአገሪቷ ክፍል በነጻነት እንደ አገራቸው እንዲኖሩ የሚያስቸል የፌዴራል አወቃቀር ነው።