የሥራ ማቆም አድማ የመቱ የጤና ባለሙያዎች ተወካዮች ግንቦት 15 ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን ከተወካዮቹ መስማቱን ቢቢሲ ዘግቧል። ኢሰመኮ በጉዳዪ ገለልተኛ አደራዳሪ ለመኾን ጥያቄ ማቅረቡንና በዚህ ዙሪያ “ቅድመ ውይይት” እየተደረገ መኾኑን ተወካዮቹ መናገራቸውንም ዘገባው ጠቅሷል። ኾኖም በጤና ባለሙያዎች ላይ እስሩ፣ ዛቻውና ማስፈራሪያው አለመቆሙን በመጥቀስ፣ መንግሥት ለድርድር ባለው ቁርጠኝነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተወካዮቹ ገልጸዋል ተብሏል። ከ320 ሺሕ በላይ ከሚገመቱት የአገሪቱ የጤና ባለሙያዎች፣ ከ65 እስከ 75 በመቶ ያህሉ በንቅናቄው እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተወካዮቹ መጥቀሳቸውንም ዘገባው አመልክቷል።