የብሄራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ፣ የመንግሥት ቀጣይ ዕቅድ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውንና ገበያ-መሩን የውጭ ምንዛሬ ገበያ “ይበልጥ ሥር እንዲሰድ” ማድረግ እንደኾነ ከዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ሃላፊ አበበ አዕምሮሥላሴ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል። ድርጅቱ ዛሬ ያሠራጨው ቃለ ምልልስ የተደረገው፣ በቅርቡ ዋሽንግተን ላይ ከተካሄደው የዓለም ባንክና ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጋራ ስብሰባ በተጓዳኝ እንደነበር ተገልጧል። ማሞ፣ ለአገሪቱ አስተማማኝ የዕድገት መሠረት ለመጣል “የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን ለማስተካከል” የሚያስችሉ ሥራዎችን መስራት ሌላኛው የመንግሥት ቀጣይ ዕቅድ መኾኑን ገልጸዋል። ገበያ-መሩ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ “አመርቂ ውጤት አስገኝቷል” ያሉት ማሞ፣ የብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ክምችትም በሦስት እጥፍ ማደጉንና የዋጋ ግሽበት ወደ 13 በመቶ ማሽቆልቆሉን ጠቅሰዋል። የአገሪቱ የወጪ ንግድም በእጥፍ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ማሞ ጠቁመዋል።