ለምን ፍርድ ቤቱን አትዘጉትም? ( ያሬድ ሀይለማርያም )

በዋስትና ጉዳይ እስከ ሰበር መሄዳችሁ ሳይበቃ የሦስት ፍርድ ቤት ውሳኔን ፖሊስ አላከብርም ካለ ለምን ፍርድ ቤቱን አትዘጉትም?

ፖሊስ በተደጋጋሚ የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ እጅግ አስነዋሪ በሆነ መንገድ  ሆን ብሎ ሲጥስና በዚህ ደረጃ የፍትህ ሥርዓቱን ሲያዋርድ ማየት ሕግ አስፈጻሚው አካል እራሱ ሕገ ወጥነትን ብቸኛ አፈናን የማጽኛ መንገድ አድርጎ መምረጡን ማሳያ ነው። ይህ ችግር አንዴና ሁለቴ ተፈጽሞ ቢያበቃ ጉዳዩ ፖሊስ ጋር ያለ ችግር እንደሆነ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።

ይህ አይነቱ ሕገ ወጥነት ሲደጋገምና እንደ ትክክለኛ አሠራር ሲወሰድ ግን ፍትህ ሚንስትሯን ጨምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ስምምነት ተደርጎበት የሚከናወን ሕገ ወጥነትን ሕጋዊ የማድረግ  የፖለቲካ ውሳኔ ነው።

– ጋዜጠኛ ተስፋለም ከመጀመሪያ ፍርድ ቤት አንስቶ ሰበር ድረስ በዋስትና እንዲለቀቅ በየደረጃው ሦስት ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ ግለሰቡ ዋስትናውን ካስያዘ በኋላም ፖሊስ አለቅም የሚለው በምን አግባብ ነው?

– የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ማይክ መላኩም እንዲሁ ከአመት በላይ አታሰረ በኋላ በቅርቡ 300ሺ ብር ዋስትና ተጠይቆበት ገንዘቡን አስይዞ ከማረሚያ ቤት ሲወጣ በር ላይ ጠብቀው አቃቤ ሕጉና ደህንነቶች አፍነው ሰውረውታል፣

– በሌሎችም በርካታ የፖለቲካ ተከሳሾች ላይ ፍርድ ቤት ዋስትና ከፈቀደ በኋላ ፖሊስ አለቅም እያለ ዜጎች ለእንግልት ይዳረጋሉ።

– በሕጉ በዋስትና በሚያስለቅቁ ጉዳዬች ከይግባኝም አልፎ እስከ ሰበር መሄድ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው?

ቅጥ ያጣ ሥርዓት አልበኝነት ይቁም! ( ያሬድ ሀይለማርያም )