አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሥራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ ያሠራቸውን የጤና ባለሙያዎች “ባስቸኳይ” እና “ያለምንም ቅድመ ኹኔታ” እንዲፈታ በድጋሚ ጠይቋል። አምነስቲ፣ መንግሥት በአድማ ላይ ከሚገኙት የጤና ባለሙያዎች ጋር ንግግር እንዲጀምርና የተቃውሞ ድምጾችን ማፈን እንዲያቆምም አሳስቧል። አምነስቲ ይህን ያለው፣ ትናንት ዘጠኝ የጤና ባለሙያዎች በከፍተኛው የፌደራሉ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አስመልክቶ ባወጣው አጭር መግለጫ ነው። ፍርድ ቤቱ፣ በትናንቱ ችሎቱ ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ስምንት የምርመራ ቀናት መፍቀዱ ይታወሳል።