በአርሲ ካህኑን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል; ሁለት ሰዎች ቆስለዋል

“ካህኑን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል። ሁለት ሰዎች ቆስለዋል” (የሟች ቤተሰብና ነዋሪ)
=========

በአርሲ ዞን ጀጁ ወረዳ ልዩ ቦታው አንጎዶቼ ሁላ አርቦዬ ከተማ ባለወልድ ቤተክርስቲያን አካባቢ የደብሩን ኃላፊ ካህን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ ሁለት መቁሰላቸውን የሟች ቤተሰብና የአካባቢው ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናገሩ።

የሟች ካህን ቤተሰብ በሰጡን ቃል፣ “ትላንት 11ሰዓት ከአርቦዩ ገበያ ውለው ሲመለሱ እቤት ገባ ብሎ እንደወጣ ነው ከቤቱ አውጥተው ይዘውት ሂደው መኪና መንገድ ዳር የገደሉት” ብለዋል።

“ አንደኛውንም በሩ ላይ ነው የገደሉት። አንደኛውንም ከብቶች ሲነዱበት ‘ከብቶቹን ተውሉኝ’ ሲል እዛው ነው የገደሉት። ሦስቱንም እዛው ነው የገደሏቸው ” ሲሉም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

“ሟቹ ካህን ነው። ቀሲስ ተስፋ አለው ይባላል” ያሉ ሲሆን፣ የገዳዮቹን ማንነት በተመለከተ “ ‘ሸኔ ናቸው’ ነው የሚባለው ” ብለዋል።

ሟቾቹ ልጆች እንዳሏቸው፣ ካህኑም የአንጎዶቼ ቅዱስ ባለወልድ ቤተክርስቲያን አገልጋይ፣ የሁለት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች አባት እንደነበሩ ተናግረዋል።

“ ከሟቾች ባሸገር አቶ ድንቁ ኃይሌ የሚባል የተመታ አለ፤ ሌሎች የት እንደደረሱ ያልታወቁ አሉ” ያሉት የሟች ቤተሰብ፣ “ከ15 ቀናት በፊት አንዲት ሴት ተገድላለች። አምስት ልጆች አግተው ወስደዋል” ሲሉም አስታውሰዋል።

አጋቾቹ አምስቱን ታጋቾች ገንዘብ እየተቀበሉ እንደመለሷቸው አስረድተው፣ “ገዳዮቹ ትላንትም ሦስቱን ሰዎች ከገደሏቸው በኋላ መከላከያዎች ገብተው ወዲያው ለቀው ወጡ፤ እነሱ ከወጡ በኋላ ሌሊት ስድስት ሰዓት ተመልሰው ከብትም፣ ገንዘብም ከሰው ላይ ወስደዋል ” ነው ያሉት።

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው፣ “ ከአዳማ ወጣ ብሎ አርቦየ የምትባል ከተማ አለች፤ እዛ መሰመር ላይ ካህን አባትና ሌሎች ሰዎች ተገድለዋል ” ሲሉ ተናግረዋል።

“ቀሲስ ተስፉ አለሙ፣ ጎረቤቶቻው አቶ በጋሻው ስዩም፣ አቶ ክፍሌ ገ/ክርስቶስ ተገለዋል። ሁለት ሰዎች ቆስለዋል። የቀብር ሥርዓታቸው ዛሬ 28/09/2017 ከቀኑ ሰባት ስዓት በደብሩ ተፈጽሟል። የተገደሉት ትላንት ማታ ነው ” ብለዋል።

“መንግስት ዝቅ ብሎ ቢያየን፤ ቢመለከትን መፍትሄ ይመጣል ” ሲሉ ነዋሪዎቹ ያሳሰቡ ሲሆን፣ ከክልሉ ባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት ብንሞክርም ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም።