ለእንጀራ፣ ለዳቦ እና ለተለያዩ የሸቀጥ እቃዎች መጠቅለያነት የሚውለውን የአንድ ብሩን ፕላስቲክ ይዞ መገኘት ከ2,000 እስከ 5,000 ብር የሚያስቀጣው አዋጅ ጸደቀ፡፡
ማንኛውም ሰው አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የፕላስቲክ ከረጢት ይዞ ከተገኘ ከ2,000 እስከ 5,000 ብር የሚያስቀጣው አዋጅ ፤ ” ዜጎችን በማያውቁት ጉዳይ ለቅጣት የሚዳርግ ነው ” የሚል ትችት ከምክር ቤት አባላት ቀርቦበታል፡፡
የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ የጸደቀው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ ፤ ማንኛውም ሰው አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የፕላስቲክ ከረጢት ይዞ ከተገኝ ከ2,000 እስከ 5,000 ብር እንዲቀጣ ይደነግጋል፡፡
ያመረተ ወይም ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ ለገበያ ያቀረበ ወይም የሸጠ፣ ለንግድ ዓላማ ያከማቸ ወይም ይዞ የተገኘ ከ50,000 ብር በማያንስና ከ200,000 ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እና ከ5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አዋጁ ያዝዛል፡፡
የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር) የአዋጁን ይዘት በንባብ ከቀረቡ በኃላ የም/ቤት አባላት ጥያቄ አቅርበዋል።
የምክር ቤት አባሉ አለሙ ጎንፋ (ዶ/ር) ህዝባችን በፕላስቲክ እቃ ይዞ ወደ ቤቱ ከገባ ይጣለው ? ወይስ መልሶ ለአካባቢ ጥበቃ ያስረክበው ? የሚል ጥያቄ ጠይቀዋል።
አክለው የምናመርተው የፕላስቲክ ውጤት ዳግም እንድንጠቀምበት የሚያደርግ ቢሆን አይሻልም ወይ ? ምክንያቱም 10 ጊዜ የምጠቀምበትን ፕላስቲክ አንድ ጊዜ ብቻ ተጠቀም ማለት ተገቢ አይደለም፣ አዋጁ ፕላስቲኩን ከተጠቀምኩበት ወዲያ የት ማስቀመጥ እንዳለበት አላስቀመጠም ብለዋል፡፡
አዋጁ ይዞ የተገኝ እንዲቀጣ ይደነግጋል ህዝባችን የዚህ ግንዛቤ ይኖረዋል ወይ ? የትኛው ፕላስቲክ እንደሆነ የመለየት ግንዛቤስ አለው ወይ ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ሌላ አንድ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ማንኛውም ሰው ፕላስቲክ ይዞ ከተገኘ ከሁለት እስከ አምስት ሺህ ብር እንዲቀጣ ይደነግጋል፤ ይህ ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዴት ታየ ? በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የማህበረሰብ ክፍል ሊጠቀመው ስለሚችል ጫና አይፈጥርም ወይ ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር) ለአንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ፌስታሎችን ዝቅተኛው የማህበረሰብ ክፍልም ስለሚጠቀማቸው ቅጣቱ ያን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል፡፡
” ለምሳሌ አንዲት አሮጊት ወይም ሽማግሌ የሁለት ብር ዳቦ ወይም የአስር ብር ስኳር ገዝተው ሲሄዱ 5 ሺህ ብር ክፍሉ ቢባሉ ላይኖራቸው ስለሚችል ቅጣቱ ከ5 ሺህ ወደ 2 ሺህ ዝቅ እንዲል ተደርጓል ይህም የህብረተሰቡን የመክፈልም አቅም ከግንዛቤ ያስገባ ነው ” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
” የፕላስቲክ ከረጢቶች ከቅጣቱ በላይ ሀገርን የሚጎዱ ናቸው እስከ መቶ ዓመት ድረስም አይበሰብሱም ” ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፤ ” ከዚህ አንጻር ቅጣቱ ሃያም ሰላሰም ሺህ ቢሆን ሀገርን ለማትረፍ ነው ” ብለዋል፡፡
ለህዝቡ ግንዛቤ ለመስጠትም ከመጪው ሃሙስ ጀምሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ይካሄዳል ሲሉ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
አዋጁ የፕላስቲክ ጫማዎችን፣ የውሃ ኮዳዎችን እና ወፍራም የፕላስቲክ ውጤቶችን አይጨምርም ተብሏል።
አዋጁ ማንኛውም ሰው ከመኖሪያ ቤቱ ድንበር አንስቶ ከሃያ ሜትር በላይ አካባቢውን የማጽዳት ግዴታንም ያስቀምጣል፡፡
አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከሚወጣበት ቀን ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ጣቢያ ነው።