የኢትዮጵያ ኢንሳይደር መስራች ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ መታሰሩ ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ ካሉ የካበተ ልምድ ካላቸው ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው ተስፋለም ወልደየስ ‘ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት’ በሚል ተጠርጥሮ መታሰሩ ታወቀ።

የጋዜጠኛውን መታሰር በተመለከተ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር አታሚ ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጋዜጠኛው የታሰረው ሰኔ 1/2017 ዓ/ም ነበር።

ተስፋለም ወልደየስ

በአዲስ አበባ ከሚገኘው ግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋለው ተስፋለም ሌሊቱን እስጢፋኖስ አካባቢ በሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ሕንፃ ውስጥ ወንበር ላይ እንዲያሳልፍ መደረጉን ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ገልጿል።

ተስፋለም የመጀመሪያውን ሌሊት ካሳለፈበት እስጢፋኖስ አካባቢ ከሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ትላንት ሰኞ ሰኔ 2 ቀን፤ 2017 ቄራ አካባቢ ወደሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ተዘዋውሯል የተባለ ሲሆን ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ቂርቆስ ምድብ ችሎት ቀርቦ በ15,000 ብር ዋስትና እንዲፈታ ተወስኖ ነበር።

“ለዋስትና የተጠየቀው ገንዘብ ከተከፈለ በኋላ ተስፋለም የጠየቀውን መስፈርት የሚያሟላ በመሆኑ ከእስር እንዲለቀቅ በፍርድ ቤቱ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። ተስፋለም ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት እንደተጠረጠረ ፍርድ ቤቱ ከእስር እንዲፈታ ትዕዛዝ በሰጠበት ደብዳቤ ላይ ሠፍሯል። የተስፋለም የዋስትና መብት እንዲከበር ከተሰጠው ትዕዛዝ በኋላ መርማሪ ፖሊስ በቃል ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጿል” በማለት መግለጫው አስታውቋል።

ይሁንና እስካሁን በይፋ ፍርድ ቤት ይግባኝ አለመጠየቁ ታውቋል።

“የተስፋለም ዋስትና እንዲከበር ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን አስፈላጊውን ክፍያ ፈጽሞ በፍርድ ቤቱ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተጻፈው ደብዳቤ በሚመለከታቸው የፖሊስ መኮንን ሳይፈረምበት ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ይህ መግለጫ ይፋ እስከሆነበት ሰዓት ድረስ ጋዜጠኛ ተስፋለም በፍርድ ቤት የተረጋገጠለት የዋስትና መብት አልተከበረም” በማለት ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ይፋ አርጓል።

ተስፋለም ለሚድያ ስራ ባለው ክብር እና ፍቅር የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ አጋጣሚዎች ለእስር ተዳርጎ እንደነበር ይታወሳል።

የጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ መታሰርን በተመለከተ ከሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን የተሰጠ መግለጫ

በሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ሥር የሚተዳደረው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የበይነመረብ ሚዲያ መሥራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ እሁድ ሰኔ 1 ቀን፤ 2017 በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውሏል። በአዲስ አበባ ከሚገኘው ግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋለው ተስፋለም ሌሊቱን እስጢፋኖስ አካባቢ በሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ሕንፃ ውስጥ ወንበር ላይ እንዲያሳልፍ መደረጉን ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተገንዝቧል።

ተስፋለም የመጀመሪያውን ሌሊት ካሳለፈበት እስጢፋኖስ አካባቢ ከሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ትላንት ሰኞ ሰኔ 2 ቀን፤ 2017 ቄራ አካባቢ ወደሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ተዘዋውሯል። ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን፤ 2017 በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ቂርቆስ ምድብ ችሎት ቀርቦ በ15,000 ብር ዋስትና እንዲፈታ ተወስኖ ነበር። ለዋስትና የተጠየቀው ገንዘብ ከተከፈለ በኋላ ተስፋለም የጠየቀውን መስፈርት የሚያሟላ በመሆኑ ከእስር እንዲለቀቅ በፍርድ ቤቱ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። ተስፋለም “ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት” እንደተጠረጠረ ፍርድ ቤቱ ከእስር እንዲፈታ ትዕዛዝ በሰጠበት ደብዳቤ ላይ ሠፍሯል። የተስፋለም የዋስትና መብት እንዲከበር ከተሰጠው ትዕዛዝ በኋላ መርማሪ ፖሊስ በቃል ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጿል። ይሁንና እስካሁን በይፋ ፍርድ ቤት ይግባኝ አልጠየቀም።

የተስፋለም ዋስትና እንዲከበር ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን አስፈላጊውን ክፍያ ፈጽሞ በፍርድ ቤቱ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተጻፈው ደብዳቤ በሚመለከታቸው የፖሊስ መኮንን ሳይፈረምበት ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ይህ መግለጫ ይፋ እስከሆነበት ሰዓት ድረስ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ በፍርድ ቤት የተረጋገጠለት የዋስትና መብት አልተከበረም።

ለጋዜጠኝነት ባለው ፅኑዕ ክብር እና ለሙያው ባለው ቁርጠኝነት የሚታወቀው ተስፋለም ዳግም በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መዋሉ የሥራ ባልደረቦቹን፣ ወዳጆቹን እና ቤተሰቦቹን በእጅጉ አሳስቧል። ተደጋጋሚ ችግሮች ቢገጥሙትም “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባለፉት ዓመታት ነጻ እና ገለልተኛ የሆኑ፣ ከፍተኛ ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን የጠበቁ ዘገባዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። በዚህም ተዓማኒነት እና ተቀባይነትን እያፈራ የመጣ የበይነመረብ ሚዲያ ተቋም ነው።

ተቋማችን የዋና አዘጋጁ ተስፋለም ወልደየስ እስር በሚዲያው ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን እየገለፀ፣ በአስቸኳይ ወደ ሥራው እንዲመለስ ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም፣ ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ተቋማችን ከፖሊስ እና ከፍርድ ቤት የሚያገኛቸውን መረጃዎች ለሚዲያው ቤተሰቦች ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።