የአዲስ አበባው ታላቅ ‘የማፊያ ስራ’!

(መሠረት ሚድያ)- አራት ኪሎ የሚገኘው ‘አምባሳደር ህንፃ’ ላይ ይገኝ የነበረው የድርጅቱ ቢሮ ውስጥ ሲገባ በመጀመርያ ቀልብን የሚስበው በብዙ የመንግስት ቢሮዎች ውስጥ እንደሚደረገው በትልቁ ታትሞ እና በፍሬም ተዘጋጅቶ የተሰቀለው የጠ/ሚር አብይ አህመድ እና የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ፎቶ ነው።

ድርጅቱ ቢሮው ብቻ ሳይሆን ማስታወቂያውም ቀልቢ ሳቢ ነበር።

“ልጄ ውጭ ሀገር ሄዳ ነው ትምህርቷን መከታተል የምትፈልገው፣ አገሯን የምታስጠራ ምሁር እንድትሆንልኝ እፈልጋለሁ” ትላለች ዝነኛዋ የማስታወቂያ ባለሙያ ሙሉአለም ታደሰ ከሌላኛዋ ታዋቂ የሚድያ ሰው ዳናይት መክብብ ጋር በመሆን በጋራ የሰሩት የዚህ ድርጅት ማስታወቂያ።

ይህ ዛሬ የምናቀርብላችሁ የከባድ ማጭበርበር ድርጊት ዋና ተዋናይ ቀላል ሰውም አይደለችም። ከጥቂት አመታት በፊት በአዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ላይ ከ ‘ተስፋ ሰጪ’ ‘እና ‘ስራ ፈጣሪ’ አምስት የሀገራችን ግለሰቦች አንዷ ሆና ቀርባለች፣ በተጨማሪም ከሴቶች እና ህፃናት ማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጌጎ ተስፋዬ ልዩ ሽልማት ተበርክቶላታል።

ግለሰቧ ቤተልሄም ታደሰ ይማም ትባላለች፣ ታድያ ተሸላሚ ያረጋት ስራዋ ምን ይሆን? ድርጅቷ ከ120 ሚልዮን በላይ ብርስ ከህዝብ እንዴት ማጭበርበር ቻለ?

ቤተልሄም ታደሰ ይማም

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ለስራ ወይም ለትምህርት ወደ ውጪ ሀገር ሰው እንልካለን በማለት ገንዘብ የሚሰበስቡ ድርጅቶች መብዛታቸውን ብዙ ሰው ታዝቧል፣ ከነዚህም አንዱ Aim Ultra Consultancy የተባለው ድርጅት ነው።

“እኔ Aim Ultra ን ለደቂቃ እንኳን አልተጠራጠርኩም። ማስታወቂያውን ታዋቂ ሰዎች በቲቪ እና በሶሻል ሚድያ ሲሰሩ ስላየሁ እውነት ይሆናል ብዬ ከቤተሰብ ያገኘሁት ገንዘብ ላይ ከብድር እና ቁጠባ ተጨማሪ በመበደር 520,000 ብር ከፈልኩ” ብሎ ለሚድያችን የተናገረው የማጭበርበር ድርጊቱ ሰለባ የሆነ ወጣት ነው።

መሠረት ሚድያ ለምርመራ ዘገባው ለበርካታ ቀናት ሲያሰባስብ የነበረው መረጃ እንደሚጠቁመው ይህ ድርጅት ከ600 በላይ ከሆኑ ሰዎች ከትንሹ 40 ሺህ ብር እስከ ከፍተኛው 680,000 ብር ተቀብሎ አሁን ቢሮውን ዘግቶ ጠፍቷል። እነዚህ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ድርጅቱ በትንሹ 120 ሚልዮን ብር ገደማ ከህዝብ ሰብስቦ ተሰውሯል።

ይህ Aim Ultra የተባለ ድርጅት ‘ካባ ሆልዲንግ’ በሚል ስም በህጋዊ መንገድ ከተቋቋመ እና በስሩ ቢያንስ አስራ ሁለት ከሚሆኑ ሌሎች ድርጅቶች አንዱ ነው።

ባለፉት ሁለት አመታት እንደ አርቲስቶች ሙሉአለም ታደሰ፣ ዳናዊት መክብብ፣ ሩታ መንግስተአብ፣ ቲክቶከሮች ዩቲ ናስ፣ ፊዮና ወዘተ ያሉትን በህዝብ ዘንድ የሚታወቁ ግለሰቦችን በመጠቀም ባሰራጨው ማስታወቂያ የተታለሉ ብዙዎች ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል።

ሚድያችን የደረሰው የተረጋገጠ መረጃ እንደሚጠቁመው ስማቸው አይጠቀስ የተባሉ ህይወታቸውን ያጠፉ ወጣቶች አሉ፣ ከክፍለ ሀገር በራሳቸው እና በቤተሰባቸው በኩል ተበድረው አዲስ አበባ መጥተው ከተጭበረበሩ በኋላ ወደመጡበት መመለስ ፈርተው እና አፍረው በመዲናዋ በሴት አዳሪነት የተሰማሩ ሴቶች ይገኛሉ፣ ‘ምን ብዬ ወላጆቼ ጋር ልመለስ?’ ብለው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የሚያድሩ እንዳሉም ደርሰንበታል።

Aim Untra ምን ቃል ገባ፣ የቱንስ ቃል አጠፈ?

ድርጅቱ የዱቤ እና የሙሉ ክፍያ አሰራርን በመተግበር ሰዎችን ለትምህርት እንደ ሩማንያ፣ ፖላንድ እና ሀንጋሪ ያሉ ሀገራት እንደሚልክ በስፋት ማስታወቂያ ሲያስነግር ቆይቷል።

እስከ 680,000 ብር ከፍለው የሚመዘገቡ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው እና ኬዛቸው አልቆ ትኬት በአራት ወር ግዜ ውስጥ እንደሚረከቡ እና እንደሚጓዙ ይነገራቸዋል። ሙሉ መክፈል ያልቻሉ ደግሞ ከ10 ፐርሰንት ጀምሮ እየከፈሉ በሂደት የሚቀርባቸውን ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ስራ ከጀመሩ በኋላ እንደሚከፍሉ ውል ይፈርማሉ።

“የግፋቸው ብዛት አንዳንዶቻችንን ይባስ ቪዛው መጥቷል፣ የትኬት ክፈሉ ብለው የሙሉ የአውሮፕላን ትኬት ጭምር አስከፍለውናል” የሚለው አንድ የድርጊቱ ሰለባ ወጣት ነው።

ከዛሬ አራት ወር ወዲህ ግን ድርጅቱ ቢሮውን መዝጋቱን፣ የድርጅቱ ሀላፊ ቤተልሄም ታደሰ እና ገሊላ በለጠ የተባለች የቢሮው ሀላፊ ስልክ ማንሳት እንዳቆሙ ተበዳዮች ይናገራሉ።

“እስካሁን አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌደራል ፖሊስ እና በፍትህ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት እና አቃቤ ህግ ቢሮ ሄደን አቤት ብለናል” ብለው ለመሠረት ሚድያ ቃላቸውን የሰጡ ተበዳዮች ተጠርጣሪዋ በወቅቱ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ እያለች ለምን እንዳልተያዘች ስንጠይቅ የሚሰጡን መልስ አስገራሚ ነበር ይላሉ።

“አንዴ ወንጀሉ ውስብስብ ነው ይሉናል፣ ሌላ ግዜ ሀገር ውስጥ የለችም ይላሉ። በጣም ያስገረመን አንዴ ደግሞ ‘በቦዲጋርድ’ ታጅባ ስለምትሄድ ነው አሉን። በቦዲጋር ታጅቦ የሚሄድ ወንጀለኛ አይያዝም ማለት ነው?” ብለው የሚጠይቁት እነዚህ ወጣቶች ‘ምርጥ ስራ ፈጣሪ’ ተብላ የተሸለመች እና በህጋዊ መንገድ ፈቃድ አውጥታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያጭበረበረች ግለሰብ የፀጥታ አካላት እንዴት ማግኘት እንዳልቻሉ ይጠይቃሉ።

ከአራት ቀናት በፊት ግን ይህ ለምን እንደሆነ መሠረት ሚድያ መረጃ ከፖሊስ አካላት ፍንጭ ደርሶታል፣ ይህም ጉዳዩ ላይ ክትትል የሚያደርጉ ፖሊሶች ስራቸው እንዳይሰሩ እና ግለሰቧን እንዳይዙ “ጫና አለ” ብለው ነግረውናል፣ ነገር ግን  ጫናው ከየት እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።

ተጠርጣሪዋ ቤተልሄም ‘Ethio Airs’ የተባለ እና የአዲስ አበባ መስተዳድር የከንቲባ ቢሮን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ቢሮዎችን በማፅዳት እና የተባይ ቁጥጥር በማድረግ የሚታወቅ ድርጅት ባለቤት ናት። ግለሰቧ በዚህ እና በሌሎች ድርጅቶቿ ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ጋር ትስስር እንዳላት የቀድሞው የድርጅቱ ሰራተኞች ይናገራሉ።

“አሁን አድራሻዋ ከመጥፋቱ በፊት ወደ ክስ እንሄዳለን ስንላት መልሷ ‘የትም ብትሄዱ አያዋጣችሁም፣ ራሳችሁ ትጎዳላችሁ’ ብላ ማስፈራርያ ትሰጠን ነበር” የሚሉት ከሳሾች በመጨረሻ የሄዱት ወደ ፍትህ ሚኒስቴር እንደነበር ያስረዳሉ።

እዛ ያገኟቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዴኤታ ፀሀፊ ጉዳዩን ለዴኤታው ካስተላለፉ በምላሹ “ጉዳዩን ወደ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ዳይሬክቶሬት ውሰዱ” እንዳሏቸው እና ወደ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ሀላፊ ሲሄዱ ደግሞ “ወንጀሉ ውስብስብ ነው” ብለው እንደመለሷቸው በተስፋ መቁረጥ ይናገራሉ።

በ Aim Ultra ለተጭበረበረው እና ስሜ አይጠቀስ ላለው ወጣት የደረሰው የአበዳሪው የአዋጭ የገንዘብ ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበር ማስጠንቀቂያ እንዲህ ይላል: “ውዝፍ እዳዎትን የማያስተካክሉ ከሆነ እርሶንም ዋሶትንም በገቡት ውል መሰረት ውዝፍ ዕዳውን በህግ አግባብ ለማስመለስ እየተዘጋጀን መሆኑን በጥብቅ እናሳስባለን።”

ወጣቱ ገንዘቡን እንዴት እንደሚመልሰው አያውቅም፣ የ Aim Ultra ቢሮም ተዘግቷል፣ ስልክ እንኳን የሚመልስ የለም።

“በብድርም ሆነ ንብረት ሽጠን መክፈል የቻልን የጠየቀችንን ገንዘብ በሙሉ ብንከፍልም መጨረሻ ላይ ‘አልተሳካም’ አለችን። እኔ በግሌ በ Aim Ultra 586,000 ብር ከፍያለሁ። ምንም ቪዛ ባልተመታበት ሁኔታ የአየር ቲኬት፣ የኮቴ እናም የትራቭል ኢንሹራንስ በሙሉ አስከፍላናለች። ለአንድ ዓመት ያክል ፕሮሰሱን ስከታተል የነበረው ደግሞ ከክፍለ ሀገር በአውሮፕላን (በጦርነት ምክንያት የየብስ ትራንስፖርት ዝግ ስለነበር) እየተመላለስኩ ነበር። በዚህም ለፕሌን እናም ለአልጋ ከ120,000 ብር በላይ አውጥቻለሁ” የሚለው ሌላኛው የማጭበርበር ድርጊቱ ሰለባ ነው።

በዚህ የማጭበርበር ተግባር ምክንያት የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ ትዳር ፈርሷል፣ ቤተሰብ ተበትኗል የብዙ ወጣቶች ህይወት ሲኦል ሁኗል የሚለው ይህ ወጣት እሱ ፕሮሰሱን ሲጀምር ቢያንስ 200,000 ብሩ የራሱ ገንዘብ እንደነበር ያስረዳል።

“ሌላው በተለያየ መንገድ የተቀበልኩት የቤተሰብ፣ የጓደኛ፣ ብሎም የእቁብ ብር ስለነበር ይሄንን መመለስ ባለመቻሌም ከቤት የመውጣት ሞራል አጣሁ። ስለእውነት አሁን ላይ ሙሉ ገንዘቤን ብትመልስልኝ እንኳን የማልሸፍነው እዳ ውስጥ ገብቻለሁ። ብዙ ነገር አጥቻለሁ። ከቤተሰብ ጋር ተቆራርጫለሁ። ገንዘብ በሰጡኝ ሰዎች ፊት አንገቴን ለመድፋት ተገድጃለሁ! ከአልጋ ላይ የምነሳበት ሞራል እያጣሁ ብዙ ቀኖችን አልጋዬ ላይ እያሳለፍኩ አለሁ! ጉዳዩ ከተበላሸ ጀምሮ ንጋትን እየፈራሁ አለሁ! ሁሉም ነገር ያደክማል! ከማስታወሻዬ ውጭ ለቅርብ ቤተሰቤ እንኳን አውርቼው የማላውቀውን ችግሬን እና መከፋቴን ሁሉ [ለቤተልሄም ታደሰ] በዝርዝር ነግሬያት ነበር እንኳንስ አዝና ገንዘቤን ልትመልስልኝ ለመልዕክቴ እንኳን መልስ አልሰጠችኝም” በማለት የደረሰበትን ፅፏል።

አክሎም “ሴትዮዋን ተከታትሎ ለመያዝም ሆነ ለማስያዝ ከባድ ያደረገው ሌላው ጉዳይ በተለያዩ የቤተሰብ አባል ፍቃድ ማውጣቷ ነው። መኖሪያ አድራሻም ስለምትቀያይር ማግኘት አልቻልንም። አንድ ድርጅት ትከፍት እና እሱን ትዘጋ እና በሌላ ሰው ስም በአዲስ ፈቃድ በአዲስ ስም ትመለሳለች እንዲህ እያለች ትቀጥላለች። በእርግጠኝነት ይቺ ሴትዮ በጊዜ በህግ ቁጥጥር ውስጥ ካልዋለች ገና ብዙ ግፍ እናም ማጭበርበሮች እንሰማለን” ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) እና ፋና ሬድዮ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የድርጅቱን ስም ብቻ በመጥቀስ የተበዳዮችን መረጃዎች እንዳጋሩ የተመለከትን ሲሆን ከዛ ወዲህ ምንም ለውጥ እንደሌለ እና ተጠርጣሪዋ አሁን ውጭ ሀገር (ምናልባትም ዱባይ) እንደምትገኝ ግምቶች ተሰጥተዋል።

ቤተልሄም በምትዘውራቸው ተቋማት ውስጥ ቁልፍ ሰዎች እንደሆኑ የተጠቆሙት በአብዛኛው የቤተብ አባል እና ጓደኛ የሆኑት ገሊላ በለጠ፣ በለጠ ሳህሉ፣ አቤል ተስፋዬ፣ ሩት መኮንን፣ ዳዊት በለጠ እና እዮሲያስ ታደሰ የተባሉ ግለሰቦች መሆናቸው ታውቋል።

መሠረት ሚድያ ቤተልሄም ታደሰ ይማምን በተለያዩ መንገዶች ለማነጋገር እና ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ምላሽ ባለመስጠቷ አልተሳካ።

መሀል አዲስ አበባ ላይ ፈቃድ አውጥተው ወጣቶችን ወደ አውሮፓ እንልካለን ብለው ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ ቢሯቸውን ዘግተው ከሚጠፉት ድርጅቶች በአንዱ ላይ ያሰናዳናው ዘገባ በዚህ ይጠናቀቃል።