ታዬ ደንድዐ ነፃ ተብለው የተሰናበቱባቸው ክሶች እንደ አዲስ አገርሽተው እንዲከላከሉ ተወሰነ

አቶ ታዬ ደንዳዓ ከዚህ ቀደም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነፃ የተባሉባቸው ሁለት የክስ ጭብጦች ተሻረ።

የአቶ ታዬ ዳንዳዓ የህግ ጥበቃ አበራ ንጉሱ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ” የፈዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት አቶ ታዬ ነፃ የተባሉባቸው ክሶችን በመሻር እንዲከላከሉ ትዛዝ ሰጥቷል ” ብለዋል።

” የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀር ሽብር እና ህግ መንግስት ጉዳዮች ችሎት 30/12/2016 ዓ/ም አቶ ታዬ ከተከሰሱባቸው ሶስት ክሶች ውስጥ አንደኛው ፤ ‘ በመንግስት ሀላፊነት ላይ እያሉ የህዝብ እና የመንግስት የተሰጣቸውን ሀላፊነት ወደ ጎን በመተው የፀር ሰላም ሀይሎች ሀሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማሰብ በግል ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው የታጠቁ ሃይሎችን የሚደግፍ መልዕክት አስተላልፈዋል ‘ የሚለውን መከላከል ሳያስፈልጋቸው ነፃ ተብለው ነበር ” ብለዋል ጠበቃቸው።

አክለውም የዋስትና መብታቸው በሰበር ሰሚ ችሎት ከተጠበቀላቸው በኃላ ከህግ ፍቃድ ውጭ የጦር መሳሪያ ይዘው መገኘት የሚለው አንዱን የክስ ጭብጥ እንዲከላከሉ በተሰጠው ብይን መሰረት በከፍተኛ ፍርድ ቤት እየተከታተሉ ነበር።

ሆኖም ዛሬ አቶ ታዬ ነፃ በተባሉበት ክስ ጭብጦች ላይ ቅሬታ እንዳለው የገለፀው አቃቤ ህግ ” ተከሳሹ በቂ ማስረጃ ቀርቦባቸው መከላከል ሲገባቸው ነፃ መባላቸው አግባብነት የለውም ” በማለት ለፈዴራል ጠቅላይ  ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት የኢትዮጵያ ወንጀል ህግ አንቀጽ 251/ሐ ጠቅሶ ይግባኝ ማለቱን ተከትሎ ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው ፍርድ ቤት ዛሬ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ነፃ የተባሉበትን ክሶች ብይን ሽሮ እንዲከላከሉ አዟል።

ጠቃቸው አቶ አበራ ንጉሱ ፤ ለውሳኔ ብቻ ዛሬ በአምስተኛ ተለዋጭ ቀጠሮ መገኘታቸውን ጠቅሰው ችሎቱ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን ሽሮ እንዲከላከሉ ብይን በመስጠቱ ቅሬታ እንዳላቸው ገልፀው በቀጣይ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ እንደሚሉ ገልፀዋል።

ይሁንና ደንበኛቸው ችሎት ተከታትለው ከተለያዩ ከቀትር በኃላ 10:00 በፌደራል ፖሊስ መወሰዳቸውን ከአቶ ታየ ባለቤት በስልክ እንደተነገራቸው ገልፀዋል።