የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለኢትዮጵያ የምሰጠውን ዕርዳታ ይበልጥ ለመቀነስ እገደዳለሁ አለ

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተረጂዎች የምሠጠውን ዕርዳታ ከእስካኹኑ ይበልጥ ለመቀነስ እገደዳለሁ በማለት ሰሞኑን ባሠራጨው መረጃ አስጠንቅቋል። በገንዘብ እጥረት ሳቢያ፣ በሚያዝያ ወር ለተረጂዎች የሠጠው የምግብ ዕርዳታ ከመደበኛው ኮታ 65 በመቶውን ብቻ እንደኾነና በተያዘው ወር ለስደተኞች የሚሠጠው የምግብ ኮታም ከመደበኛው 50 በመቶውን ብቻ እንደኾነም ድርጅቱ ገልጧል። ድርጅቱ፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የቀጠሉ ግጭቶች የደኅንነት ስጋት እንደደቀኑበት፣ ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያወጣቸውን ወጪዎች እንደጨመሩበትና የምግብ ዕርዳታን ለተረጂዎች ደኅንነቱ በተጠበቀ ኹኔታና በጊዜ እንዳያቀርብ እንቅፋት እንደፈጠሩበትም ጠቅሷል።