የመንጋ ፍርድ ይውደም! ሕግ ይከበር! #ግርማ_ካሳ

በምእራብ ጎጃም የዚያው አካባቢ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን፣ ሕዝብን ለማገልገል ሄደው፣ እዚያ ባሉ ጉጅሌዎች ተደብድበው ሞተዋል። የሞቱ ወገኖቼን ነፍስ ይማር እያሉ፣ ድርጊቱ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን አንገት የሚያስደፋ መሆኑ ለመግለጽ እወዳለሁ።

ለሌላው መቀጣጫ እንዲሆን ይሄን የፈጸሙ በአስቸኳይ ተይዘው ለፍርድ መቅረብ ብቻ ሳይሆን ፣ ለፍርድ እንደቀረቡ ዋጋቸውን እንደተቀበሉ በሜዲያ በግልጽ መዘገብ አለበት፡፡ሁሉም የክልሉ መንግስት ይህ አይነቱን ተግባር እንደማይታገስ፣ በክልሉ ቦታ እንደሌለው ማስየት መቻል አለበት። ያ ብቻ አይደለም፣ የክልሉ መንግስቱ ሃላፊነት ወስዶ በይፋ ይቀርታም መጠየቅ አለበት።

በአንጻራዊነት ከሌሎች ቦታዎች የተሻለውና የተረጋጋው የአማራ ክልል ነበር። በአማራ ክልል በሌላ ቦታ እንደምናየው የመንጋ ፍርድ እንዲኖር ፣ ከላይ እንደገለጽኩት፣ በምንም መልኩ ሊፈቀድ አይገባም። አሁን ነገሩ በቸልታ ከታየ ፣ አሁኑኑ የማያዳግም እርምጃ በመንጋ ፖለቲካ ላይ ካልተወሰደ ነገ የሚሻሻል ነገር አይኖርም። የመንጋን ፖለቲካ ማባባል ምን እንደሚስከትል የአማራ ክልል ከነ ለማ መገርሳ መማር አለብት።

ከዚህ በታች የምታዩት ወንድም፣ ጦማሪ ጥላሁን ግርማ አንጎ እንደ ጦምረው፣ ተደብድቦ የተገደለ አንዱ ወንድማችን ነው። ወሰን ይባላል። በአውሮፓ በቤልጅየም የ ማስተርስ ድግሪውን ካጠናቀቀ በኋላ፤ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሥራ ጀመረ ፣ ከሐዋሳ ወደ ፓስተር የጤና ኢንስቲትዩት ተዛውሮ አገለገለ። ከፓስተር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ3 አመት በፊት ተዛወሮ ማገልገል ጀመረ። ለዶክትሬት ማሟያ ጽሁፉ የመረጠው የምርምር ቶፒክ …. በአማራ ሀገር፤ በተለይም ተወልዶ ባደገበት ምእራብ ጎጃም አካባቢ ያስቸገረ የትራኮማ በሽታ ለማጥፋት የሚል ነበር። ለዚሁ የ ዶክትሬት ማሟያ ጽሁፉ የሚሆነውን ዳታ(መረጃ) ለመሰብሰብ ወደ ተወለደበት ምእራብ ጎጃም ገጠር ሻንጣና ላፕታፕ ኮምፕዩትሩን ሸክፎ ሄደ! እዚያ ሄዶ ግን አልተመለሰም!!! ደብደበው ገደሉት።