ብሪታኒያ ጀርመን እና ፈረንሳይ ዜጎቻቸው አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መከሩ

የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር በኩል ረቡዕ ምሽት ባወጣው ማሳሰቢያ ዜጎቹ የንግድ በረራዎችን በመጠቀም “አሁን” ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ጠየቀ።

ሚኒስትሯ ቪኪ ፎርድ እንዳሉት ግጭቱ እየተባባሰ በመሄዱ “ጦርነቱ ወደ አዲስ አበባ እየቀረበ ሊመጣ ከቻለ ከኢትዮጵያ ለመውጣት ያሉ አማራጮች ውስን ሊሆኑ ይችላሉ” ብለዋል።

ስለዚህም ሁሉም የብሪታኒያ ዜጎች በረራዎች ባሉበትና የቦሌ አየር ማረፊያ ክፍት ሆኖ እየሰራበት ባለበት ጊዜ በአስቸኳይ እንዲወጡ፣ ገንዘብ ለሌላቸውም የአየር ትኬት ብድር መመቻቸቱንም ገልጸዋል።

ጨምረውም “ከኢትዮጵያ ለመውጣት የማይፈልጉ ከሆነም በሚቀጥሉት ሳምንታት ለደኅንነታቸው አስተማማኝ በሆነ ስፍራ እንዲቆዩ” መክረዋል።

ቀደም ሲልም ጀርመን እና ፈረንሳይ ዜጎቻቸው አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የመከሩ ሲሆን ሌሎች አገራትም በተመሳሳይ ዜጎቻቸው ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ የመከሩ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም አንዳንድ ሠራተኞቹን በጊዜያዊነት ማዛወሩን ገልጿል።

አገራቱ ይህንን ጥሪ እያቀረቡ ያሉት የትግራይ ተዋጊዎች ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እያመሩ መሆናቸውን ባስታወቁበትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማፂያኑን ለመዋጋት ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን እመራለሁ ባሉበት ወቅት ነው።

በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልል የተዛመተው ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስከተሉን ቀጥሏል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በረሃብ አፋፍ ላይ ሲሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታትና የእርዳታ ድርጅቶች አመልክተዋል።

የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄዎች ላይ መሻሻሎች ቢታዩም መሬት ላይ ያለው ጦርነት መባባስ ሁኔታውን ስጋት ላይ ጥሎታል ብለዋል።

ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በወታደራዊ ድል አፋፍ ላይ መሆናቸውን ያመኑ ይመስላሉ ብለዋል ልዩ መልዕክተኛው።

ፌልትማን አማጽያኑ ወደ አዲስ አበባ የሚጠጉ ከሆነ ተቀባይነት የሌለው እና አስከፊ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

ከጦር ግንባሩ የሚወጡ ዘገባዎች ለማጣራት ቢከብዱም ህወሓት ተዋጊዎቹ ከአዲስ አበባ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማን መቆጣጠራቸውን ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል የአማጺያኑን ድል ዘገባን አስተባብሏል።

“ግንባር ላይ እንገናኝ”

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎቿ አማራጭ የንግድ በረራዎችን በመጠቀም መውጣት አለባቸው ሲል ፈረንሣይ በበኩሏ ዜጎቿ “ሳይዘዩ” አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አሳስባለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጣዊ የደኅንነት ሰነድ “ብቁ የሆኑ የዓለም አቀፍ ሠራተኞች ቤተሰብ አባላት” እስከ ኅዳር 16/2014 ዓ.ም ድረስ አገሪቱን ለቀው መውጣት አለባቸው ብሏል።

ቀደም ሲል አሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደም አስፈላጊ ያልሆኑ የዲፕሎማቲክ ሠራተኞች እያስወጡ መሆኑን አስታውቀው ሌሎች በአገሪቱ የሚገኙ ዜጎቻቸውም አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኖቤል የሰላም ሽልማት ያገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ሰኞ ማምሻውን ባስተላለፉት መልዕክት የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምራት ወደ ጦር ግንባር እንደሚሄዱ ገልጸዋል።

“ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ” በማለት ሌሎችም የእሳቸውን አርአያ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ድላቸውን ያገኙት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ተከትሎ ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀው ውጥረት ማክተሚያ መፍትሄ በመሆናቸው ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ግንባር በመሄድ ጦሩን እመራለሁ ማለታቸውን የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ አጣጥለውታል።

“የእኛ ኃይሎች በሕዝባችን ላይ ያለውን (የዐብይን) ማነቆ ለማብቃት እያደረጉት ካለው ግስጋሴ አይመለሱም” ብለዋል አቶ ጌታቸው።

ጦርነቱ በድርድር እንዲቋጭ የአፍሪካ ሕብረት ጥረቶችን እያደረገ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች ለውይይት ቁርጠኛ አይደሉም።

ለጦርነቱ ዋነኛ መነሻ የሆነው በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እና ትግራይን ብቻ ሳይሆን መላ አገሪቷን በበላይነት ይመራ በነበረው ህወሓት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ በጠላትነት ሲተያዩ ከነበሩት ኤርትራ ጋር እርቅ መፍጠርና ሌሎች ማሻሻያዎችን አካሂደዋል። በዚህ ወቅት ህወሓት ወደ ጎን ገሸሽ ተደርጓል።

በህወሓትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል የከረመው መሻከርም ወደ ጦርነት አምርቷል።

ከዓመት በፊት የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል እንዲሁም መሳሪያ ዘርፈዋል በሚልም የፌደራል መንግሥቱ ወታደራዊ ምላሽ ሰጥቷል።