የአሜሪካው የእርዳታ ድርጅት ከኢትዮጵያ ሊወጣ ነው የተባለው ሐሰት ነው ሲል አስታወቀ።

የአሜሪካው የእርዳታ ድርጅት ዩኤስኤይድ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አቁሞ ከአገሪቱ ሊወጣ ነው የተባለ ሐሰት ነው ሲል ለቢቢሲ አስታወቀ።

ዩኤስኤይድ እየተካሄደ ባለው ጦርነት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ አቅርቦቶችን ማቅረብ መቀጠሉን አስታውቋል።

የተቋሙ ቃል አቀባይ ሬቤካ ክሊፍ፤ “የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሠራተኞቻችን ከአገሪቱ ቢወጡም፤ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ከሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ጋር በቅርበት እየሰራን እንገኛለን” ብለዋል።

የሰላም ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ የሆኑት ታዬ ደንደዓ ከቀናት በፊት የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት ዩኤስኤይድ ኢትዮጵያን ለቆ ሊወጣ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ሚንስትር ዲኤታው በፌስቡክ ገጻቸው ላይ፤ “መልካም አጋጣሚ ሆኖ ዩኤስኤይድ ከኢትዮጵያ ሊወጣ ነው ተብሏል” ካሉ በኋላ የዩኤስኤይደ ከኢትዮጵያ ለመውጣት ምክንያቱ፤ “መንግሥት የሁመራ ኮሪዶርን አልከፍትም ማለቱ ነው” ሲሉ ጨምረው ጽፈው ነበር።

የዩኤስኤይድ ቃል አባይ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በሰብዓዊ ስራው እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ አሜሪካ ከየትኛው ተቋም በላይ የሰብዓዊ እርዳታ ስታቀርብ መቆየቷን አስታውሰዋል።

“ከተቀስቀሰ ጀምሮ [የትግራይ ጦርነት] አሜሪካ ከየትኛው ተቋም በላይ ግዙፍ የተባለውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት አድርጋለች። ድርጅቱ 663 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ አድርጓል” ብለዋል ቃል አባይዋ ሬቤካ ክሊፍ።

ቃል አቀባይዋ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ፤ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የተለያዩ እክሎች እንደሚገጥማቸው አንስተዋል።

“አጋር ድርጅቶቻችን ከመንግሥት ጨምሮ ጠንካራ እክሎች ይገጥማቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የደህንነት ችግር አለ። እንዚህ እክሎች ዩኤስኤይድ እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጓቸው ሰዎች እርዳታ እንዳይደርሱ ፈተና ይሆናሉ” ብለዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት የተቀሰቀሰው የትግራይ ጦርነት ወደ አጎራባች ክልሎች ተስፋፍቶ ቀጥሏል።

የፌደራሉ መንግሥት ከህወሓት አማጺያን ጋር እያደረገ ያለው ጦርነት በድርድር እንዲፈታ ምዕራባውያን አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ድምጻቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ወደ ትግራዩ ጦነርት ተገዶ መግባቱን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

ምዕራባውያን በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እንዲቆምና ሰብአዊ እርዳታ በችግር ላይ ላሉ ሰዎች ያለገደብ እንዲደርስ ጫና እያደረጉ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ለአማጺያን ድጋፍ በማድረግ የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ እየሞከሩ ነው ሲል ይከሳል