የተመድ ፖፒዩሌሽን ፈንድ የኢትዮጵያ ኃላፊ ዴኒአ ጌይል ለሕወሓት ድጋፍ ይሰጣሉ በተባሉ ከፍተኛ የተመድ ባለስልጣናት ጫና እንደሚደረግባቸው ተናገሩ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ያልተገባ አስተያየት ሰጥተዋል ያላቸውን ሁለተኛዋን የተመድ የኢትዮጵያ ኃላፊን ጠራ።

የተመድ ፖፒዩሌሽን ፈንድ የኢትዮጵያ ኃላፊ ዴኒአ ጌይል መጠራታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ትናንት ምሽት ዘግቧል።

ትናንት የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ “የድርጅቱን እሴቶች የማያንጸባርቅ” አስተያየት በመስጠታቸው ምክንያት አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስዱ መደረጉን ተቋሙ ለቢቢሲ አስታውቆ ነበር።

የፖፒዩሌሽን ፈንድ እና አይኦኤም ኃላፊዎች ለትግራይ ኃይሎች ርህራሄ አላቸው ባሏቸው የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ጎን ገሸሽ ተደርገናል ስለማለታቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ሁለቱ በኢትዮጵያ የተመድ ከፍተኛ ኃላፊዎች የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ በመደገፍ በርካታ መጣጥፎችን ለሚፅፈው ጄፍ ፒርስ ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል።

በቃለ መጠይቁ ላይ እንደሚሰማው የአይኦኤም ኃላፊ ማውሪን ጦርነቱ ከተነሳ በኋላ አዲስ አበባ የገቡ የተባበሩት መንግሥታት የሥራ ባልደረቦቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በመተቸት መሬት ላይ ያሉ የድርጅቱ ተወካዮችን አግልለዋል ብለዋል።

ህወሓትንም “ቆሻሻ” እና “ጨካኝ” በማለትም ሲናገሩም ይሰማል።

በአንድ ወቅትም ህወሓት ከሳዑዲ አረቢያ የተባረሩ የትግራይ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ እንዲላኩ አሲረዋል በማለትም ሲከሱ ይሰማል።

ማውሪን አቺየንግ
የምስሉ መግለጫ, ማውሪን አቺየንግ

የፖፒዩሌሽን ፈንድ ኃላፊዋ ጌይል ደግሞ ኢትዮጵያ የገቡ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪዎች አዲስ አበባ የሚገኙ ከፍተኛ የተመድ ኃላፊዎችን በማለፍ የተመድ ዋና መስሪያ ቤት ካሉ ኃላፊዎች ጋር በቀጥታ ይገናኛሉ ይላሉ። ይህም የሚያመለክተው “በተመድ ውስጥ የስልጣን ሽኩቻ” ስለመኖሩ ሲሉ ጌይል ይሰማሉ።

የኢትዮጵያ የፖፒዩሌሽን ፈንድ ኃላፊ ዴኒያ ጌይል እና የአይኦኤም ኃላፊዋ ወደ ኒው ዮርክ መጠራታቸው በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነት ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚደረገውን ሥራ የበለጠ እንደሚያውከው ተጠቅሷል።

ተመድ በኢትዮጵያ የአይኦኤም ኃላፊን በጠራበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት በውሳኔው ደስተኛ አለመሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ አቀባይ ቢልለኔ ስዩም አመላክተው ነበር።

ቢልለኔ በትዊተር ገጻቸው ላይ፤ “የተባበሩት መንግሥታት ሥርዓት ከሽብርተኛው ቡድን ህወሓት ጋር ባለው ግንኙነት ተቋማዊ አድሏዊነትን መከተሉን በግልፅ በመናገራቸው ማውሪን አቺየንግ ላይ የተጣለው አስተደዳራዊ እረፍት በጣም የሚረብሽ ነው” ብለው ነበር።

አክለውም “በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች ያለው ውስጣዊ እና የውጭ ተፅእኖ ፓለቲካ በጥልቀት መመርመር እንዳለበት” በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

ኢትዮጵያ ከሰሞኑ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ቀውስ ጋር ተያይዞ በወገንተኝነትና እንዲሁም ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ደቅነዋል ያለቻቸውን የተመድ ሰባት ሠራተኞች ከአገር እንዲወጡ ማድረጓ ይታወሳል።