የቬይና ማራቶን ያሸነፈው ኢትዮጵያዊ ውጤቱ ተሰረዘበት

የቬይና ማራቶን ያሸነፈው ደራራ ሁሪሳ ያልተፈቀደ ጫማ አድርጎ በመሮጡ ውጤቱ ተሰረዘበት።

አትሌት ደራራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ደራራ ውድድሩን ካሸነፈ ከ45 ደቂቃዎች በኋላ የውድድር ደንብን በመጣሱ ውጤቱ እንደተሰረዘበት ተነግሮታል።

ያልተፈቀደ ጫማ

ትናንት በወንዶች የቬይና ማራቶንን አሸንፎ የነበረው አትሌት ደራራ ሁሪሳ ተጨምቶት የነበረው የጫማ ሶል (መርገጫው) ከሚፈቀደው በላይ አንድ ሳንቲ ሜትር ወፍሮ በመገኘቱ ውጤቱ ውድቅ ተደርጎበታል።

አትሌት ደራራ ውድድሩን 2፡09፡22 በሆነ ሰዓት ቢያጠናቅቅም ከ45 ደቂቃዎች በኋላ የውድድር ደንብን በመጣሱ ውጤቱ እንደተሰረዘበት ተነግሮታል።

የውድድሩ አዘጋጆች አትሌቶች መጫመት የሚችሉት የጫማ ሶል ውፍረት 4 ሳንቲ ሜትር መሆን አለበት ይላሉ። አትሌቱ ግን ተጨማምቶት የነበረው የጫማ ሶል 5 ሳንቲ ሜትር የሚወፍር መሆኑን ሮይተር የዜና ወኪል የውድድሩን አዘጋጆች ጠቅሶ ዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪም አትሌት ደራራ ከውድድሩ መጀመር በፊት በሞላው ቅጽ ላይ ከሞላ የተለየ ጫማ አድርጎ ወደ ውድድሩ ስለመግባቱ ተመልክቷል።

“በቴክኒክ ስበሰባ ላይ በጫማ ዙሪያ ያለውን መመሪያ ትኩረት ሰጥተና ተናግረናል። አለመታደል ሆኖ የአትሌቱን ውጤት ከመሰረዝ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረንም” በማለት የውድድሩ አስተባባሪ ሃነስ ላንገር ተናግረዋል።

“እንደዚህ አይነት ነገር ሲከሰት ይህ የመጀመሪው ነው። በውድድሮች ላይ እንደዚህ አይነት ነገር እንዳይከሰት ቀድሞ ማጣራት የሚቻልበት አሰራራ ከአሁን በኋላ ይኖራል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ የውድድሩ አዘጋጅ ተናግረዋል።

ከአትሌት ደራራ ቀጥሎ በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ኬንያዊው ሊኦናርድ ላንጋት የውድድሩ አሸናፊ ተብሏል።

“የአትሌቱ ውጤት እንደተሰረዘ አልሰማሁም ነበር። ውድድሩን ለማሸነፍ አቅጄ ነበር። በመጨረሻ በማሸነፌ ፈጣሪን አመሰግናለሁ” ብሏል ኬንያዊው አትሌት ላንጋት።

ይህ ውድድር በየዓመቱ ሚያዚያ ወር ላይ ይካሄደ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት መካሄዱ በበርካታ አትሌቶች ተቃውሞን አስተናግዶ ነበር። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከፍተኛ ሙቀት ነው።

በግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረ አትሌት ሕይወቱ ስለማለፉም ተሰምቷል። የውድድሩ አዘጋጆች እንዳሉት ከሆነ፤ የ40 ዓመቱ የኦስትሪያ አትሌት ውድድሩን ከጨረሰ በኋላ ራሱ ስቶ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

የውድድሩ አዘጋጆች በክስተቱ እጅጉን ማዘናቸውን ከመግለጽ ውጪ ስለ አትሌቱ አሟሟት ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

አትሌት ሰንበሬ ውድድሩን ካሸነፈች በኋላ

አትሌት ሰንበሬ የ5 ኪሎ ሜትር ውድድሯን ከዚህ ቀደም በኬንያዊቷ አትሌት ብትሪስ ቼፕኮኤች በ14፡44 ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን 14፡30 በሆነ ሰዓት ማሻሻል ችላለች።

በቶኪዮ ኦሊምፒክ 5ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃ የነበረችው አትሎት ሰንበሬ “በጣም ደስታ ተሰምቶኛል” ያለች ሲሆን፤ “ከኦሊምፒክ በኋላ ይህን የዓለም ክብረ ወሰን ማሻሻል እንደምችል ገብቶኛ” ስለማለቷ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪ ትናንት ኬንያዊቷ አትሌት አግነስ ቲሮፕ ጀርመን በተካሄደው ውድድር የ10 ኪሎ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን ማሻሻል ችላለች።

አትሌት አግነስ በሞሮኮ አትሌት አሰማኤ ሌግህዛኦዩ ከ19 ዓመት በፊት ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በ28 ሰከንዶች በማሻሻል 30፡17 በሆነ ሰዓት ውድድሯን አጠናቃለች።