ለዘላቂ ሰላም የሚንቀሳቀሰው የአማራ ልዩ ኃይል መተከል ገባ

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ እንደገባና አቀባበል እንደተደረገለት ቡለን ወረዳ አሳውቋል።

የቡለን ወረዳ በይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገፁ ፥ “ለዘላቂ ሰላም የሚንቀሳቀሰው የአማራ ክልል ልዩ ሀይል በቡለን ከተማ አቀባበል ተደርጎለታል” ሲል ፅፏል::

ወረዳው በአቀባበሉ ላይ የቡለን ወረዳ ወጣቶች፣ ነዋሪው፣ ማህበረስቡና የሴክተር መስርያ ቤት ሰራተኞችና አመራሩን ጨምሮ ከከተማው 1 ኪ/ሜትር ወጣ ብሎ በመሄድ አቀባበል አድርገዋል ሲል ገልጿል።

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ወደቡለን ወረዳ መግባቱ በወረዳው ያለውን የፅጥታ ችግር ለመፍታት፣ ማህበረሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ለማድረግ አስተዋጽዖ ያደርጋል ተብሏል።

ቡለን ወረዳ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ የፀጥታ ስጋት ካለባቸው ወረዳዎች አንዱ ሲሆን በተደጋጋሚ ጊዜ የታጠቁ ኃይሎች በሚፈፅሙት ጥቃት ንፁሃን ተገድለውበታል፣ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደውበታል::