ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፍቃደኛ ባልሆኑ 21 የመንግስት ሰራተኞች ክስ ሊመሰረትባቸው ነው።

በ2013 በጀት ዓመት 21 የመንግስት ሰራተኞች ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ስም ዝርዝራቸው ለፍትህ አካላት መላኩን የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታውቃል፡፡ ሀብት ለማስመዝገብ አልተባበሩም የተባሉት ግለሰቦች ክስ ይመሰረትባቸዋል ነው የተባለው።

ከዛሬ 11 ዓመታት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት ጸድቆ ስራ ላይ በዋለው አዋጅ የፌደራል መንግስት እና የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞችን እንዲሁም የህዝብ ተመራጮች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

ይህንን ተከትሎ የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለፈው የ2013 በጀት ዓመት 629 ሺህ 625 የሚሆኑ የመንግስት ተሿሚዎች፣የህዝብ ተመራጮች እና ሁሉም የፌደራል መንግስት ሰራተኞች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ እና እንዲያሳድሱ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።

በበጀት ዓመቱ ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፍቃደኛ ያልሆኑ ሀብት አስመዝጋቢዎችን ተጠያቂ ለማድረግ በተደረግ ጥረት 3 ሚሊዮን 601 ሺህ ብር በቅጣት ተሰብስቦ ለገንዘብ ሚኒስቴር ገቢ መደረጉን የኮሚሽኑ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ መስፍን በላይነህ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።