አቶ በቀለ ገርባ፣ ምነው እንዲህ አይነት የወረደ አስተሳሰብ ውስጥ ወደክ? (አቡ ሳለም)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

ከአቡ ሳለም

የት ይደርሳል የተባለን ዛፍ ቀበሌ ቆርጠው እንዲል ይህ ትውልድ አንተም በቀበሌኛ መጥረብያ ከብዙዎች ልብ ተቆረጥህ። ለመሆኑ በኦርምኛ ብቻ የተጻፉትን ጹሑፎች ካላነበብክ በቀር ፊንፊኔ የሚለው የቀደመ የአዲስ አበባ መጠርያ የመጣው በእቴጌ ጣይቱ ምክንያት እንደሆነ እና ይኸውም ከፍል ውሃ አካባቢ ጋር የተያያዘ መሆኑን ይሄ ጠፍቶህ ነው?

እቴጌይቱ ከእንጦጦ ወርዳ ይህን አካባቢ ባየች እና የፍል ውሃ ወደ ላይ ፊን ፊን ሲል ባየች ግዜ “ፊን ፊን ” ስትል አካባቢውን ጠራችው እናም እየቆየ ሲሄድ በአካባቢው ነዋሪዎች(ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ይሁኑ አይሁኑ ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም) ምክንያቱም ኦሮምኛ እሰማለሁ እናገራለሁ ግን ይሄ ቃል ኦሮምኛ ስለመሆኑ አላውቅም እንደውም ፊን ፊን ወደ አማርኛው ያደላ ወይም በሁለቱ መሃል ነው።

በሌላ በኩል እቴጌይቱ ከኦሮሞና ከአማራ ዘር የሚመዘዙ እንደሆነ የሚናገሩ የታሪክ ፀሃፊዎች አሉ። እናም ኦሮሞ እንደቆረቆራት ከተማ ለመወሰድ አያስኬድም ከእቴጌይቱ በፊት የተቆረቆረች ከተማ ነች የሚሉ ከሆነ ከዝያ በፊት የነበረውን ስሟን እና መከራከሪያ ነጥቡን እንወቀው።

አለም በመኃሏ ያለውን አርቴፍሻል ወሰን እየናደች ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ እና ፓለቲካዊ ትስስር እየተፈጠረ ባለበት በ21ኛው ክ/ዘመን ዝም ብሎ የኛ የኛ እያሉ ሌሎች ባለቤት እንዳልሆኑ በድፍረት መናገር አሳፋሪም የእውቀት እጥረትም ነው። ካለበለዝያም የዘረኝነት በሽታ። ኦሮሚያ ወይም ኦሮሞ ከአዲስ አበባ ማግኘት ያለበትስ ጥቅም ምንድነው? ለምን? ጣልያን አዲስ አበባን ይዞ በነበረበት ግዜ የጣልያንን ሹማምንት በጨበጣና በቦንብ በልዩ ልዩ መንገድ እየተፋለሙ ያርበደበዱ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ኦሮሞዎች ብቻ ነበሩ እንዴ? ሌላው ይቅርና አዲስ አበባን እያስጨነቀ የነበረውን ግራዝያኒን እና ወታደሮቹን በቦንብ የናጡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም ኦሮሞዎች ነበሩ እንዴ? ኤርትራስ ልጄ ለአዲስ አበባ እና ህዝቦቿ ሲል በአዲስ አበባ ተሰውቶአልና ልዩ ጥቅም ከአዲስ አበባ ወይም ከኦሮሚያ ማግኘት አለብኝ ብላ መጠየቅ አለባት? ያ ሁሉ 30 ሺህ ህዝብ በግራዝያኒ በግፍ የተጨፈጨፈው ሁሉሞ ኦሮሞ ብቻ ነው ? በፍፁም ስለዚህ አዲስ አበባ የኦሮሞም ወይ የአማራ የማንላት የሁሉም ናት እንደውም ከኦሮምያም ሆነ ከሌሎቹ ልዩ ጥቅም የሚገባው ለአዲስ አበባ ነው እንበል?

አቶ በቀለ እባክህ ከቻልክ አለም አቀፍ ግንዛቤ ካልተቻለ አገር አቀፍ ግንዛቤና መግባባት ይዘህ ለሃገርህ ለመስራት ሞክር ካለበለዝያ ከንቱነት ነው።

አንተ እራስህ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ ። እናም በሁለት እግር የሚንቀሳቀስ ክምር አፈር (እጩ ፈራሽ) የሚራመድበትን አፈር የኔ ብቻ ነው ሲል ከንቱነት ነው።