አዲሱ የአሜሪካ ሹም በትግራዩ ቀውስ ዙሪያ ግጭት ቆሞ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ እስከ ድርድር የሚደርስ ሀሳብ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።

ዋዜማ ራዲዮ– የአሜሪካ መንግስት የአፍሪቃ ወንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፊልትማን በትግራይ ቀውስና በሌሎች ክፍለ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ሰኞ ዕለት ወደ ምስራቅ አፍሪቃ አምርተዋል።

በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተሰየሙት ልዩ መልዕክተኛው ፊልትማን የትግራይን ጦርነት ጨምሮ በሕዳሴው ግድብ በሱዳንና በኢትዮጵያ የድንበር ውዝግብ ዙሪያ መፍትሄ የማፈላለግ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል።

በአንድ ሳምንት ቆይታቸው ሱዳንን ግብፅን ኤርትራንና ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ። ከየሀገራቱ ባለስልጣናት ጋር የመነጋገር መርሀ ግብር እንዳላቸውም ከአሜሪካ የወጪ ጉዳይ መስሪያቤት የገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ልዑኩ በትግራዩ ቀውስ ዙሪያ ግጭት ቆሞ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ እስከ ድርድር የሚደርስ ሀሳብ እንዳላቸው በስፋት እየተነገረ ነው።በአዲስ አበባ ከአፍሪቃ ህብረትና ከመንግስታቱ ድርጅት ሀላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ተነግሯል።

ጄፍሪ ፊልትማን አንጋፋ ዲፕሎማት ሲሆኑ የመንግስታቱ ድርጅት የፖለቲካና የፀጥታ አማካሪ በመሆን ስርተዋል። በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለይም በሶሪያና ሊባኖስ ጦርነት ቆሞ ሰለም እንዲመጣ በተደረጉ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ዋና ልዑክ በመሆን አገልግለዋል።[ዋዜማ ራዲዮ]