የትሕነግንና ጽንፈኛ የኦነግ-ሸኔ ኃይሎችን በሽብርተኝነት ስንፈርጅ አገራችንና ሕዝባችን እነሱ ባቋቋሙት ሥርዓት የተተከለውን ትርክት፣ ሕገ-መንግስትና መዋቅር ተሸክመው የሚቀጥሉበት አመክንዬ ሊኖር አይችልም።


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የትሕነግንና ጽንፈኛ የኦነጋዊ-ሸኔ ኃይሎችን በሽብርተኝነት ስንፈርጅ አገራችንና ሕዝባችን ዘረኞች ባቋቋሙት ሥርዓት የተተከለውን ትርክት፣ ሕገ-መንግስትና መዋቅር ተሸክመው የሚቀጥሉበት አመክንዬ ሊኖር አይገባም!የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ
******
የኢፌዲሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ትሕነግና ኦነግ-ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ምክረ ኃሳብ ማቅረቡ ታውቋል።

ትሕነግና ኦነግ-ሸኔ ከመጀመሪያው ጀምሮ በሕዝብ ላይ በጥላቻ ትርክት ተመስርተው ወገኖቻችንን በግፍ ሲጨፈጨፉና ለሕዝብና ለአገር አዋራጅ የሆኑ በርካታ ጅምላ ጥቃቶችን ሲፈጸሙ ቆይተዋል። በተጨማሪም እነዚህ በሕዝብ ጥላቻ የናወዙ ኃይሎች የአገራችንን ክብርና አጠቃላይ የስብዕና እሴቶችን ያራከሱ ተግባራትን መፈጸማቸው እና ዛሬም እየፈጸሙ ሁሉም የሚያውቀው እውነታ ነው።

ትሕነግና ኦነግ-ሸኔ የአገራችን ሕዝቦች ዘመናትን የተሻገሩ የጋራ በጎ ቁርኝቶችና የአርበኝነት ባሕልን በእጅጉ ያጎደፉ፣ በረጅሙ የነፃነት ታሪካችን መካከል በተፈጠሩ የታሪክ ክፍተቶች ሾልከው የገቡ የአገርና የሕዝብ እንዲሁም አጠቃላይ የስብዕና ጠንቅ ናቸው።

ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እነዚህ አደረጃጀቶች በሽብርተኝነት መፈረጅ እንዳለባቸው፣ ቀጣይ በሚኖረው አገራዊ የውይይትና የድርድር መድረክ ውስጥ መካተትና መሳተፍ እንደሌለባቸው፣ ጉዳያቸው በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ ብቻ ሊስተናገድ እንደሚገባው እና ለዘመናት በሕዝብና በአገር ላይ ከፈፀሙት ዘርፈ-ብዙ ዘግናኝ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አሻጥሮች፣ አጠቃላይ ጥቃቶች በተለይም ከዘርና እምነት ተኮር ጅምላ ፍጅቶች አንፃር «አገራዊ የሽግግር ፍትኅ» (Transitional Justice) በማቋቋም መዳኘትና ለተፈፀሙ ጉዳቶች ማካካሻ ማድረግ እንደሚገባ ግልፅ ማሳሰቢያ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል።

ስለሆነም፦

1/ አብን ስትራቴጂክ ትንተና ላይ ተመስርቶ አቅርቦት የነበረው ኃሳብ ላይ በጊዜው ምርመራ ተደርጎና አቋም ተወስዶበት የመፍትኼ አቅጣጫ ተቀምጦ ቢሆን ኖሮ በመካከል የደረሰውን አገራዊ ምስቅልቅል እንዲሁም ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ መቀነስ ወይም ማስቀረት ይቻል እንደነበር በማመን፤

2/ ትሕነግና ኦነግ-ሼኔ በየአጽናፉ ላሰማሯቸው ቅጥረኞች ግልፅ የሆኑ የኃሳብና የቁስ ድጋፎችን በማድረግ የተቀናጀው አፈናና ጥቃት አድማሱን ሲያሰፋ በተጓዳኝ የአገራችን የነፃነት ቀጠና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጣበበ በአሁኑ ሰአት ችግሩ የብሔራዊ ደኅንነት ግንባር ቀደም አደጋ መሆኑን በተደጋጋሚ ያቀረብነውን ኃሳብ ትክክለኛነት ያረጋገጠ መሆኑን በማመን፤

3/ ከሁሉም በፊት ትሕነግና ጽንፈኛ ኦነጋዊ ኃይሎች በሕዝብና በአገር ላይ የአሻጥርና የጥቃት ዘመቻ መክፈት የጀመሩት እንደሚባለው ከሦስት ዓመት ወዲህ ሳይሆን ላለፉት ከሰላሳ ዓመታት በላይ መሆኑን መተማመን ስለሚያስፈልግ፤

4/ በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በእነዚህ ኃይሎች እየተፈፀሙ ያሉት የተቀናጁ ጥቃቶች በዋናነት በአማራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠሩ ተከታታይ «የዘር ማጥፋት» ወንጀሎች መሆናቸውን መቀበልና በትክክለኛ ስማቸው መጥራት እንደሚገባ በማመን፤

5/ እንደሚታወቀው ጥቃቶቹና ጥፋቶቹ በግንባር ቀደም የሚፈፀሙት በትሕነግና በኦነግ-ሸኔ ቢሆንም እስካሁን ወጥ በሆነ ሁኔታ እንደተረጋገጠው በአገር ውስጥና በተለያዩ የውጭ አገራት የሚገኙ ግለሰቦችና ተቋማት የኃሳብና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የፕሮፖጋንዳ ሽፋን በመስጠት በሰፊው ትብብር የሚያደርጉ በመሆኑ፤

6/ የሽብርተኞቹን የጥላቻ ትርክት በተለያዩ ስልቶች የሚያስተጋቡና ድጋፍ የሚያደርጉ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትና አመራሮች እንዲሁም የስልጠና እና የገንዘብ እንዲሁም የመረጃ ድጋፍ የሚያደርጉ የአስተዳደርና የደኅንነት መዋቅሮችና አመራሮች መኖራቸውን በመተማመን፤

7/ በዘመነ ኢሕአዴግ በሽብር ስም ሲፈፀም የነበረውን የፖለቲካ ጥቃትና የኃሳብ ልዩነትን ለማፈን የመብት ጥሰት የሚያስከትሉ እንቅስቃሴዎች እንዳይኖሩ በማሳሰብ፤

8/ ወቅታዊውን የፖለቲካ ትኩሳት ለማብረድና በተለይም መንግስታዊና ሕጋዊ ኃላፊነትን እንደተለመደው ለጊዜያዊ የምርጫ ቅስቀሳ ፍጆታ ለማድረግ ከመሞከር መታቀብ እንደሚገባ እያሳሰብን፤

9/ ጥያቄውን የአማራ ሕዝብ በተለይም እንደ ድርጅት አብን ሲያቀርበው መቆየቱ የሚታወቅ ኃቅ ሲሆን ፍትኅ ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መላው የአማራ ሕዝብ፣ የንቅናቄያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ለዘመናት ሲያቀርቧቸው የቆዩት የፖለቲካ ጥያቄዎች ትክክልና ቅቡል መሆናቸውን ያረጋገጠ መንግስታዊ ምክረ-ኃሳብ በመሆኑ እንኳን ደስ ያላችሁ እያልን፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በብዙ የተገፋው የአማራ ሕዝብ አሁንም የፍትኅ፣ የእኩልነትና የዴሞክረሲ ብሎም ሰላምና ደኅንነትን በተመለከተ ያሉትን ጥያቄዎች ለማስመለስ ይበልጥ የተደራጀና የተቀናጀ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥሉ ስንል ጥሪ እናቀርባለን።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፦

ሀ/ ገለልተኛ ኮሚሽን በማቋቋም ጥልቅ የሆኑ ምርመራዎችን በማድረግና ሪፖርት በማጠናቀር ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ፤

ለ/ የሚገኘውን ማረጋገጫ መሰረት በማድረግ እስካሁን የነበሩትን አጠቃላይ ድክመቶች በማጋለጥ ለወደፊቱ በዘላቂነት እንዲታረሙ ማስቻል ይገባል።

ሐ/ በፖለቲካ ቁርጠኝነት መጓደል ምክንያት ለተፈፀሙት በርካታ ዘርና እምነት ተኮር ጥቃቶች ኃላፊነት መወሰድ አለበት።

መ/ በሽብር ጥቃቶቹ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመካስና ለማቋቋም የሚያስችል አገራዊ የማካካሻ ፍትኅ /restorative justice/ ሊዘረጋ ይገባል።

ሠ/ ትሕነግና ኦነግ-ሸኔ ያስከተሏቸውን የማኅበራዊ ሰቆቃዎችና አገራዊ ምስቅልቅሎች ግዝፈት እንዲሁም በአገራዊ ኅልውናችን ላይ የደቀኑትን ከባድ አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን ምክረ ኃሳብ የተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ተቀብሎ እንዲያፀድቀው የከበረ አደራችንን ለማቅረብ እንወዳለን።

ረ/ ትሕነግና ኦነግ-ሸኔ በከፈቷቸው የተቀናጁ ጥቃቶች በሕዝብና በአገር ላይ በቀጥታ ከደረሱት በርካታ የሰብዓዊና የንብረት ውድመቶች በተጨማሪ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ በፖለቲካና ተጓዳኝ ተቋማት፣ እንዲሁም በግለሰቦችና ወዳጆች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት በማጉደፍ እርስበእርስ ለመጠራጠር፣ ለመጠላላትና ለግጭት እንዲጋለጡ አድርገው መቆየታቸውን መተማመን ይገባል።

ሰ/ የትሕነግና ጽንፈኛ የኦነግ-ሸኔ የሽብር ድርጅቶች የአገራችንን መልካም ስም ያጠለሹ ከመሆናቸውም በላይ በአለማቀፉ የዲፕሎማሲ ግንኙነታችን ላይ ያስከተሏቸውን አሉታዊ ተጽእኖዎች በመረዳት በጎ አገራዊ ኃይሎችን ከአገር ጎን በማሰለፍ የማስተካከያ ርምጃዎችን ለመውሰድ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይገባል።

ሸ/ የጥፋት ኃይሎቹን በሕግ የመፈረጅ እርምጃውን ተከትሎ የሚኖረው የሕግ አስፈፃሚ አካላት ብቃትና ቁርጠኝነት ለስኬቱ የሚኖረውን ቁልፍ አስተዋፅኦና አንድምታ በመገንዘብ አፈፃፀሙን በማያወላዳ ሁኔታ ማረጋገጥ ይገባል። በአፈፃፀም ኺደት የሚፈጠሩ መፋለሶች፣ የአቅምና የፍላጎት እጥረቶች፣ ሕገ-ወጥ ጥሰቶች፣ የወገንተኝነትና የአድሎኝነት ተግባራት ያሉትን ችግሮች ይበልጥ ሊያባብሱ እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባል።

በመጨረሻ በአገራችን ውስጥ በተደራጀ መልኩ የተነሱ፣ የተቀነቀኑና የማታገያ አጀንዳ ሆነው ካገለገሉ በርካታ ታሪካዊ ጥያቄዎች መካከል ጊዜያዊ የጠመንጃ የበላይነትን በመጠቀም ንጥል የሆኑ ድርጅታዊ አጀንዳዎችን በሕዝብ ላይ በመጫን፣ ሕገ-መንግስታዊና መዋቅራዊ ቅርጽ በማላበስ አግላይ፣ ፈራጅና ዘረኛ የሆነ የአምባገነን ሥርዓትን በማንበር ሕዝባችንንና አገራችንን ላልተቋረጠ የኋልዬሽ ጉዞ ዳርገውት ቆይተዋል።

የሕዝቦችን መብት ማስከበር ይገባል በሚል ሰበብ የሉዓላዊነት መሰረት ለሆነው «የኢትዮጵያ ሕዝብ» እንዲሁም የዴሞክራሲ መሰረት ለሆነው “አገራዊ ዜግነት” እውቅና በመንፈግ በምትኩ ለአምባገነንነት፣ ለጭቆና፣ ለክፍፍልና ለፍረጃ ብሎም የቅራኔና የግጭት ምንጭ የሆነው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ተመስርቶ ቆይቷል። በአገራችን ላይ የተጋረጡት ችግሮች የጥላቻ ፖለቲካ፣ የሰላም እጦት፣ የመሰረታዊ መብት ጥሰቶች፣ የአፈና ተግባራት፣ ዘርፈ-ብዙ የሆኑ ዘርና እምት ተኮር ጭፍጨፋዎች በዋናነት ምንጫቸው ሥርዓቱና መዋቅሮቹ መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም።

የጥቃቶቹና ጥፋቶቹ ግንባር ቀደም መሀንዲሶች የሆኑትን አካላት በሽብርተኝነት የመፈረጁና በሕግ አግባብ የመዳኘቱ (አዋጅ ቁ .1176/ 2012) ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ዘላቂ እልባት ለማምጣት በሚያስችሉ ተግባራት ዙሪያ ከፍተኛ ትኩረትና ርብርብ እንዲደረግ አብን በድጋሜ ለማሳሰብ ይወዳል።

በዚህ ረገድ የትሕነግንና ጽንፈኛ የኦነግ-ሸኔ ኃይሎችን በሽብርተኝነት ስንፈርጅ አገራችንና ሕዝባችን እነሱ ባቋቋሙት ሥርዓት የተተከለውን ትርክት፣ ሕገ-መንግስትና መዋቅር ተሸክመው የሚቀጥሉበት አመክንዬ(logic) ሊኖር አይችልም። ስለሆነም ጥቅል የሆነው የአገራዊ ፖለቲካ ምልከታና እንቅስቃሴ ከምርጫ ተኮር ዴሞክራሲ (electoral democracy) በመሻገር የብሔራዊ ውይይትና ድርድር እርከን እንዲኖረው በማድረግ አካታች እና አሳታፊ የዴሞክራሲ (deliberative democracy) ሂደት እንዲከፈት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ንቅናቄያችን አበክሮ ለማስገንዘብ ይፈልጋል።

ሚያዚያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም

አዲስ አበባ፥ ሸዋ፥ ኢትዮጵያ!

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ National Movement of Amhara