ሱዳን ወደነበረችበት ከተመለሰች ለድርድር እንቀመጣለን – ኢትዮጵያ

“ሱዳን ወደቀደመ ይዞታዋ ከተመለሰች ኢትዮጵያ ለድርድር ዝግጁ ናት” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በቱርክና ህንድ ጉብኝት ማድረጋቸውንና በቆይታቸውም በሀገራቱ ግንኙነትና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከሀገራቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መምከራቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳዮች የማስረዳት ሥራዎችም ተሠርተዋል ብለዋል።

ከሀገራቱ ጋር ያለውን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ማሳደግ የሚያስችሉ ውይይቶችም መካሄዳቸውንም አንስተዋል፡፡ ከህንድ ጋርም በምርምርና ቪዛ ዙሪያ ስምምነቶች ተካሂደዋል ነው ያሉት።

ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋርም በተካሄደ ውይይት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም ትግራይን መልሶ በማቋቋም ዙሪያና የኢትዮ ሱዳን ድንበር ሁኔታን የማስረዳት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በሳምንቱ የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም የአውሮፓ ሕብረትን በመወከል በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውንና እየተከናወኑ ያሉ የሰብዓዊ እርዳታ ሥራዎችን እንዲገነዘቡ መደረጉንም ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ከ75 በላይ ዓለምአቀፍ ተቋማት በ92 የእርዳታ ማዕከላት እርዳታ እየሰጡ መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡

አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን በተመለከተ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ እንደሆነና በሳምንቱም 1 ሽህ 600 ዜጎች መመለሳቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ጉዳይ በተመለከተ በመግለጫቸው አምባሳደር ዲና እንዳሉት ወታደራዊ ክንፉ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ገልጸው፤ በድርጊቱ መጠቀም የሚፈልግ ሦስተኛ ወገን መኖሩንንና ይህም ለቀጣናው ሰላም ስጋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሱዳን ወደቀደመ ይዞታዋ ከተመለሰች ኢትዮጵያ ድርድሮችን ለማካሄድ ዝግጁ መሆኗን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።

የማደራደርና የማስታረቅ ሥራ ለመሥራት የሚጠይቁ ወገኖች አሉ፤ ጥያቄያቸው ተገቢ በመሆኑ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን ቅድመ ሁኔታ ሱዳን ተቀብላ ወደነበረችበት ከተመለሰች ለድርድር እንቀመጣለን ነው ያሉት።

ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር መልካም ግንኙነት የመፍጠር ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር