አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ዐረፉ
የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ አጭር ዜና ሕይወት
ልደት፡-
ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ በጎንደር ክፍለ ሀገር፣ በደብረ ታቦር አውራጃ በፋርጣ ወረዳ ልዩ ስሟ መገንታ ቍስቋም በተባለች ደብር፣ ከቄስ ወርቅነህ ትኩ እና ከወይዘሮ አንጓች አታሌ በ1916 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡
–
መንፈሳዊ እና ዘመናዊ ትምህርት፡-
በሕፃንነት ዕድሜያቸው፥ ከደጉ አባታቸው ከቄስ ትኩ ፊደል ቈጥረው፣ ንባብ ለይተው፣ ዳዊት ከደገሙ በኋላ የቃል ትምህርት ጀመሩ፡፡ በአቅራቢያቸው ከሚገኘው ድድም ጊዮርጊስ ከመሪጌታ ወንድም ጾመ ድጓ እና ምዕራፍ ተማሩ። ቀጥሎም በዝነኛዋ ደብር አዛውር ኪዳነ ምሕረት ከታላቁ የዜማ መምህር መሪጌታ ጀንበር የዜማ ትምህርታቸውን አጠናከሩ። ከዚያም ወደ ሌላኛው ዝነኛ ደብር አትከና ጊዮርጊስ ከመሪጌታ ፈቃዱ ድጓ ተምረዋል። ቅኔ ቈጥረው የተቀኙት ደግሞ በታላቁ ደብር ቆማ ፋሲለደስ ከሚገኙት ከሊቁ መምህር መሪጌታ ዓምደ ብርሃን ነበር። ቀጥሎም፣ ወደ አማራ ሳይንት ገርት አቡነ አቢብ ተጉዘው ከመሪጌታ አበበ፣ ገርቲ ቅኔያቸውን ከነአገባቡ አጠናክረው ተቀኝተዋል።
ከታላቁ ሊቅ መምህር ሰይፈ ሥላሴ በአዲስ አበባ መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ የመጻሕፍተ ሐዲሳትን ትርጉም ተምረው፣ በመምህርነት በመመረቅ ወንበር ዘርግተው አስተምረዋል። ከሌላው ሊቅ ከመምህር ፊላታዎስ ደግሞ የአምስቱን ብሔረ ኦሪት ትርጓሜ፣ መዝሙረ ዳዊትን፣ መጽሐፈ ኢሳይያስን በሚገባ አጠናቀው ተምረዋል። ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ ከፍተኛ የሃይማኖት ትምህርትን፣ በአገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ተምረዋል።
ከመንፈሳዊው እና ትውፊታዊው ትምህርት ባሻገር፣ ዘመናዊ ትምህርትን አጠናክረው ለመማር፣ በ1939 ዓ.ም. ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተዋል። በዚህም ለአራት ዓመታት ሲሰጥ የነበረውን ሥርዓተ ትምህርት በከፍተኛ ትጋት በመከታተል እና ከጓደኞቻቸው ብልጫን በማሳየት ለሦስት ዓመታት ደጋግመው ተሸልመዋል። በአራተኛው ዓመትም፣ ከወዳጅ ቤተ ክርስቲያን በተገኘው የከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ዕድል ወደ ግሪክ ኦርቶዶክስ ኢኩሜኒካል መንበረ ፓትርያርክ(ቍስጥንጥንያ) ተልከው ልዩ ስሙ “ሐልኪ” በሚባለው የቴዎሎጅ ትምህርት ቤት ገብተው፣ ለአምስት ዓመታት ተምረው በከፍተኛ የቴዎሎጅ ትምህርት ተመርቀዋል። የመጀመርያው ባለዲግሪ ካህን በመኾን በ1949 ዓ.ም. ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
–
ሥልጣነ ክህነት እና ማዕርገ ምንኵስና:-
1. መዓርገ ዲቁናን ከብፅዕ አቡነ አብርሃም በ1927 ዓ.ም.
2. መዓርገ ቅስናን ከብፁዕ አቡነ ይስሐቅ በ1938 ዓ.ም.
3. የመነኰሱት ደግሞ ጣና በምትገኘው ዝነኛዋ የክርስቶስ ሠምራ ገዳም ነው።
ማዕርገ ጵጵስና፡-
በፊት ስማቸው ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህ፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ተብለው መዓርገ ጵጵስናን የተቀበሉት፣ በ1983 ዓ.ም. ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ነው።
–
አገልግሎት፡-
በግሪክ አገር የሚሰጠውን የነገረ መለኰት ትምህርት አጠናቅቀው እንደተመለሱ መደበኛ ሥራቸውን የጀመሩት፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተመድበው የተማሩትን በማስተማር ነበር። ከ1950 እስከ 1952 ዓ.ም. ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር እና መምህር በመኾን ሞያቸውን በተግባር አሳይተዋል። ተዳክሞ የነበረውን ትምህርት ቤት ነፍስ በመዝራት ሥርዓተ ትምህርቱን አሻሽለው፣ መምህራንን አሟልተው፣ ግቢውን አለምልመው በአጠቃላይ የጠፋውንና የጠመመውን አቅንተው ከፍተኛ የሥራ ውጤት አሳይተዋል። ለከፍተኛ ደረጃ እንዲታጩ ያደረጋቸውም፣ በዚህ ትምህርት ቤት በጥንካሬ ያሳዩት የሥራ ፍሬ ነው።
በዚሁ ትምህርት ቤት፣ በዳይሬክተርነት እና በአስተማሪነት ከሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ፣ በወቅቱ በክብር ዘበኛ ራዲዮ ጣቢያ ተከታታይ ፕሮግራም ያቀርቡት የነበረው ስብከተ ወንጌል ታዋቂነትን አትርፎላቸው ነበር። በ1952 ዓ.ም. የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ልዩ ካቢኔ ሲቋቋም፣ ለንጉሠ ነገሥቱ የሚቀርቡትን መንፈሳዊ ጉዳዮች ለማጣራት በሓላፊነት ተመርጠው፣ የመንፈሳዊ ጉዳዮች መምሪያ ዳይሬክተር ኾነው ተሹመዋል። ወዲያውኑም፣ የመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት ኾነው ተሹመው፣ ኹለቱንም ከፍተኛ ሓላፊነቶች እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ለ14 ዓመታት ከፍተኛ የሥራ ውጤት አሳይተዋል። የሠሩአቸውም ሥራዎች እጅግ ብዙዎች ናቸው።
–
በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና በሐዋርያዊ ድርጅት ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡
በሰጡት ሰፊ አገልግሎትም የተሸለሙአቸው ሽልማቶች፤
ሀ) ከኢትዮጵያ መንግሥት
• የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ባለአምበል 1ኛ ደረጃ
• የዳግማዊ ምኒልክ የክብር ኮከብ ባለ አምበል 1ኛ ደረጃ
• የቅድሥት ሥላሴ ኒሻን የኮማንደር ደረጃ ያለፕላኩ
• የቅድሥት ሥላሴ ኒሻን የኮማንደር ደረጃ ከነፕላኩ
ለ) ከውጭ ሀገራት
• ከግሪክ መንግሥት
• ከግሪክ ቤተ ክርስቲያን
• ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን (በግሪክ)
• የላዝሩስ ኒሻን ከኦስትርያ(ቪዬና)
የተሸለሟቸው የክብር አልባሳት፤
1) ጥቄር ካባ ባለራስ ማዕርግ በሙካሽ የተሠራ
2) ቀይ ከፋይ ላይ ወርቅ የተጠለፈበት ካባ እንዲሁም በሙካሽ የተሠራ ቀሚስ
3) ከወርቅ የተሠራ የእጅ መስቀል ይጠቀሳሉ፡፡
በሰሜን አሜሪካ በኒውዮርክ ጽዮን ቅድስት ማርያምን ቤተ ክርስቲያንና በሌሎችም አብያተ ክርስቲያን በማቋቋም እና በማደራጀት ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ ብፁነታቸው ለቤተ ክርስቲያን ካበረከቷቸው መጻሕፍት መካከል፤
1/ ዜና ሕይወቱ ለቅዱስ ጳውሎስ
2/ ስለ እግዚአብሔር መኖር
3/ ትምህርተ አበ ነፍስ
4/ ክብረ ድንግል
5/ ድንግልናዊ ሕይወት
6/ የእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት
7/ እንጸልይ
8/ ማኅበራዊ ኑሮ በኢትዮጵያ
9/ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት
10/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት እና ትምህርት የሚሉት መጻሕፍት በታሪክ ይዘከራሉ፡፡
ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ ከአገር ውጭም በተመሳሳይ አገልግሎት ቆይተዋል፡፡ በመንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ዘርፍ ረጅም ዘመን ላበረከቱት አስተዋፅኦ፣ በካሊፎርኒያ ግዛት ኦክላንድን ጨምሮ በሰባት ከተሞች መታሰቢያ ይኾናቸው ዘንድ፣ በየዓመቱ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጁላይ 19 የልደታቸው ቀን በስማቸው፣ ”የመልከጼዴቅ ቀን” ተብሎ ተሠይሞላቸዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በእርግና በጸሎት ተወስነው ቆይተው፣ በ97 ዓመታቸው፣ ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ድካም በክብር ዓርፈዋል፡፡