ወደ ጦርነት መግባት ይበልጥ ለራሱ ለህወሃት ኪሳራ መሆኑን ነግረነው ነበር – ብ/ጄኔራል ከመል ገልቹ

DW : በፌዴራል መንግሥት እና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) መካከል የነበረው አለመግባባት ውጥረትን ፈጥሮ ወደ ጦርነት መሸጋገሩ ለሀገርና ለህዝብ ከሚሰጠው ጥቅም ጉዳቱ እንደሚከፋ በኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች አመለከቱ። የኦሮሚያ ፓርቲ ሊቀመንበር ብርጋዴር ጄኔራል ከመል ገልቹ እንዳሉት ህወሃት ምርጫውን ከማድረጉ አስቀድሞ እንደ ፓርቲ የጋራ ውይይት አድርገን ወደ ጦርነት መግባት ይበልጥ ለራሱ ለህወሃት ኪሳራ መሆኑን ነግረነው ነበር ብለዋል። ሌላው ፖለቲከኛ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ህወሃት ለጦርነቱ መቀስቀስ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ከሆነ ድርጊቱ የእራስ ቤት ላይ እንደ መለኮስ ይቆጠራል ነው ያሉት። የሆነ ሆኖም አሁንም የሰላሙ መንገድ በሁለቱም ሃይሎች አማራጭ መሆኑ ተስፋ ሊቆረጥበት የማይገባ ነውም ብለዋል የፖለቲካ አመራሮቹ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየታቸው፡፡