ዶ/ር አብይን ንጉሳችን የሚለው አባባል አይመቸኝም #ግርማ_ካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

ዶ/ር አብይን “ንጉሳችን” እያሉ አንዳንድ ወገኖች ሲጠሩ ሰምቻለሁ። ያንን የማለት መብታቸውን አከብራለሁ። ለምን እንደዚያ እንዳሉም ይገባኛል። ዶ/ር አብይ አሁን እያደረጉ ባለው ነገር ከምናምነውና ከምንገምተው በላይ አስደናቂ ነገሮችን እያየን ስለሆነ ነው። ላለፉት ሃያ ሰላሳ አመታት በመሪዎቻችን ተጎድተናል። አንገታችንን ደፍተናል። ተሰደናል። ቀደም ሲል ከነበሩ መሪዎች ጋር ዶ/ር አብይን ስናወዳድራችው፣ ዶ/ር አብይ እዚያ ላይ፣  ማማ ላይ፣  ብናወጣቸው አይፈረድብንም። ሆኖም ግን “ንጉሳችን” የሚለው አባባል በጣም አይመቸኝም።

ዶ/ር አብይ ሰው እንደመሆናቸው ሊሳሳቱ ይችላሉ። ይሳሳታሉም። በመሆኑም ለሰሩት ጥሩ ስራ ሙገሳ እንደሚቸራቸውም፣ ሲሳሳቱ መተቸትም አለባቸው። በሰለጠነ መልኩ በፖሊሲ ዙሪያ እርሳቸውና ደርጅታቸውን መቃወም አስፈላጊ ነው። ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትሬ፣ መሪዬ ናቸው። ንጉሴ ግን አይደሉም። ንጉስ ይገዛል። ዶ/ር አብይ ገዢዬ አይደሉም። ንጉስ ካልሞተ ወይንም ካልተገረሰሰ አይነሳም፣ ጠቅላይ ሚኒስተር ግን ሕዝብ ሲፈለግ የሚሾመው፣ ሲፈለግ የሚሽረው ነው።

በአሁኑ ወቅት ለዶ/ር አብይ ትልቅ ድጋፍ አለኝ። ስደግፋቸው በምክንያት ነው። ለምን እንደምደገፋቸው በስፋት የጻፍኩበት ጉዳይ ነው። ወደፊትም እጽፋለሁ። አንድ ዶላር በቀን የተሰኘውን ሐሳብ ዶ/ር አብይ ከመናገራቸው በፊት ያቀረብኩትና ብዙዎች በተለያዪ ድህረ ገጾች ያነበቡት ሐሳብ ነው። ይሄን ሐሳብ የኔን ጽሁፍ አንበበው ይሁን ወይንም በአጋጣሚ እርሳቸው ልብ ውስጥ ስለነበረ፣ ጠ/ሚኒስተሩ መድገማቸው አስደስቶኛል። ይሄን ሐሳብ ከሐሳብነት ወደ ተግባራዊነት በመለወጥ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ተቋቁሞ በዚያ በኩል አገራዊ ግዴታዉን እንዲወጣ ዶ/ር አብይ ዳያስፖራውን ቻሌንጅ አድርገዋል። ይሄን ቻሌንጅ ከሙሉ ልቤ ተቀብዬ ለተግባራዊነቱ የድርሻዬን ለማበርከት ተዘጋጅቻለሁ። በዚህ ረገድ ለዶ/ር አብይ አስተዳደር ድጋፌን እሰጣለሁ።

ሆኖም ግን በግለሰብ ደረጃ ለዶ/ር አብይ ድጋፍ ቢኖረኝም ደርጅታቸውን ኦህዴድን ግን አጥብቄ ነው የምቃወመው። ኦህዴድ የበላይ በሆነበት በኦሮሞ ክልል የሌሎች ማህበረሰባት መብት አሁንም እንደተረገጠ ነው።አሁንም ኦሮሞኛ የማይናገሩ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ነው የሚቆጠሩት። በአዳማ ፣ በጂማ አብዛኛው አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት ባሉባቸው አካባቢዎች የስራ ቋንቋ ኦሮምኛ ብቻ ነው። መንግስታዊ አገልግሎትም ለማግኘት የግድ ገንዘብ ከፍለው በላቲን አስተርጉመው ነው ማመልከቻዎችንና ደብዳቤዎችን የሚያስገቡት። ሰማኒያ በመቶ የሚሆነው የአዳማ፣ ስድሳ አምስት በመቶ የሚሆነው የጂማ፣ አርባ አምስት በመቶ የሚሆነው የቡራዪ ዞን፣ አርባ በመቶ የሚሆነው የምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ሃያ በመቶ የሚሆነው የአርሲ ዞን … እያልን በኦሮሞ ክልል በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ የአፍ መፍቻ ቋንቋው ኦሮምኛ አይደለም። ሆኖም በኦሮሞ ክልል መንግስት መዋቅር መስሪያ ቤቶች ውስጥ ኦሮምኛ ስለማይችሉ አይመረጡም፣ አይቀጠሩም። በአጭሩ በኦሮሞ ክልል ያለው አፓርታይዳዊ አሰራር ነው። እነዚህን የመሳሰሉ በኦህዴድ መንግስት መዋቅሮች ውስጥ ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ ሕጎችና አሰራሮችን በማሻሻሉ ዙሪያ ከኦህዴድ አምስት ሳንቲም ተግባራዊ የፖሊሲ እንቅስቃሰዎችን አላሳየንም። ታዲያ በተግባር ኢትዮጵያዊነትንና እኩልነት ያልተገበረ፣ ነገር ግን ላይ ላዩን በቃላት ብቻ ኢትዮጵያ የሚልን ኦህዴድ እንዴት ልቀበል እችላለሁ ?

ከኦሕዴድ አልፎ ወደ ፌዴራል መንግስት ስንመጣ፣ ዶ/ር አብይ በቃላት እየነገሩን ያለው የኢትዮጵያ ትልቅነት ተመችቶኛል ብቻ ሳይሆን ልቤን አቅልጦታል። ሆኖም ግን ይህ እርሳቸው የሚናገሩት የኢትዮጵያ ታላቅነት አሁን ባለው ሕግ መንግስት የተንጸባረቀ አይደለም። ሕገ መንግስቱ አገሪቷን በዘር ሸንሽኖ ፣ እንደ እኔ ያሉት ብሄራችን ኢትዮጵያዊነት ነው የምንለውን አገር አልባ አድርጎናል። እኛ ብቻ አይደለንም፣ አማራዉ ከአማራ ክልል ውጭ፣ ኦሮሞው ከኦሮሞ ክልል ዉጭ፣ ጉራጌው ከጉራጌ ዞን ዉጭ፣ ወላያታው ከሲዳማ ዞን ዉጭ ..አገር አልባ ነው። ይሄን አይነት አሰራር ዶ/ር አብይ የማይቀበሉ ስለመሆናቸው ምንም ማስተማመኛ አላገኘሁም። ምን አልባት እርሳቸው በአመራርነታቸው ከቀጠሉ አሁን ያለው በሕወሃትና በኦነግ የተዘረጋዉን የዘር አወቃቀር መጠነኛ ጥገናዊ ለውጦች አድርገዉበት ብቻ ሊቀጥሉም ይችላሉ።ያም መደመር አይደለም፤ መቀናነስ ነው።

አዲስ አበባ ከተማ ኦህዴድ የኦሮሞ ናት ብሎ፣ ቢችል ወደ ኦሮሞ ክልል ለመቀላቀል ካልቻለም ደግሞ በሸገር የኦሮሞ ልዩ ጥቅም ተጠብቆ ፣ ኦሮሞው የበላይ ሆኖ እንዲገኝ አላማ እንዳለው የታወቀ ነው። በኦህዴድ ዘንድ የአዲስ አበባ ሕዝብ መጤና በከተማው ጉዳይ መብት የሌለው ነው። ቀደም ሲል የኦህዴድ ከፍተኛ አመራር አቶ አዲሱ አረጋ “የአዲስ አበባ ሕዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንጂ፣ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት የለውም” ነበር ያሉት። በአዲስ አበባ ጉዳይ የመወሰን መብት ያለው ኦሮሞው ነው ከሚል ሕሳቤ መሰለኝ። ሰሞኑን ደግሞ ጭራሹን አቶ አዲስ ከተናገሩት በባሰ ሁኔታ፣ የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ የመወሰን መብቱን ብቻ ሳይሆን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ተገፎ ፣ ሕገ ወጥ በሆነና የአዲስ አበባ ሕዝብን ፍላጎት ባላንጸባረቀ መልኩ ኦህዴድ ከንቲባ ሾሟል። ይሄ መደመር አይደለም። የአዲስ አበባን ህዝብ መቀነስ ነው።

ሕገ መንግስቱ ኢትዮጵያዊነትን ያሳያል ወይ በሚለውና በአዲስ አበባ ዙሪያ ዶ/ር አብይ ተጠይቀው ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ ብለው ነው ያለፉት። ከዚህም የተነሳ አቋማቸውን ለማወቅ አልቻልኩም።

በመጨረሻ የማነሳው ደግሞ ዶ/ር አብይ በሕዝብ ተወዳጅ ቢሆንም አብረዋቸው ያሉ የኢሕአዴግ አባላት አብዛኞቹ ላለፉት 27 አመታት ሕዝብን ይበድል ከነበረው ህወሃት ጋር ሲሰሩ የነበሩ ፣ አንዳንዶቹን ደም ያለባቸው መሆናቸውን ነው። ሃላፊነት ላይ የተቀመጡት ብቃት ስላላቸው ሳይሆን የኢሕአዴግ አመራር ስለሆኑ ብቻ ነው። በዶ/ር አብይ ካቢኔ ውስጥ፣ ዶ/ር አብይ በአደባባይ “የሚያዝን አልቃሽ ነው” ያሉት ወርቅነህ ገበየሁ ይገኝበታል። እኔ ግን ወርቅነህ ገበየሁን ሳስብ የማስበው፣ ይሁ ሰው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆኖ በዘጠና ሰባት ያስገደላቸው ሽብሬ ደሳለኝን ጨምሮ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የአዲስ አበባ ልጆች እናቶችን እንባ ነው። እንደ ከበደ ጫኔ ያሉ አደርባይ ግለሰቦች አሁንም በሚኒስተሮች ምክር ቤት ውስጥ አሉ። ዶ/ር አብይ እነዚህ የተወሰኑ ደም በእጃቸው ያለባቸውን፣ ሌሎችም አደርባዮችን ሳያራግፉ በቀጣይነት ራእያቸውን ይፈጽማሉ ብዬ አላስብም።

የሚቀጥሉት ሁለት አመታት የዶ/ር አብይ አመታት ናቸው። በነዚህ ሁለት አመታት ጠቅላይ ሚኒስትሬ ናቸው። የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ናቸው። የሕዝቡን ሙሉ ድጋፍ ያገኛሉ ብዬ እጠበቃለሁ። ሆኖም ከሁለት አመታት በኋላ ግን የኔ የምላቸው፣ የኔ ሕልዉና በተመለከቱ ያሉ ጥያቄዎች ካልተመለሱ ዶ/ር አብይን ለመደገፍ አልችልም። እንደዉም በዶ/ር አብይ ተቃራኒ የምሰለፍ ነው የሚመስለኝ። ዶ/ር አብይን ንጉሴ ናቸው ካልኩ ያንን ማድረግ አልቻልም። ለዚህም ነው ነገ ለመተቸትና ለመቃወም እንዲመቸኝ አሁን ስደገፍ ድጋፌ በለከት የማደረገው።