አባላቶቹ እየታሰሩበት መሆኑን አብን ተናገረ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ መከልከሉ አግባብ ካለመሆኑ በላይ ከትናንት ጀምሮ አባላቶቹ እየታሰሩበት መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ተናገረ። የፓርቲው ሊ/መንበር አቶ በለጠ ሞላ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ከታሰሩት መካከል በተለያዩ አካባቢዎች ሰልፍ የወጡ አባላቱ ይገኙበታል። ሰልፉ መታገዱን የተለያዩ ፓርቲዎች «የሕገ መንግሥታዊ መብት ክልከላ» ሲሉ ነቅፈዋል። እገዳውን ከተቃወሙት መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)ና ፣የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ ይገኙበታል። የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችም ድርጊቱን ኮንነዋል። DW


ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች፣
ለመላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ !
የአማራን ሕዝብ የትግል ምንነትና ባሕሪ ለመረዳትና የወደፊት አቅጣጫውንም ለመገመት ታሪካዊና ሥር ሰደድ ፖለቲካዊ፣ መዋቅራዊና
ምጣኔኃብታዊ እንዲሁም ማኅበረ-ባኅላዊ መንሥዔዎችን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር አጣምሮ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝባችን በማንነቱ ተነጥሎና ተፈርጆ መንግሥታዊ፣ መዋቅራዊ መገለልና ሥርዓታዊ ጥቃት ደርሶበታል፡፡ ፖለቲካዊ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተገፍፈዋል፤ተገድበዋል፡፡
ባለፉት በርካታ ዓመታት ዘውጋዊ ብሔርተኝነት ብቸኛው የማደራጃና የመብቂያ (ፖለቲካዊ፣ ምጣኔኃብታዊ፣ ማኅበራዊና ባኅላዊ) ርእዮተዓለም መሆኑ እንዲሁም የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጎራ መዳከሙና አማራ-ገፍ ዝንባሌ ማሳየቱ አማራው የራሱን ርእዮታዊ አማራጭ እንዲፈልግ የየበኩላቸውን አስተዋፅዖ አድርገዋል፡፡
አማራው በማንነቱ ተነጥሎ እንደሕዝብ ከብሔራዊው ኅብስት በእኩልነት ተካፋይ የሚሆንበት ዕድል መነፈጉ ለማንነት ትግሉ አንዱ ዋና ገፊ ምክንያት ነው፡፡
ለበርካታ አስርተ ዓመታት የውንጀላና የበቀል ብሔርተኞች የአማራን ሕዝብ በደመኛነት በመፈረጅ እንደማኅበረሰብ ሰላም እንዲያጣ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ ጥቃቶችን ከፍተውበታል፡፡ በታሪኩ፣ በባኅሉና በማንነቱ እንዳይኮራ፤ ታሪኩ ጠልሽቶ፣ ባሕሉና እሴቶቹ ተንቋሽሸው በኃፍረት ተሸማቆ እንዲኖር ለማድረግ ተሞክሯል፡፡
አብን ይህ ስሪት ተቀልብሶ አማራው በነፃነትና በእኩልነት የሚኖርበት ሥርዓተ ማኅበር እንዲመሰረት ይታገላል፤ በመታገል ላይም ይገኛል። ድርጅታችን በመብቶች መካከል ሚዛን መጠበቅ እንዳለበት ቢያስቀምጥም በተግባር የሚፈጠሩ ችግሮች እንደየጉዳዩ ፋይዳ እየተገመገሙ መፈታት እንዳለባቸውም አጥብቆ ያምናል፡፡
የፖለቲካ ተወስዖው እና የፖለቲካ ትርክቱ የአማራ ሕዝብ የእኩልነት፣ የፍትኅና የነፃነት ንቅናቄ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡
ስለሆነም የአማራው ሕዝብና የአብን የፖለቲካ ግብ ለውጣዊ (reformist) ነው፡፡
በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ጥቃት እየተባባሰና አድማሱን እያሰፋ ሕዝባችን በቅርቡ እንኳን በኦሮሚያ ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በደቡብ በጉራ ፈርዳ ተከታታይ ለሆኑ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ የዘር ማፅዳትና የማፈናቀል ጥቃቶች ሰለባ ሆኗል፡፡
አብን በሕዝባችን ላይ ስልታዊ፣ የተደራጀ፣ ሰፊ የመገናኛ ብዙሃን ቅስቀሳ የተደረገበት ዘመቻና በመንግሥት መዋቅር ጭምር የተደገፈ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመበት መሆኑን በመግለፅ መንግሥት ችግሩን እንዲያስቆም ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ጥቃቶቹ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባበሱና አድማሳቸውም እየሰፋ መምጣታቸውን በመገንዘብ መላው የአማራ ሕዝብና አገር ወዳድ ኢትዬጵያዉያን እንዲሁም ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጥቃቶቹንና ምክንያቶችን እንዲያወግዙና መንግስትም ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ለመጠየቅ ሕዝባዊ ሰልፍ መጥራታችን ይታወሳል።
ሆኖም የክልሉ መንግስት እና የከተማ አስተዳደሮቹ በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸውና ተቀባይነት የሌላቸውን ምክንያቶች በመደርደር ሰልፎቹ እንዳይካሄዱ አድርገዋል። ጊዜውንና ሥርዓቱን ጠብቀው የተፃፉ ድርጅታዊ የመጠየቂያ ደብዳቤዎችን ካለማስተናገድ ባለፈ እውቅና ላለመስጠት ጭምር ተሞክሯል። ምንም አንኳን ሰልፎቹ የተከለከሉበት አግባብ ተቀባይነት እንደሌለው የሚታወቅና በድርጅታችንና በሕዝባችን በኩል ይሄን መሰረታዊ መብት በተግባር ለማስቀጠል ፍላጎት የነበረ ቢሆንም የአብን ብሔራዊ ሥራአስፈፃሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር፣ ለሚዲያ አካላት መግለጫ እንዲሁም በሰልፎቹ አመራር ዙሪያ አቅጣጫና ስምሪት ለመስጠት በዋናው ጽ/ቤቱ ውስጥ ስብሰባ በተቀመጠበት ወቅት የአድስ አበባ ከተማ ፖሊስ በኃይል ያልተገባ የማስተጓጎልና የክልከላ ድርጊት በመፈፀሙ ምክንያት ሰልፉን ለመሰረዝ መገደዳችን ይታወቃል።
በዋናነት ግን ሕዝባችን በዚህ የወከባና የደኅንነት ስጋት ውስጥ ሆኖ ሰልፍ ቢወጣ አደጋዎች ሊከሰቱና ጉዳቶች ሊደርሱበት ይችላሉ በሚል ስጋት መነሻነት ሰልፉን ማቋረጥ የተሻለ መሆኑንም ጨምረን ገልፀናል።
አጠቃላይ ሂደቱ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮችን በተመለከተ በድርጅታችን በኩል ጥያቄ ቀርቦ ከመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል። የሰልፉ ሂደት ጋር በተያያዘ በመንግስት በኩል የታዩ ግድፈቶችና ጥሰቶች በውይይት ወቅት በዝርዝር ቀርበው ታምነዋል። በመንግስት በኩልም ይቅርታ ተጠይቋል። በፍጥነት የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድ ስምምነቱን ገልፆ ለድርጅታችን ግልፅ በሆነ መልኩ እንደሚከናወን ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በአብዛኛው ሕዝባችን በድርጅታችን በኩል የተሰጠውን የስጋት አቅጣጫ በመቀበል ተግባራዊ ማድረጉን አስተውለናል።
በሌላ በኩል ሰልፍ የወጣባቸው ከተሞችና አካባቢዎች እንደነበሩና የተወሰኑት በሰላም የተጠናቀቁ ሲሆን በተወሰኑ አካባቢዎች በወጣው ሕዝብ ላይ ያልተገቡ የኃይል አማራጮች ተወስደዋል። ይህ የሚያመላክተው አሁን ያለው ስርዓት ከትላንትናው የማይለይ አምባገነናዊነቱን ያሳየበት ነው። በሕዝባችን፣ በድርጅታችን አባላት፣ አመራሮች እና ደጋፊዎች ላይ የማዋከብ እና የእስር እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙና የታሰሩትም እንዲፈቱ ጠይቀን በርካታዎቹ እልባት እንዳገኙ የታወቀ ሲሆን በቀሩት ላይም ማስተካከያዎች እንዲደረጉ አቅጣጫ አስቀምጠን እየሰራን እንገኛለን።
በቀጣይ መንግስት በኩል ሕዝባችን መስዋእትነት የከፈለላቸው መሰረታዊ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ አበክሮ እንዲሰራ፣ በአማራ-ጠሉ ሕገ-መንግስት፣ ሕግጋትና ፖሊሲዎች፣ ሥርዓትና መዋቅሮች ላይ አፋጣኝ የማሻሻያ እና የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ፣ ሕዝባችን በሚኖርባቸው የአገራችን ክፍሎች ሁሉ የሕይወት፣ የኑሮና የፖለቲካ ተሳትፎውን ማረጋገጥ እንዲችል ዋስትና ማግኘት እንዲችል ቀጣይ የተቀናጀና የተጠናከረ የትግል አካሄዶችን በመንደፍ ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል።
ትግላችንን ለማሳለጥ እና እውን ለማድረግ ሕዝባችን አንድነቱን እንዲያጠናክር፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ ትስስሩን እንዲያጎለብት፣ ሰላሙን እና ደኅንነቱን ነቅቶ እንዲጠብቅም ለማሳሰብ እንወዳለን። የመንግስት አመራሮችና የፀጥታ አካላት ከግል የስልጣን ፍላጎትና ከማናቸውም ያልተገቡ የወገንተኝነት አሰራሮች በመታቀብ ሕዝባዊ ውግንና አለኝታነታችሁን እንድታረጋግጡ እና በተለይም ዘወትር በደኅንነት ስጋት ውስጥ የሚኖረውን ሕዝብ የመታደግ ታሪካዊ የአርበኝነት ድርሻችሁን እንድትወጡ ለማሳሰብ እንወዳለን።
የአማራ የሲቪክ አደረጃጀቶች፣ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ማኅበራዊ ተቋማት በአሁኑ ወቅት በሕዝባችን ላይ የተጋረጠው ፈተና የኅልውና በመሆኑ የአሰላለፍ ትንተናችን ፖለቲካ ዘለል መሆን እንዳለበት ተገንዝባችሁ ፍፁም የሆነ አማራዊ የትብብር ማዕቀፍ ለመመስረት መንቀሳቀስ ይጠበቅባችኋል።
የአማራን ሕዝብ በጥላትነት ፈርጀው ጥቃት የሚሰነዝሩ ስብስቦች እንዳሉ ሁሉ አብዛኛው የኢትዬጵያዊ በወገንተኝነት ስሜት ከጎኑ እንደሚሰለፍ ተረጋግጧል። በቀጣይ ከወዳጆቹ እና አጋሮቹ ጋር ሰፊ ትስስሮችን መፍጠር እና መሰረታዊ ጥያቄዎቻችን የሚመለሱት አማራ-ጠልና አፍራሽ የሆነው ኃይል በአገራዊ የበጎዎች ጥምረት ሲሸነፍ እንደሆነ እንገነዘባለን።
በመጨረሻም ለመላው የአማራ ሕዝብ፣ ለድርጅታችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እየመራችሁት ላለው ታሪካዊ የፍትኅ ትግል፣ በሕዝባችን ላይ የሚደርሰውን የዘር ፍጅትና ዘርፈ-ብዙ ጥቃቶች በመቃወም አጋርነታችሁን ለገለፃችሁልን የአገራችን ልጆች፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች አባላትና አመራሮች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር የሚዲያ አካላት፣ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ አክቲቪስቶች፣ ተዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች አብን ከፍ ያለ ምስጋናውን ማቅረብ ይወዳል።